የፍልስጤም ፕሬዚዳንት ከትራምፕ ጋር በሁለት አገር መፍትሄ ላይ ለመሥራት ዝግጁ ነኝ አሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፍልስጤሙ ፕሬዚዳንት ማሃሙድ አባስ በእስራኤል እና ፍልስጤም መካከል ሰላም ለማምጣት በሚል ሰኞ ዕለት በፈረንሳይ ይፋ የሆነው ዕቅድ ላይ ከዓለም መሪዎች ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናገሩ።
በመንግሥታቱ ድርጀት ጉባዔ ላይ በቪዲዮ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንቱ ሐማስ በወደፊቷ ጋዛ ላይ ምንም ዓይነት የመሪነት ስፍራ እንደማይኖረው አረጋግጠው፤ ትጥቁን እንዲፈታ ጠይቀዋል።
ለፍልስጤም የአገርነት እውቅና ያልሰጡ አገራት እንዲሰጡ እንዲሁም የመንግሥታቱ ድርጅት ሙሉ አባል እንዲያደርጋቸው ጠይቀዋል።
አባስ እስራኤል በጋዛ የምታካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻ የኮነኑ ሲሆን "በ20ኛው እና በ21ኛው ክፍለ ዘመን እጅግ በጣም ዘግናኝ ከሆኑት ሰብዓዊ ቀውሶች መካከል አንዱ" ሲሉ ጠርተውታል።
መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት "ማውገዛቸውን" አስታውሰዋል።
ሐማስ በዚህ ጥቃቱ አብዛኛዎቹ ሰላማዊ ዜጎች ሆኑ 1,200 ሰዎችን ከገደለ እና 251 ደግሞ አግቶ መውሰዱን ተከትሎ ጦርነቱ ተቀስቅሷል።
የሐማስ ጤና ሚኒስቴር ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ቢያንስ 65,502 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጦር ጥቃት ሲገደሉ ከእነዚህ መካከል ግማሽ ያህሉ ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው ብሏል።
የ89 ዓመቱ አባስ እና 80 የልዑካን ቡድናቸው በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቪዛቸው ባለፈው ወር መሰረዙን ተከትሎ በኒውዮርክ የመንግሥታቱ ድርጅት ጉባዔ ላይ በአካል መገኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ የሰላም ጥረትን በማደናቀፍ እና "የፍልስጤም ምናባዊ አገርነትን እውቅና በተናጠል በመፈለግ" ወንጅለዋቸዋል።
አባስ በመንግሥታቱ ድርጅት ላይ በቪዲዮ ባደረጉት ንግግር በቅርቡ ለፍልስጤም አገርነት እውቅና የሰጡ አገራትን ካናዳ፣ አውስትራሊያ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፖርቹጋልን አመስግነዋል።
ፈረንሳይ፣ ቤልጂየም፣ ሉክሰምበርግ፣ ማልታ፣ ሞናኮ፣ ሳን ማሪኖ፣ አንዶራ እና ዴንማርክ ደግሞ ዩኬን ተከትለው እውቅና ሰጥተዋል፥።
አሜሪካ ለፍልስጤም የአገርነት እውቅና መስጠት ሐማስን መሸለም ነው በሚል ትቃወማለች።
አባስ ሰኞ ዕለት በፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑዔል ማርኮን የቀረበውን የሰላም ዕቅድ ደግፈዋል።
የሰላም ዕቅዱ ጋዛን ለማስተዳደር እና "ሉዓላዊ፣ ነጻ እና ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ የሆነ የፍልስጤም ግዛት ለመመስረት" ሐማስን ያገለለ፣ የፍልስጤማውያን አስተዳደርን ያካተተ የሽግግር አስተዳደር እንዲመሰረት ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።
አሜሪካም ሆኑ እስራኤል ዕቅዱን አልተቀበሉትም።
አባስ ግን "ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከፈረንሳይ፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የሰላም መንገድን ከሚቀይሱ እና አጠቃላይ ቀጠናዊ ትብብርን ለማምጣት የሰላም ዕቅዱን ከሚተገብሩ ሁሉም አካላት ጋር ለመስራት ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።
አክለውም የእስራኤል ጋዛን ለቅቆ መውጣት እና በወረራ ከያዘችው ዌስት ባንክ ጋር መገናኘትን ተከትሎ በጋዛ ሰርጥ "ሙሉ ኃላፊነት" የሚወስድ የፍልስጤም አስተዳደር እንዲኖር ጠይቀዋል።
እስራኤል ከዚህ ቀደም ከጦርነቱ በኋላ የፍልስጤም አስተዳደር በጋዛ የሚኖረውን ሚና ውድቅ አድርጋ ነበር።
የፍልስጤም ፕሬዚዳንት " የጦርነቱን ማብቃት ተከትሎ ብሔራዊ ሪፎርም እንዲሁም በአንድ ዓመት ውስጥ ፕሬዚዳንታዊ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ" እንደሚደረግ ተናግረዋል።
"ዲሞክራሲያዊ፣ ዘመናዊ መንግሥት ለዓለም አቀፍ ሕግ፣ የሕግ የበላይነት፣ የብዝሃነት ስርዓት፣ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እና የሴቶች እና የወጣቶች ሥልጣን መረጋገጥ እንፈልጋለን።"
ፍልስጤም ለመጨረሻ ጊዜ ምርጫ ያካሄደችው እአአ በ2006 ሲሆን ሐማስ ማሸነፍ ችሏል።
ቡድኑ ከአንድ ዓመት በኋላ የፖለቲካ ተቀናቃኙ የሆነውን የአባስ አንጃ፣ ፋታህ ከጋዛ እንዲወጣ በማድረግ አካባቢውን ለብቻው ተቆጣጥሯል።















