ፍልስጤማዊ እስረኛ ላይ "ወሲባዊ ጥቃት ሲፈጸም" የሚያሳይ ቪዲዮ እንዲለቀቅ ያደረገችው የእስራኤል ጦር ዐቃቤ ሕግ ከኃላፊነቷ ለቀቀች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
*ይህ ዘገባ አንባቢዎችን ሊረበሹ የሚችሉ ገለጻዎችን ይዟል
የእስራኤል ወታደሮች ፍልስጤማዊ እስረኛ ላይ ወሲባዊ ጥቃት ሲያደርሱ የሚያሳይ ነው የተባለ ቪዲዮ ሾልኮ እንዲወጣ ማድረጓን ያመነችው የእስራኤል ጦር ዋና ዐቃቤ ሕግ ከኃላፊነቷ ለቀቀች።
ሜጀር ጄነራል ዩፋት ቶመር የሩሻልሚ የተባለችው ይህቺ የሠራዊቱ የሕግ ባለሙያ፤ በዚህ ሳምንት ፖሊስ የወንጀል ምርመራ መጀመሩን ተከትሎ እረፍት እንድትወጣ ተደርጋ ነበር።
የፖሊስ ምርመራ፤ ስዴ ቴኢማን በተባለው የእስር ተቋም ውስጥ በሚገኝ የደኅንነት ካሜራ የተቀረጸው ቪዲዮ እንዴት ሾልኮ እንደወጣ የሚያጣራ ነው።
ቪዲዮው የእስራኤል ወታደሮች አንድ እስረኛን ገለል አድርገው ወደ አንድ ጥግ ከወሰዱት በኋላ፤ የሚካሄደው ነገር ለመሸፈን የጸጥታ ኃይሎች በተቃውሞ ወቅት በሚይዙት የፕላስቲክ ጋሻ ዙሪያውን ሲከብቡት ያሳያል። በዚህ ወቅት እስረኛው በሹል ነገር ፊንጢጣው ላይ ተወግቷል።
እስረኛው ፊንጢጣው ላይ በደረሰው ጉዳት መራመድ አይችል የነበረ ሲሆን የደረሰበትን ከባድ ጉዳት ለማከም ክትትል ሲደረግለት ነበር። ከዚህ ጥቃት ጋር በተያያዘ አምስት የእስራኤል ጦር ተጠባባቂ ወታደሮች ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ከእስር ተቋሙ ሾልኮ ወጣው ቪዲዮ ነሐሴ 2016 ዓ. ም. 'ቻናል 12' በተባለው የእስራኤል የቴሌቪዥን ጣቢያ ተላልፏል።
ሜጀር ጄነራል ቶመር የሩሻልሚ በጻፈችው ሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ላይ ከወታደራዊው ክፍል ወጥቶ ለመገናኛ ብዙኃን ለደረሰ ማንኛውም ማስረጃ ሙሉ ኃላፊነት እንደምትወስድ አስታውቃለች።
"በሠራዊቱ የሕግ አስከባሪ ባለሥልጣናት ላይ የተሰነዘረውን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ለመቋቋም እንዲቻል ማስረጃው ለመገናኛ ብዙኃን እንዲለቀቅ ፈቅጃለሁ" በማለት ጽፋለች።
ዐቃቤ ሕጓ የጠቀሰችው፤ የተወሰኑ በእስራኤል የሚገኙ የቀኝ ክንፍ ፖለቲከኞች ቪዲዮው እና በእስረኞች ላይ የደረሰን በደል የተመለከቱ ሪፖርቶች የተፈበረኩ እንደሆኑ በመግለጽ ለማስተባበል ያደረጉትን ጥረት ነው።
ሜጀር ጄነራሏ፤ "በእስረኞች ላይ የጥቃት ድርጊት ስለመፈጸሙ አሳማኝ ጥርጣሬ በሚኖርበት በማንኛውም ጊዜ ምርመራ ማድረግ ኃላፊነታችን ነው" ብላለች።
የዐቃቤ ሕጓ መልቀቂያ ደብዳቤ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ዋና አዛዥ እስራኤል ካትዝ፤ ውሳኔዋን የሚደግፍ መግለጫ አውጥተዋል።
"የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ወታደሮችን በሐሰት የጭካኔ ድርጊት የሚከስስ ማንኛውም ሰው የሠራዊቱን የደንብ ልብስ ለመልበስ ብቁ አይደለም" ብለዋል።
ይህ ቪዲዮ መውጣቱን ተከትሎ የእስራኤል ወታደራዊ ፖሊስ አስራ አንዱን ተጠባባቂ ወታደሮችን ለመጠየቅ ወደ እስር ማዕከሉ ባመራበት ወቅት፤ እርምጃውን የተቃወሙ ቀኝ አክራሪዎች ተቋሙን ሰብረው ገብተዋል።
ኋላ ላይ ግን አምስት ተጠባባቂ ወታደሮች በእስረኛ ላይ ከፍተኛ ጥቃት በመፈጸም እና ከባድ አካል ጉዳት በማድረስ ወንጀል ተከስሰዋል። ተጠርጣሪዎቹ ድርጊቱን ፈጽመዋል መባላቸውን ክደዋል።
ሾልኮ የወጣው ቪድዮ፤ ከመስከረም 2016 ቱ የሐማስ ጥቃት ወዲህ ፍልስጤማውያን እስረኞች ላይ በደል እየደረሰ መሆኑን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ለወጡ ዘገባዎች ጠንካራ ማስረጃ ሆኖ ታይቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ኮሚሽን ባለፈው ዓመት ባወጣው ሪፖርት ከጋዛ የተወሰዱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት እና አዋቂ እስረኞች "ለሰፊ እና ስልታዊ በደል፣ አካላዊ እና አእምሯዊ ጥቃት፣ እንዲሁም ወሲባዊ እና ጾታዊ ጥቃት" መጋለጣቸውን ይፋ አድርጎ ነበር።
የተፈጸሙት ድርጊቶች "በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል የሆነ ስቅይት፣ የጦር ወንጀል የሆነ መድፈር እንዲሁም ሌሎች የወሲባዊ ጥቃት ዓይነት" እንደሆኑም ገልጿል።
የእስራኤል መንግሥት የቀረቡበትን ወንጀላዎች ውድቅ አድርጓል። "በዓለም አቀፍ የሕግ ስታንዳርድ" ለመመራት ያለውን "ሙሉ ቁርጠኝትም" በአጽንኦት አንስቷል። በእያንዳንዱ አቤቱታ ላይም ጥብቅ ምርመራ እንደሚያኬድ አስታውቋል።















