220 የዩኬ ፓርላማ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፍልስጤም አገርነት እውቅና እንዲሰጡ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
220 የዩናይትድ ኪንግደም ፓርላማ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ለፍልስጤም አገርነት እውቅና እንዲሰጡ ፊርማቸውን ባኖሩበት ደብዳቤ ጠየቁ።
ከሲሶ በላይ የሚሆኑት የፓርላማ አባላቱ ከዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ ሲሆን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ደግሞ የሌበር ፓርቲ አባላት ናቸው።
ፖለቲከኞቹ ዩናይትድ ኪንግደም ለፍልስጤም ዕውቅና መስጠቷ "ጠንካራ" መልዕክት እንደሆነና ሁለት አገር የመመስረት መፍትሄ ለመስጠትም ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ በመልዕክታቸው አስፍረዋል።
ፈረንሳይ በጥቂት ወራት ውስጥ ለፍልስጤም አገርነት እውቅና እንደምትሰጥ ማስታወቋን ተከትሎ የመጣው የፓርላማ አባላቱ ደብዳቤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጫና እንደሚፈጥር ተገልጿል።
ኪር ስታርመር ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና ከጀርመኑ ቻንስለን ፍሬድሪክ መርዝ ጋር አስቸኳይ የስልክ ጥሪ ካደረጉ በኋላ በሰጡት መግለጫ ለፍልስጤም አገርነት እውቅና መስጠት የሁለት አገራት ምስረታን መፍትሄ የሚያመጣ "ሰፋ ያለ እቅድ መሆን አለበት" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው "ከቅርብ አጋሮቻችን ጋር ሆነን በዚህ ጦርነት እየተሰቃዩ ባሉ ሰዎች ላይ ለውጥ በሚያመጡ ተግባራዊ እርምጃዎች ላይ በማተኮር በቀጣናው ሰላም እንዲመጣ እየሰራሁ ነው" ብለዋል።
አክለውም "ይህ እርምጃ የተኩስ አቁምን ወደ ዘላቂ ሰላምነት ለመቀየር የሚያስፈልጉ ተጨባጭ እርምጃዎችን ያስቀምጣል" ብሏል።
"ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና መስጠት ከነዚህ እርምጃዎች አንዱ መሆን አለበት። ለዚህ ምንም አትጠራጠሩ" ብለዋል።
"ሆኖም ለፍልስጤማውያን እና እስራኤላወያን የሁለት አገር መመስረትን እንዲሁም ዘላቂ ደህንነትን የሚያመጣ ሰፊ እቅድ አካል መሆን አለበት" ብለዋል።
ደብዳቤው እንደ የቀድሞው ሚኒስትር ሊያም ባይረን እና የትራንስፖርት ኮሚቴ ሊቀመንበር ሩት ካድበሪ ያሉ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሪ 131 የሌበር ፓርላማ አባላት ተፈርሟል።
ደብዳቤው ፓርላማው የፍልስጤም አገርነት እውቅና የሁለት አገራት ምስረታ አካል መሆኑን ለአስርት ዓመታት በተለያዩ ፓርቲዎች መካከል ስምምነት ሲያደርግ ቆይቷል ሲል ተከራክሯል።
እውቅና ብቻውን በጋዛ ያለውን ስቃይ ማስቆም ባይችልም "ብሪታንያ በቀጣናው ካላት ታሪካዊ ዳራ አንጻር ለፍልስጤም ዕውቅና መስጠቷ ጠንካራ መልዕክት ነው" ብለዋል።
ደብዳቤውን ያስተባበሩት እና አለም አቀፍ ልማት የተሰኘ ኮሚቴ የሚመሩት የሌበር ተወካይ ሳራ ሻምፒዮን የሁለት አገራት ምስረታ "በቀጣናውን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ብቸኛው አዋጭ መፍትሄ ነው" ብለዋል።
አክለውም "ዕውቅና መስጠቱ የፍልስጤም ህዝቦችን መብት እንደምንደግፍ፣ ብቻቸውን እንዳልሆኑ እና ለእስራኤልም ሆነ ለፍልስጤም ህዝቦች ዘላቂ ሰላም እና ደህንንት የሚያመጣ መንገድ እንዳለ ተስፋን የሚሰጥ ጠንካራ ተምሳሌታዊ መልዕክት ያስተላልፋል" ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ193 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት መካከል 140ዎቹ ፍልስጤምን በአገርነት ዕውቅና ሰጥተዋታል።
ከነዚህም መካከል ስፔንና አየርላንድን ጨምሮ ጥቂት የአውሮፓ ህብረት አባላት አገራት ይገኙበታል።
እስራኤል በአገርነት፣ በአውሮፖውያኑ 1948 ስትመሰረት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ያፈናቀለች ሲሆን ይህንንም "ናቅባ" (ትልቁ እልቂት) ሲሉ ይጠሩታል።
በአሁኑ ወቅትም ፍልስጤማውያኑ ይኸው ይደገማል በሚል ፍራቻ ላይ ናቸው።
ከቀያቸው የተፈናቀሉት ፍልስጤማውያኑ አብዛኛዎቹ በጋዛ ሰፍረዋል።
በአሁኑ ወቅት ካሉ የጋዛ ነዋሪዎች መካከል ሶስት አራተኛውን የሚይዙት በዚያን ወቅት የተፈናቀሉ የልጅ ልጆች ናቸው።
ሌሎች 900 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ አሁን እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ ይኖራሉ።
3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በዮርዳኖስ፣ ሶሪያ እና ሊባኖስ እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።
የዩናይትድ ኪንግደም፣ የፈረንሳይ እና የጀርመን መሪዎች የስልክ ጥሪን ተከትሎ ያወጡት የጋራ መግለጫ ፍልስጤምን በአገርነት እውቅና የመስጠትን ጉዳይ አይጠቅስም።
ነገር ግን ሶስቱም አገራት "አስቸኳይ የተኩስ አቁም ላይ እንዲደረስ እንዲሁም ለእስራኤላውያን፣ ፍልስጤማውያን እንዲሁም ለመላው ቀጣና ዘላቂ ደህንት እና ሰላም የሚያመጣ የፖለቲካ ሂደትን ለመደገፍ ተጨማሪ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ" መሆናቸውን ገልጸዋል።
መግለጫው የእስራኤል መንግሥትን በመተቸት የእርዳታ እገዳ እንዲቆም የጠየቀሰ ሲሆን "በጋዛ እያየነው ያለው ሰብዓዊ ጥፋት አሁን ማብቃት አለበት" ሲል አስጠንቅቋል።
እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን እርዳታ እንዳይደርሳቸው ከመጋቢት ጀምሮ ሙሉ እገዳ ጥላለች። ለሁለት ወራት የቆየው የተኩስ አቁም መፍረሱን ተከትሎ በጋዛ የማያባራ ጥቃት እያካሄደች ነው።
የእስራኤል ጦር ይሄንን ሁሉ የሚያደርገው ሐማስ የቀሩ ታጋቾችን እንዲለቅ ጫና ለማድረግ ነው ይላል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጋዛ ረሃብ እያንዣበበ ነው የሚል ማስጠንቀቂያ በተደጋጋሚ ማሰማቱን ተከትሎ እገዳው በከፊል ቢላላም አሁንም ፍልስጤማውያኑ በከፍተኛ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የነዳጅ እጥረት እየተፈተኑ ነው።
ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተወሰኑ የእርዳታ መኪኖች በተጨማሪ፤ እስራኤል እና አሜሪካ ለፍልስጤማውያን እርዳታ እናከፋፍላለን በሚል 'የጋዛ ሂውማኒታሪያን ፋውንዴሽን' (ጂኤችኤፍ) የተሰኘ አወዛጋቢ ድርጅት አቋቁመዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እርዳታ ሲጠባበቁ ባሉ ፍልስጤማውያን ላይ በየቀኑ በሚባል ሁኔታ የእስራኤል ጦር በሚከፍተው ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።
በባለፉት ሁለት ወራት የእስራኤል ጦር በእርዳታ ጠባቂ ፍልስጤማውያን ላይ በከፈተው ተኩስ ከ1,000 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ አስታውቋል።
ከእነዚህ ውስጥም 766 ግድያዎች የተፈጸሙት በጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽን ግቢ ውስጥ ነው።
ቀሪዎቹ 288 ፍልስጤማውያን ደግሞ የተገደሉት የተፈጸሙት በተባበሩት መንግሥታት እና በሌሎች የእርዳታ መኪኖች አቅራቢያ ነው።















