እስራኤል ቅድመ ሁኔታዎችን ካላሟላች ዩናይትድ ኪንግደም ለፍልስጤም መንግሥት እውቅና ልትሰጥ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስራኤል "በጋዛ ያለውን አስከፊ ሁኔታ ለማስቆም ተጨባጭ እርምጃዎችን" ካልወሰደች ዩናይትድ ኪንግደም በመስከረም ወር ለፍልስጤም እውቅና እንደምትሰጥ ጠቅላይ ሚኒስተር ኪር ስታርመር ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነትን ማድረግ፣ የሁለት አገር መፍትሄ የሚያመጣ ዘላቂ ሰላም ማስፈን እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ አቅርቦቱን እንደገና እንዲጀምር መፍቀድን ጨምሮ፣ ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት አለባት፤ አለዚያ እንግሊዝ እርምጃውን በመስከረሙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ትወስዳለች ብለዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እርምጃው "ለሐማስ አስከፊ አሸባሪነት ሽልማት ነው" ብለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ከዚህ ቀደም ለፍልስጤም እውቅና መስጠት እንደ የሰላም ሂደት አካል ከፍተኛ ተጽዕኖ በሚያሳድርበት ጊዜ ሊደረግ ይገባል ሲል ተናግሯል።
ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፍጥነት እርምጃ እንዲወስዱ ከራሳቸው የፓርላማ አባላት ጭምር ጫና እየደረሰባቸው ነው።
ባለፈው ሳምንት ፈረንሳይ በመስከረም ወር ለፍልስጤም መንግሥት በይፋ እውቅና እንደምትሰጥ አስታውቃለች። ይህም በቡድን ሰባት ውስጥ ካሉ አገራት የመጀመሪያዋ ያደርጋታል።
አስቸኳይ የካቢኔ ስብሰባ ካደረጉ በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ኪር፣ እቅዱን አሁን እያስታወቁ ያሉት በጋዛ ስላለው "ትዕግሥት የሚፈትን ሁኔታ" እና "የሁለት መንግሥታት የመፍትሄ ዕድሉ እየቀነሰ ነው" የሚል ስጋት ስላደረባቸው ነው።
ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የእንግሊዝ ግብ የሆነው "ዘላቂ እና ሉዓላዊ የፍልስጤም መንግሥት ጋር ደህንነቷ የተጠበቀ እስራኤል" የመመስረት ዓላማ "ከመቼውም ጊዜ በላይ ጫና ውስጥ ነው" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም "ዋና ዓላማው" በጋዛ መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ማሻሻል፣ እርዳታ መግባቱን ማረጋገጥ ጭምር ነው።
ዩናይትድ ኪንግደም የእስራኤል መንግሥት እንዲወስድ የምትፈልገውን እርምጃዎች ሲገልጹ፣ ኪር በዌስት ባንክ ውስጥ ምንም ዓይነት ወረራ እንደማይኖርም ግልፅ ማድረግ አለበት ብለዋል።
አሁን ያለው የእስራኤል መንግሥት ወደ ሁለት አገር መፍትሄ መሄዱን ይቃወማል፤ ስለዚህ በቅድመ ሁኔታዎቹ የመስማማት ዕድሉ በጣም ጠባብ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ሰር ኬር ሐማስ ሁሉንም ታጋቾች በአስቸኳይ መልቀቅ፣ የተኩስ ማቆም ስምምነት ማድረግ፣ ትጥቅ መፍታት እና በጋዛ መንግሥት ውስጥ ምንም ዓይነት ሚና እንደማይጫወቱ መቀበል አለበት ብለዋል።
ኔታንያሁ ዩናይትድ ኪንግደም መግለጫ ምላሽ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ "ዛሬ በእስራኤል ድንበር ላይ ያለ የጂሃዲስት መንግሥት ነገ ብሪታንያን ያስፈራታል" ሲሉ ጽፈዋል።
"ለጂሃዲስት አሸባሪዎች ማባባያ መስጠት ሁሌም ይከሽፋል። አይሆንም"
ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ያውቁ እንደሆን የተጠየቁት ዶናልድ ትራምፕ ሰኞ ዕለት በስኮትላንድ በነበሩበት ወቅት ባደረጉት ውይይት ሁለቱ መሪዎች "በጭራሽ አልተወያየንበትም" ብለዋል።
ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ጉዳዩን ልታደርጉት ትችላላችሁ... ይህን ካደረጋችሁ ለሐማስ ሽልማት ነው። እና እነሱ መሸለም ያለባቸው አይመስለኝም።"
ዩናይትድ ስቴትስ እንደ ብዙ የአውሮፓ አገራት ሁሉ ለፍልስጤም መንግሥት እውቅና የምትሰጠው ለግጭቱ ዘላቂ ጊዜ መፍትሄ ለማምጣት የሚደረገው እንቅስቃሴ አካል ከሆነ ብቻ እንደሆነ ተናግራለች።
የሊበራል ዴሞክራት መሪ ሰር ኤድ ዴቪ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥትን መግለጫ "ወሳኝ እርምጃ" ሲሉ በደስታ ቢቀበሉትም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፍልስጤም መንግሥት በአስቸኳይ እውቅና እንዲሰጡ እና "በጋዛ ያለውን ሰብዓዊ አደጋ ለማስቆም እጅግ የላቀ እርምጃ" እንዲከተሉ አሳስበዋል።
አክለውም "ከብዙ ወራት በፊት መካሄድ የነበረበትን እውቅና እንደ መደራደሪያ ከመጠቀም ይልቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጦር መሳሪያ ሽያጭን ሙሉ በሙሉ በማቆም እና በእስራኤል ካቢኔ ላይ የሚጣሉ ማዕቀቦችን በመተግበር በእስራኤል ላይ ጫና ማድረግ አለባቸው" ብለዋል።
255 የሚሆኑ የፓርላማ አባላት የዩኬ መንግሥት በአስቸኳይ ለፍልስጤም መንግሥት እውቅና እንዲሰጥ የሚጠይቅ ደብዳቤ ፈርመዋል፤ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሌበር ፓርቲ ፓርላማ አባላት ናቸው።
ደብዳቤውን ያስተባበረችው የሌበር ተወካይ ሳራ ሻምፒዮን በውሳኔው በጣም እንደተደሰተች እና እፎይታ እንደተሰማት ተናግራለች።
"ይህ በእስራኤል ላይ ፖለቲካዊ ጫና ይፈጥራል እና በጋዛ እና በዌስት ባንክ እየተካሄደ ያለው ነገር ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት እንደሌለው ግልጽ ያደርገዋል" ብላለች።















