እስራኤል ሐማስ የተኩስ አቁሙን ጥሷል ስትል ከወነጀለች በኋላ በፈጸመችው ጥቃት በርካቶች ተገደሉ

የሕይወት አድን ሠራተኞች በእስራኤል ጥቃት የተጎዱ ሰዎችን በአምቡላንስ ወደ ሆሰፒታል ሲያደርሱ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

እስራኤል ሐማስ ስምምነት የተደረሰበትን የተኩስ አቁም ጥሷል በሚል በፈጸመችው ተከታታይ የአየር ድብደባ ቢያንስ 33 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ እና የሆስፒታል ምንጮች ገለፁ።

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ ሐማስ ማክሰኞ ዕለት የእስራኤል ወታደሮችን አጥቅቷል ሲሉ ወንጅለውታል።

ከዚህም ባሻገር የታጋቾች አስከሬን ሲመለስ ጥሰት ተፈጽሟል ብለዋል።

ሐማስ ከጥቃቱ ጋር "ምንም ግንኙነት " እንደሌለው በመግለጽ ለተኩስ አቁሙ አሁንም ተገዢ መሆኑን አስታውቋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የተኩስ አቁም ስምምነቱን ምንም ነገር "አደጋ ላይ አይጥለውም" ያሉ ቢሆንም እስራኤል ወታደሮቿ ዒላማ ተደርገው ጥቃት ከተፈጸመባቸው "ምላሽ መስጠት አለባት" ብለዋል።

እስራኤል ማክሰኞ ዕለት በፈጸመችው የአየር ድብደባ በጋዛ ከተማ፣ ቤይት ላሂያ፣ አል ቡረጂ፣ ኑሲራት እና ካን ዮኒስ የሚገኙ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች እና የመኖሪያ ሕንጻዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል።

የጋዛ ሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የሕይወት አድን ሠራተኞች "በተደጋጋሚ በሚፈጸመው የአየር ድብደባ መካከል እና በግብዓት እጥረት ውስጥ ሆነው በአስቸጋሪ ሁኔታ መካከል ሕይወት ለማትረፍ እየሰሩ ነው" ብለዋል።

"የተወሰኑት ያልተገኙት ሰዎች በፍርስራሽ ውስጥ ናቸው፤ በዚህም የተነሳ የሟቾች ቁጥር ይጨምራል የሚል ፍርሃት አለ" ብለዋል።

ማክሰኞ ምሽት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሰጠው አጭር መግለጫ የአገሪቱ ጦር "ከባድ ድብደባ" እንዲፈጽም መታዘዙን የገለፀ ሲሆን ምክንያቶቹን ግን አላሳወቀም።

ካትዝ ግን ማክሰኞ ዕለት ሐማስ በጋዛ በሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች ላይ ጥቃት በመክፈት "በደማቁ የተሰመረውን ቀይ መስመር" ጥሷል ብለዋል።

"ሐማስ ወታደሮቹ ላይ ጥቃት በመፈጸሙ እንዲሁም የተሰዉ ታጋቾችን ለመመለስ የገባውን ስምምነት በመጣሱ በተደጋጋሚ ዋጋ ይከፍላል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የእስራኤል ጦር ባለሥልጣን ሐማስ ጥቃቱን የፈጸመው በተኩስ አቁም ስምምነቱ መሠረት በእስራኤል ጦር ቁጥጥር ስር በሚገኘው የጋዛ አካባቢ "በቢጫው መስመር ምሥራቃዊ ክፍል" መሆኑን ተናግረዋል።

የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ማክሰኞ ከሰዓት በራፋህ የሚገኙ የእስራኤል ወታደሮች የፀረ ሚሳዔል እና ስናይፐር ጥቃት እንደደረሰባቸው ዘግበዋል።

የፍልስጤም ሚዲያዎች በተመሳሳይ ሰዓት የእስራኤል ጦር ድብደባዎችን መፈጸም መጀመሩን ተናግረዋል።

ማክሰኞ ምሽት የእስራኤል ጦር ጥቃት ከፈጸመ በኋላ የዓይን ምስክሮች ጋዛ ከተማ እና ካን ዮኑስን ጨምሮ የተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ ፍንዳታ መሰማቱን ተናግረዋል።

ሐማስ ወታደሮቹ የእስራኤል ሠራዊት ላይ ጥቃት አለመፈጸሙን ገልጾ መግለጫ ያወጣ ሲሆን የእስራኤልን ጥቃት አውግዟል።