ለፍልስጤም አገርነት እውቅና መስጠት ምን ማለት ነው?

የፍልስጤምን ባንዲራ የያዘ ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በሚቀጥሉት ቀናት ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ሌሎችም አገራት ለፍልስጤም የአገር እውቅና እንሚሰጡ ይጠበቃል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ለእውቅና ዜናው አሉታው ምላሽ ሰጥተዋል።

"ለሐማስ አረመኔያው ሽብር" ሽልማት የሚሰጥ ውሳኔ ሲሉም አጣጥለውታል።

አሜሪካም እርምጃው ላይ ያላትን ጠንካራ ተቃውሞ ገልፃለች።

ለመሆኑ እውቅና ምን ማለት ነው? ምንስ ጠብ ያደርጋል?

ለፍልስጤም የአገርነት እውቅና መስጠት ምን ማለት ነው?

ፍልስጤም የነበረች እና የሌለች አገር ናት።

በበርካታ የዓለም ክፍል እውቅና ያላት፤ በውጭ አገራት የዲፕሎማቲክ ተልዕኮዎች የከፈተች እና ኦሎምፒክን ጨምሮ በስፓርታዊ ውድድሮች የሚሳተፉ ቡድኖች አሏት።

ይሁን እንጂ ከእስራኤል ጋር ለረጅም ዘመናት በዘለቀው ግጭት ዓለም አቀፍ ስምምነት ያለው ድንበር የላትም። ዋና ከተማም ሆነ ጦር የላትም።

በዌስት ባንክ በእስራኤል ወታደራዊ ወረራ እ.አ.አ በ1990ዎቹ የሰላም ስምምነትን ተከትሎ የተቋቋመው የፍልስጤም ባለሥልጣን መሬቱንም ሆነ ሕዝቡን መቆጣጠር አልቻለም።

እስራኤል ወረራ እየፈፀመችበት ያለው ጋዛ አስከፊ ጦርነት ውስጥ ይገኛል።

በከፊል ግዛቱን የማስተዳደር ሥልጣን ቢኖረውም እውቅና መስጠቱ በተወሰነ መልኩ ተምሳሌታዊ ነው። ጠንካራ የሞራል እና የፖለቲካ መልዕክት ቢኖረውም መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሀቁን እምብዛም አይቀይረውም።

ነገር ግን ተምሳሌታዊነቱም ጠንካራ ነው። የቀድሞ የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ በመንግሥታቱ ድርጅት የሐምሌው ጉባኤ እንደጠቆሙት "ብሪታኒያ የሁለት አገር መፍትሔን በመደገፍ ልዩ የኃላፊነት ሸክም አለባት"።

ላሚ በፍልስጤም ውስጥ ለአይሁዳዊያን አገር ምስረታን የሚፈቅደውን እና እ.አ.አ 1917 የተፈረመውን የቤልፋር ስምምነትን ጠቅሰዋል።

የብሪታኒያ ወታደሮች እ.አ.አ በ1948 በፍልስጤም

የፎቶው ባለመብት, Bettmann Archive/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የብሪታኒያ ወታደሮች እ.አ.አ በ1948 በፍልስጤም የነበረውን አገዛዝ መጠናቀቁን በማስመልከት ሰንደቅ ዓለማ ሲያወርዱ

ስምምነቱ ክቡር ቃል ኪዳን የያዘ ነው ያሉት ላሚ፤ ቃል ኪዳኑም "ፍልስጤም ውስጥ የሚኖሩ አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎች የሲቪል እና ኃይማኖታዊ መብቶች የሚጎዳ ምንም ነገር እንዳይደረግ" የሚል መሆኑን አስታውሰዋል።

የእስራኤል ደጋፊዎች ስምምነቱን የፈረሙት የያኔው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቤልፎር በግልፅ ፍልስጤማውያንን ወይም ብሔራዊ መብታቸውን እንዳልጠቀሱ በተደጋጋሚ ይጠቁማሉ።

ነገር ግን ፍልስጤም ተብሎ የሚታወቀው ግዛት ብሪታኒያ በሊግ ኦፍ ኔሽን እውቅና እ.አ.አ ከ1922 እስከ 1948 ያስተዳደረችው ሲሆን ለረጅም ጊዜ ያልተቋጨ ዓለም አቀፍ ጉዳይ ተደርጎ ይታያል።

እስራኤል በግዛቱ በ1948 የተከሰተች ሲሆን፤ ትይዩ የፍልስጤም አገር ለመመስረት የተደረጉ ጥረቶች በበርካታ ምክንያቶች አልተሳኩም።

ዴቪድ ላሚ ፖለቲከኞች "የሁለት አገር መፍትሔ ብለው መጥራት ለምደዋል" ብለዋል።

የሁለት አገር መፍትሔ ከ1967ቱ የአረብ-እስራኤል ጦርነት በፊት በነበረ ድንበር፣ እስራኤል ከጦርነቱ በኋላ ዋና ከተማዋ አድጋ የወረረችውን ምሥራቅ እየሩሳሌምን ጨምሮ በዌስት ባንክ እና በጋዛ ሰርጥ የፍልስጤም መንግሥት መመመስረት ማለት ነው።

ይሁን እንጂ የሁለት አገር መፍትሔን እውን ለማድረግ የተደረጉ ዓለም አቀፍ ጥረቶች ፍሬ ያላፈሩ ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ሕግ ሕገ ወጥ የሆነው በዌስት ባንክ የእስራኤል ወረራ ፅንሰ ሀሳቡን ባዶ መፈክር አድርጎታል።

የፍልስጤም ሰንደቅ ዓላማ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ፍልስጤምን እንደ አገር ማን እውቅና ሰጥቷታል?

ፍልስጤም አሁን ላይ ከተባበሩት መንግሥታት 193 አባል አገራት ውስጥ 75 በመቶዎቹ እውቅና የተሰጣት አገር ናት።

በመንግሥታቱ ድርጅት "ቋሚ ታዛቢ አገር" የሚል ስም የተሰጣት፤ተሳትፎ የተፈቀደላት ነገር ግን የድምፅ መብት የሌላት አገር ናት።

በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ዩኬ እና ፈረንሳይ (ቡድኑ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ቤልጂየም እና ማልታን ያካትታል) እውቅና ለመስጠት ቃል የገቡ ሲሆን፤ ፍልስጤም በቅርቡ ከተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አምስት ቋሚ አባሎች ውስጥ የአራቱን ድጋፍ ታገኛለች።

ቻይና እና ሩሲያ በ1988 ለፍልስጤም እውቅና ሰጥተዋል።

እርምጃው የእስራኤል ጠንካራ አጋር የሆነችውን አሜሪካን በምክር ቤቱ አነስተኛ ድምፅ እንዲኖራት ያደርጋል።

ዋሽንግተን በአሁኑ ወቅት በሞሐሙድ አባስ የሚመራውን የፍልስጤምን ባለሥልጣን ከምስረታው ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ እውቅና ሰጥታለች።

ከዚህን ጊዜ በኋላ በርካታ ፕሬዝዳንቶች በመጨረሻም ሊመሰረት ለሚችለው የፍልስጤም አገርነት ድጋፍ እንደሚሰጡ ገልፀዋል። ነገር ግን ዶናልድ ትራምፕ አንዱ አይደሉም። በሁለቱም የሥልጣን ዘመናቸው የአሜሪካ ፖሊሲ በእጅጉ ለእስራኤል ድጋፍ መስጠት ላይ ያመዘነ ነው።

ዩኬ እና ሌሎች አገራት ለምን አሁን እውቅና መስጠት ፈለጉ?

ተከታታይ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥታት ለፍልስጤም የአገርነት እውቅና ለመስጠት ንግግር አድርገዋል። ነገር ግን የሰላም ሂደት አካል በማድረስ፤ በሀሳብ ከምዕራባዊያን አገራት ጋር በመተባበር እና "ትልቅ ተፅዕኖ ማምጣት በሚቻልበት ቅፅበት" እውቅና ለመስጠት ያላቸውን ፍላጎት አንፀባርቀዋል።

የዩኬ መንግሥታት በቀላሉ ለምልክት ብቻ እውቅናው ከተሰጠ ስህተት እንደሚሆን እምነታቸውን ገልፀዋል። ተምሳሌታዊ እውቅና ሰዎች በጎነት እንዲሰማቸው ከማድረግ የዘለለ መሬት ላይ እውነተኛ ለውጥ አያመጣም የሚል ስጋት አድሮባቸዋል።

ይሁን እንጂ አሁናዊ ክስተቶች የበርካታ አገራት መንግሥታትን እጅ መጠምዘዙ በግልፅ እየታየ ነው።

በጋዛ የተንሰራፋው ረሃብ፣ የእስራኤል ጦር ላይ የጨመረው ቁጣ እና የሕዝብ የእይታ ለውጥ ዛሬ ላነሳነው ነጥብ እንድንደርስ በማድረግ ሚና ተጫውተዋል።

እርዳታ የተሸከሙ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በጋዛ ሰርጥ የከፋ ረሃብ መከሰቱን ተመድን ጨምሮ በርካታ ድርጅቶች አስታውቀዋል

አንዳንዶች ቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ቃል እንዲገቡ አድርጓቸዋል።

ለካናዳ እውቅና የፍልስጤም አስተዳደር ራሱን የማሻሻል ቁርጠኝነት ላይ የተመሰረተ ሲሆን፤ በ2026 ምርጫ እንዲያካሄድ እና ወታደሮችን መቀነስ እንደ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጧል።

የብሪታኒያ መንግሥት የእውቅና ውሳኔውን ሲያሳውቅ ኃላፊነቱን በተቃራኒ ወገን ላለው አገር ወርውሯል። የእስራኤል መንግሥት በጋዛ ያለውን መከራ ለመቋጨት፣ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ፣ በዌስት ባንክ ግዛቶችን ከመቆጣጠር እንዲገታ እና የሁለት አገር መፍትሔ ላይ ለመድረስ ለሰላም ሂደት ቁርጠኛ ካልሆነ በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለፍልስጤም እውቅና እንደሚሰጥ ገልጿል።

ውሳኔው ግርታ የፈጠረ ሲሆን፤ አንዳንድ ተቺዎች እውቅና መስጠቱ ቅድመ ውሳኔ ላይ በሙሉ መውደቅ የለበትም፤ በተለይም ደግሞ በእስራኤል እርምጃ ላይ የተመሰረተ መሆን የለበትም ባይ ናቸው።

በብሪታኒያ መንግሥት የተቀመጡት አራት ነጥቦች ወደ ጉልህ ትግበራ እንደማይገቡ ከወዲሁ መታወቁ እውቅናውን አይቀሬ እንደሚያደርገው ውስጥ ውስጡን ይታመናል።

እርምጃቸውን በማቀናጀት አጋራት የአገርነት እውቅና ለመስጠት ቃል መግባታቸው በጋዛ ጦርነቱን ለማስቆም እርዳታ በማስተባበር እና የፖለቲካ ሂደት ለመከተል ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ፍልስጤም ተስፋ እንድትይዝ አድርጓል።

የአሜሪካ ተቃውሞ

የትራምፕ አስተዳደር እውቅና መስጠት ላይ ያለውን ተቃውሞ ደብቆ አያውቅም።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሐሙስ በሰጡት መግለጫ በጉዳዩ ላይ ከዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር አለመስማማታቸውን ገልፀዋል።

ሁለቱ መሪዎች አንድ ለአንድ ባደረጉት ንግግር በጉዳዩ ላይ መምከራቸውን ተናግረዋል።

የአሜሪካ አቋም የፍልስጤም ነፃነት ላይ ጠንካራ ተቃውሞ እንዳላት ግልፅ ነው።

ባለፈው ሰኔ በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሀክቢ አሜሪካ የፍልስጤም የአገር ምስረታን ከዚህ በኋላ እንደማትደግፍ ጠቁመዋል።

በቅርቡ ደግሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ለፍልስጤም እውቅና ለመስጠት ዓለም አቀፍ ጫና ሐማስ 'የበለጠ ድፍረት እንዲሰማው ያደርጋል' ብለዋል።

ሩቢዮ ከኔታኒያሁ ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ ያደረጉት ንግግር የእስራኤል መንግሥት እውቅናው የሐማስን የመስከረም 26 2016 ዓ.ም. ጥቃት ተከትሎ "ለሽብርተኝነት ሽልማት" ነው የሚለውን አቋሙን ያስተጋባ ነው።

ሩቢዮ አክለውም አሜሪካ እውቅና ለመስጠት እየወተወቱ ላሉ አገራት እርምጃቸው እስራኤል ዌስት ባንክን እንድትቆጣጠር ይገፋፋታል ብላ ማስጠንቀቋን ተናግረዋል።