የእስራኤል ጦር መላውን የጋዛ ህዝብ አፈናቅሎ ወደ ካምፕ የሚያዛውርበት ዕቅድ እንዲያዘጋጅ ታዘዘ

ፍልስጤማውያን በጋዛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የእስራኤል ጦር በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን በሙሉ አፈናቅሎ በደቡባዊ ክፍል በሚዘጋጅ ካምፕ ለማስገባት እቅድ እንዲያዘጋጅ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ትዕዛዝ መስጠታቸውን የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

በራፋህ ከተማ ፍርስራሽ ላይ "ሰብዓዊ ከተማ" ለማቋቋም እንደሚፈልጉ የተናገሩት ሚኒስትሩ እስራኤል ካትዝ ይህም በመጀመሪያ 600 ሺህ ፍልስጤማውያን የሚቆዩበት ካምፕ ይሆናል ብለዋል።

በመቀጠልም አጠቃላይ የጋዛን ህዝብ፣ 2.1 ሚሊዮን የሚያኖር እንደሚሆን አክለዋል።

ዕቅዱ የሐማስ አባላት አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ የጸጥታ እና የደህንነት ምርመራ አድርጎ ወደ ካምፑ ለማስገባት እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ፍልስጤማውያኑ ከካምፑ መውጣት እንደማይፈቀድላቸው ተናግረዋል።

እስራኤል እና ሐማስ የ60 ቀናት የተኩሰ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ እየተደራደሩ ሲሆን ሁኔታዎች ከፈቀዱ በዚህ ወቅት የካምፑ ዝግጅት ይጀመራል ብለዋል።

ይህንን ህዝብ አፈናቅሎ ወደ ካምፕ የማስገባት ዕቅድ ያወገዘው አንድ የእስራኤል የሰብዓዊ መብት ጠበቃ ድርጊቱን "በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም የወንጀል ዕቅድ" ሲሉ አጥብቀው ወቅሰዋል።

"ይህ ሁሉ የሚሆነው ህዝቡን በሙሉ ወደ ደቡባዊ ጫፍ በማዛወር ከጋዛ ሰርጥ ለማባረር የሚደረግ ዝግጅት ነው" ሲሉ ማይክል ስፋርድ ለጋርዲያን ጋዜጣ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አገራት በያዟቸው ግዛቶች ላይ ሰላማዊ ህዝብን ማፈናቀል ወይም በግዳጅ ማዛወር የአለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግን የሚጥስ ሲሆን፤ እንዲሁም እንደ "የዘር ማጽዳት ወንጀል" እንደሚቆጠር ከዚህ ቀደም አስጠንቅቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ህዝቡን አፈናቅሎ ወደ ራፋህ በማዛወር ካምፕ ውስጥ የማስገባትን ዕቅድ በተመለከተ የፍልስጤም ባለስልጣናት ወይም ሐማስ የሰጡት አስተያየት የለም።

ሰኞ ዕለት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የአሜሪካው አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከጦርነቱ በኋላ ጋዛን ተቆጣጥራ ፍልስጤማውያንን አፈናቅላ በቋሚነት ወደ ሌላ ቦታ ለማስፈር ያቀረቡትን ሃሳብ አስመልክቶ በዋይት ሐውስ ተወያይተዋል።

ኔታንያሁ እንዳሉት "ፕሬዚዳንት ትራምፕ ብሩህ ራዕይ አላቸው ብዬ አስባለሁ። ነጻ ምርጫ ነው። ሰዎች መቆየት ከፈለጉ ሊቆዩ ይችላሉ። ከግዛቲቷ መውጣት ከፈለጉ ግን መውጣት መቻል አለባቸው"

አክለውም "ለፍልስጤማውያን የተሻለ የወደፊት መፍጠር እንፈልጋለን በማለት ሁልጊዜም የሚናገሩት አገራት ይህንን እውን እንዲያደርጉ ከአሜሪካ ጋር በቅርበት እየሰራን ነው" ብለዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው "ከቀጣናው አገራት ጋር ታላቅ ትብብር አለን፤ ከእያንዳንዱ አገራት ጋር አጋርነት አለን። ስለዚህ አንድ ጥሩ ነገር ይከሰታል" ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የአረብ መንግሥታት ትራምፕ ላቀረቡት የጋዛ መልሶ ግንባታ ዕቅድ አማራጭ የሆነውን ፍልስጤማውያን ባሉበት እንዲቆዩ ለሚያስችለው የግብጽን የ53 ቢሊዮን ዶላር ዕቅድ ድጋፍ አድርገዋል።

ማንኛውንም የፍልስጤም ህዘብ የመፈናቀል ዕቅድ የዓለም አቀፍ ህግን የሚጥስ፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እና የዘር ማጽዳት ሲሉ ሙሉ በሙሉ የአረብ መንግሥታቱ ውድቅ አድርገውታል።

ይህንን የግብጽ ዕቅድ በፍልስጤም አስተዳደር እና ሐማስ ድጋፍ የሰጡት ቢሆንም አሜሪካ እና እስራኤል በጋዛ ውስጥ ያለውን እውነት መፍታት የማይችል ሲሉ አልተቀበሉትም።

እስራኤል በአገርነት፣ በአውሮፖውያኑ 1948 ስትመሰረት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ያፈናቀለች ሲሆን ይህንንም "ናቅባ" (ትልቁ እልቂት) ሲሉ ይጠሩታል።

በአሁኑ ወቅትም ፍልስጤማውያኑ ይኸው ይደገማል በሚል ፍራቻ ላይ ናቸው።

ከቀያቸው የተፈናቀሉት ፍልስጤማውያኑ አብዛኛዎቹ በጋዛ ሰፍረዋል።

በአሁኑ ወቅት ካሉ የጋዛ ነዋሪዎች መካከል ሶስት አራተኛውን የሚይዙት በዚያን ወቅት የተፈናቀሉ የልጅ ልጆች ናቸው።

ሌሎች 900 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ አሁን እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ ይኖራሉ።

3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በዮርዳኖስ፣ ሶሪያ እና ሊባኖስ እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።