እስራኤል ጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት 46 ሕጻናትን ሰዎች ጨምሮ ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

ፍልስጤማዊ ታዳጊ ፍርስራሽ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

እስራኤል ማክሰኞ ምሽት ጋዛ ውስጥ በፈጸመቻቸው ተከታታይ ጥቃቶች 46 ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 104 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የእስራኤል ጦር "በርካታ የሽብር ዒላማዎች እና ሽብርተኞች" ጥቃት መፈጸሙን ያረጋገጠ ሲሆን እርምጃውን የወሰደው ሐማስ በአሜሪካ አደራዳሪነት የፈረመውን የተኩስ አቁም በመጣሱ እና አንድ ወታደር በመገደሉ እንደሆነ ገልጿል።

እስራኤል የፈጸመቻቸው ተከታታይ ጥቃቶች በሰሜናዊ፣ ማዕከላዊ እና ደቡባዊ ጋዛ የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች እና የመኖሪያ መንደሮችን መትተዋል። ጥቃቱ የደረሰባቸው በሰሜናዊ ጋዛ በሚገኙት ጋዛ ከተማ እና ቤት ላሂያ፣ በማዕከላዊ ጋዛ ባሉት ቡሬጂ እና ኑሴራት እንዲሁም በደቡባዊ ጋዛ በሚገኘው ኻን ዩኒስ አካባቢዎች ናቸው።

በጋዛ የሚገኝ አንድ የዐይን ምስክር በበርካታ የመኖርያ አካባቢዎች ላይ ፍንዳታ በተከሰተበት ወቅት "እሳት እና ጭስ" ወደ ሰማይ ሲነሳ መመልከቱን ገልጿል።

የጋዛ የጤና ሚኒስቴር በጥቃቶቹ 104 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል። ከተገደሉት ውስጥም 46 ሕጻናት እና 20 ሴቶች እንደሚገኙበት ገልጿል። ከ250 በላይ የሚሆኑ ሰዎችም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በቡሬጂ በሚገኘው መጠለያ ካምፕ ውስጥ የአንድ ቤተሰብ አባላት ሆኑ አምስት ሰዎች እንደተገደሉ ተገልጿል።

አል ማዋሲ በተባለ አካባቢ በሚገኝ የተፈናቃይ ካምፕ ውስጥ ባለ ድንኳን ውስጥ ተቀምጠው የነበሩ እናት እና አራት ልጆቿም በተመሳሳይ በእስራኤል ጥቃት ተገድለዋል።

ከእነ ልጆቿ የተገደለችው እናት የቅርብ ዘመድ ኡም መሐመድ "ምን ዓይነት ዓለም ነው? ተኩስ አቁም ይህ ነው?" ሲሉ በጥያቄዎቻቸው የተፈጠረባቸው ሐዘን ገልጸዋል። "[ሕጻናቱ] ተኝተው ነበር። ትምህርት ማግኘት ነበር የሚፈልጉት" ብለዋል።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ ሐማስ ጋዛ ውስጥ አንድ እስራኤላዊ ወታደር ገድሏል ሲል ከስሷል። የሞቱ ታጋቾች አስከሬንን ባለመመለስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ጥሷል በማለትም ተጨማሪ ክስ አቅርቧል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ እስራኤል ካትዝ፤ ሐማስ ማክሰኞ ዕለት በጋዛ በሚገኝ የእስራኤል ወታደር ላይ ጥቃት በመክፈት "ደማቅ ቀይ መስመር" ጥሷል ብለዋል።

የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር፤ በጋዛ በሚገኙ ቢያንስ 30 የታጣቂ ቡድኖች አዛዦችን ጨምሮ "በርካታ የሽብር ዒላማ እና ሽብርተኞች" ላይ ተከታታይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል። ከጥቃቱ በኋላም "የተኩስ አቁሙ እንደ አዲስ ተግባራዊ መሆን መጀመሩን" ገልጿል።

ሐማስ በበኩሉ ከጥቃቱ ጋር "ምንም ግንኙነት" እንደሌለው በመግለጽ፤ እስራኤል ስምምነቱን ለማፍረስ እየሞከረች ነው ብሏል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው "ምንም ነገር" የተኩስ አቁም ስምምነቱን አያሰናክልም ሲሉ ተደምጠዋል። ነገር ግን እስራኤል ወታደሮቿ ዒላማ በሚሆኑበት ጊዜ "መልሳ ማጥቃት" እንዳለባት ተናግረዋል።