ኔታንያሁ ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና መሰጠቱን ሲነቅፉ አመራሮች የተመድን ጉባዔ ረግጠው ወጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በመንግሥታቱ ድርጅት ባደረጉት ንግግር ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና መስጠቱን ነቅፈዋል።
ኔታንያሁ፤ "አይሁዳውያንን መግደል ውጤታማ እንደሚያደርግ ያሳየ አሳፋሪ ውሳኔ" በማለትም ገልጸውታል ።
ንግግራቸውን በሚያደርጉት ወቅት ብዙ አመራሮችና ዲፕሎማቶች አዳራሹን ጥለው በመውጣት ተቃውሟቸውን አሳይተዋል። የጉባዔው አዳራሽ በአብላጫው ባዶ ሆኖ ታይቷል።
ከአዳራሹ ውጪም በታይምስ አደባባይ እስራኤል በጋዛ የከፈተችውን ጦርነት በመቃወም ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል።
እስራኤል በጋዛ የቀጠለችውን ጥቃት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኮንኗል። ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ፣ ካናዳ እና አውስትራሊያን ጨምሮ ሌሎችም አገራት ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና ሰጥተዋል።
ኔታንያሁ በንግግራቸው መክፈቻ 'The Curse' ወይም 'እርግማኑ' ያሉትን ካርታ አሳይተዋል። በካርታው ላይ በመካከለኛው ምሥራቅ ኢራንን በእጅ አዙር የሚደግፉ ኃይሎች ያሏቸውን አሳይተዋል።
እስራኤል አምና በሊባኖስ በሔዝቦላህ ላይ፣ በየመን በሁቲ አማጽያን ላይ፣ በጋዛ በሐማስ ላይ እንዲሁም በኢራን ላይ የፈጸመቻቸውን ወታደራዊ ጥቃቶችን አብራርተዋል።
ባለፈው ሰኔ የኢራን የኒውክሌር ማብላያ ላይ ጥቃት ለማድረስ ያገዟቸውን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን አመስግነዋል።
ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት ከ9/11 ጥቃት ጋር በማስተካከልም ሁለቱ አገራት ተመሳሳይ ጠላት እየተዋጉ መሆኑን አመልክተዋል።
ፍልስጤም አገር ሆና እንድትቀጥል እንደማይፈቅዱና አብዛኞቹ እስራኤላውያን እንደሚደግፏቸው ኔታንያሁ ተናግረዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ኮሚሽን እስራኤል በጋዛ የዘር ጭፍጨፋ ፈጽማለች የሚለውን ለመመርመር መወሰኑን አስመልክተውም "መሠረት አልባ ክስ" ሲሉ አጣጥለዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ክፍሎች እስራኤል ሆነ ብላ ወደ ጋዛ የሚገባውን እርዳታ እየገደበች እንደሆነ ከዚህ ቀደም ገልጸዋል። ባሳለፍነው ነሐሴ በጋዛ ረሃብ መከሰቱንም ድርጅቱ አስታውቋል።
ኔታንያሁ ግን ይህንን ውድቅ አድገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ንግግር በጋዛ በድምጽ ማጉያ እንዲተላለፍ ተወስኗል። የጋዛ ነዋሪዎችን ስልክ በመጥለፍ ንግግሩ በየስልካቸው እንደሚላክም ተናግረዋል።
በጋዛ ያሉ የቢቢሲ ምንጮች ግን ስልኮች ላይ ጠለፋ አለመኖሩን ጠቁመዋል።
ኔታንያሁ ግባቸው በጋዛ ያሉ ታጋቾችን ማስለቀቅ እንደሆነ ጠቅሰው "የኛ ጀግኖች ከተባበሩት መንግሥታት ነው በቀጥታ እየተናገርኩ የምገኘው። ለሰከንድም አልረሳናችሁም። የእስራኤል ሕዝብ ከጎናችሁ ነው። እናንተን ወደ አገራችሁ ሳናስመልስ አንቀርም" ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በጋዛ 48 ታጋቾች የሚገኙ ሲሆን 20 የሚሆኑት በሕይወት እንዳሉ ይታመናል።
የጋዛ ነዋሪ ፋዲል "ንግግሩን በግዳጅ ከበባ ውስጥ ለከተታቸውና በድንኳን ለሚኖሩ ንጹኃን ዜጎች በማስተላለፍ ምን ይጠቀማል? የበለጠ ከማዋረድ በላይ የሚያገኘው ነገር የለም" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
ኔታንያሁ ከሶርያ ጋር ሰላም ሊያወርዱ እንደተቃረቡና የሊባኖስ መንግሥት ሔዝቦላህን ትጥቅ እንዲያስፈታ መጠየቃቸውን ተናግረዋል።
ንግግራቸውን ተከትሎ ከእስራኤል ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። የእስራኤሉ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ይር ላፒድ "ዛሬ ያየነው አልቃሻ ጠቅላይ ሚኒስትር ነው። ንግግሩ በቸከ አገላለጽ ተሞልቷል። የዲፕሎማሲ ቀውሱን ከመፍታት ይልቅ የእስራኤልን ነባራዊ ሁኔታ ወደባሰ ደረጃ ወስዷል" ብለዋል።
ያይር ጎላን የተባሉት የእስራኤል ዴሞክራትስ ፓርቲ መሪ "ንግግሩ ተጎጂነት ይስተጋባበታል። የታጋቾችና የተዋጊዎች መስዋዕትነትን የዘነጋ ነው። በድምጽ ማጉያ ድምጹን ማስተላለፍ ልጅነት፣ አላስፈላጊና እብደት ነው" ብለዋል።
የፍልስጤም ፕሬዝዳንት መሐሙድ አባስ በመንግሥታቱ ድርጅት ጉባዔ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በእስራኤላውያንና ፍልስጤማውያን መካከል ሰላም ለማውረድ ከዓለም መሪዎች ጋር ተባብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ኔታንያሁ ንግግር ካደረጉ በኋላ ትራምፕ ለጋዜጠኞች "ጋዛ ላይ ስምምነት ላይ የደረስን ይመስለኛል" ብለዋል። ምን ማለታቸው እንደሆነ ግን በግልጽ አላስረዱም።
በጋዛ የተኩስ አቁም ሊደረስ እንደሚችል ጭምጭምታዎች እየተሰሙ ነው።















