ፈረንሳይ ለፍልስጤም አገርነት እውቅና እንደምትሰጥ ፕሬዚዳንቷ ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፈረንሳይ በመጪው መስከረም ፍልስጤምን በአገርነት በይፋ እውቅና እንደምትሰጥ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ገለጹ።
ፈረንሳይ ለፍልስጤም በአገርነት ዕውቅና በመስጠት የመጀመሪያ የቡድን ሰባት አባላት አገር ያደርጋታል።
ፍልስጤምን በአገርነት በይፋ እውቅና የመስጠት እወጃው የሚደረገው በኒውዮርክ በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ እንደሆነም ማክሮን በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
"በአሁኑ ወቅት በአስቸኳይ አስፈላጊው ነገር የጋዛ ጦርነት አክትሞ የሲቪሎችን ህይወት መታደግ ነው። ሰላም ይቻላል። አስቸኳይ የተኩስ አቁም፣ መላው ታጋቾች መለቀቀ እና ለጋዛ ህዝብ ከፍተኛ ሰብዓዊ እርዳታ መሰረታዊ ነገሮች ናቸው" ሲሉም በተጨማሪ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
የፍልስጤም ባለስልጣናት የማክሮንን እርምጃ በበጎነት ሲቀበሉት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሃማስ መስከረም መጨረሻ በእስራኤል ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ውሳኔያቸው "ሽብርን የሚሸልም ነው" ሲሉ ተችተውታል።
አሜሪካ የማክሮንን እርምጃ "በጽኑ እንደምትቃወመው" በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ማርኮ ሩቢዮ በኩል ያስታወቀች ሲሆን፤ ውሳኔውን "ግድየለሽ" ሲሉ ተችተውታል።
ቡድን ሰባት (ጂ7) የሚባሉት የዓለማችን የኢኮኖሚ ኃያል አገራት ስብስብ ሲሆን እነዚህም ፈረንሳይን ጨምሮ፣ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን፣ ካናዳ እና ጃፓን ናቸው።
ማክሮን "ፈረንሳይ ለመካከለኛው ምስራቅ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ባላት ታሪካዊ ቁርጠኝነት፤ ፍልስጤምን በአገርነት እውቅና ለመስጠት ወስኛለሁ" ሲሉ ሐሙስ ዕለት በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
አክለውም "ሐማስ ከወታደራዊ ትጥቅ ውጭ መሆኑን ዋስትና መስጠት አለብን፤ እንዲሁም ጋዛን ደህንነቷን መጠበቅ እና መገንባት ይገባል" ብለዋል።
"በመጨረሻም የፍልስጤምን ግዛት መገንባት፣ እናም ወታደራዊ ትጥቅን በማፍረስ እና ለእስራኤል ሙሉ እውቅና እንድትሰጥ በማድረግ በመካከለኛው ምስራቅ ላሉ ደህንነት አስተዋጽኦ እንዲመጣ ሊደረግ ይገባል። ሌላ አማራጭ የለም" ብለዋል።
ማክሮን ለፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ ውሳኔያቸውን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ አያይዘዋል።
የማክሮንን ውሳኔ ተከትሎ ምላሽ የሰጡት የአባስ ምክትል ሁሴን አል ሼክ " ይህ አቋም ፈረንሳይ ለአለም አቀፍ ህግ ያላትን ቁርጠኝነት እንዲሁም ለፍልስጤም ህዝቦች የራስን እድን በራስ የመወሰን መብት እና ነጻ አገራችንን ለመመስረት የምታደርገውን ድጋፍ የሚያንጸባርቅ ነው" ሲሉ መናገራቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ኔታንያሁ በበበኩላቸው "ከመስከረሙ ፍጅት ማግሥት የፕሬዚዳንት ማክሮን ከቴልአቪቭ አጠገብ የፍልስጤምን በአገርነት መቆም ዕውቅና ውሳኔ አጥብቀን እናወግዛለን" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
ኔታንያሁ አክለውም "በእነዚህ ሁኔታዎች ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና መስጠት ከእስራኤል ጋር በሰላም ለመኖር ሳይሆን እስራኤል ለማጥፋት የማስጀመሪያ እርምጃ ይሆናል። ግልጽ እናድርገው ፍልስጤማውያን ከእስራኤል ጎን ሃገር አይፈልጉም። በእስራኤል ምትክ ሃገር ይፈልጋሉ" ሲሉ ኔታንያሁ አክለዋል።
ሐማስ በበኩሉ የፈረንሳይን ውሳኔ "በትክክለኛ አቅጣጫ ያለ አዎንታዊ እርምጃ" ሲል አወድሶ ሁሉም አገራት የፈንሳይን እርምጃ እንዲከተሉም ጥሪ አቅርቧል።
በአሁኑ ወቅት ከ193 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት መካከል 140ዎቹ ፍልስጤምን በአገርነት ዕውቅና ይሰጧታል።
ከነዚህም መካከል ስፔንና አየርላንድን ጨምሮ ጥቂት የአውሮፓ ህብረት አባላት አገራት ይገኙበታል።
እስራኤል በአገርነት፣ በአውሮፖውያኑ 1948 ስትመሰረት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ያፈናቀለች ሲሆን ይህንንም "ናቅባ" (ትልቁ እልቂት) ሲሉ ይጠሩታል።
በአሁኑ ወቅትም ፍልስጤማውያኑ ይኸው ይደገማል በሚል ፍራቻ ላይ ናቸው።
ከቀያቸው የተፈናቀሉት ፍልስጤማውያኑ አብዛኛዎቹ በጋዛ ሰፍረዋል።
በአሁኑ ወቅት ካሉ የጋዛ ነዋሪዎች መካከል ሶስት አራተኛውን የሚይዙት በዚያን ወቅት የተፈናቀሉ የልጅ ልጆች ናቸው።
ሌሎች 900 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ አሁን እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ ይኖራሉ።
3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በዮርዳኖስ፣ ሶሪያ እና ሊባኖስ እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።















