የተመድ ባለሙያ ትልልቅ ኩባንያዎች ከእስራኤል ጋር ያላቸውን የንግድ ግንኙነት እንዲያቆሙ ጠየቁ

የእስራኤል ጦር መድፍ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ማይክሮሶፍት እና አማዞንን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከእስራኤል ጋር የሚያደርጉትን የንግድ ግንኙነት እንዲያቆሙ ጠየቁ።

ኩባንያዎቹ ከእስራኤል ጋር የንግድ ሽርክና በመቀጠል በጋዛ እና እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ እየተፈጸሙ ባሉ የጦር ወንጀሎች ተባባሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ባለሙያዋ ፍራንቼስካ አልባኔዝ አስጠንቅቀዋል።

ለተባበበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ሪፖርታቸውን ያቀረቡት አልባኔዝ "የዘር ማጥፋት ኢኮኖሚ" ሲሉ ጠርተው የጋዛ ጦርነት ምንም አይነት ተጠያቂነት እና ቁጥጥር ሳይደረግበት ለአዳዲስ መሳሪያዎች እና ቴክኖሎጂዎች መሞከሪያ ሆኗል ብለዋል።

እስራኤል የባለሙያዋን ሪፖርት "መሰረተ ቢስ" በማለት ውድቅ አድርጋ "የታሪክ ቆሻሻን ይቀላቀላል" ብላለች።

የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች ወይም ልዩ ራፖርተሮች ከተባበሩት መንግሥታት ነጻ ሲሆኑ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ እንዲያማክሩ የተሾሙ ናቸው።

የጣሊያን ተወላጅ የሆኑት ፍራንቼስካ አልባኔዝ ዓለም አቀፍ ጠበቃ ሲሆኑ እስራኤልን በጠንካራ ሁኔታ በማውገዝ እና በመተቸት ይታወቃሉ።

ከዚህ ቀደም በነበረ ሪፖርታቸው እስራኤል በጋዛ በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው ብለው ነበር።

ሐሙስ ዕለትም እስራኤል "በዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ካሉ ጭካኔ የተሞላበት የዘር ማጥፋት እየፈፀመች ነው" ሲሉ ከሰዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚሁ ሪፖርታቸው አልባኔዝ በጋዛ ውስጥ በሚፈጸሙ የጦር ወንጀሎች ትርፋማ እና በዚህም የወንጀሉ ተባባሪ የሆኑ ኩባንያዎችን ጠቅሰዋል።

በዚህ ሪፖርት ከተጠቀሱት መካከል ሎክሂድ ማርቲን የጦር መሳሪያዎችን በመሸጥ፤ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎቹ አልፋቤት፣ አይቢኤም፣ ማይክሮሶፍት እና አማዞን እስራኤል ፍልስጤማውያንን እንድትከታተል እና እንድታነጣጥርባቸው ቴክኖሎጂ አቅርበዋል ተብሏል።

በተጨማሪም ካተርፒላን፣ ሃዩንዳይ እና ቮልቮ የተሰኙት ኩባንያዎች ቤቶችን ለማፍረስ እና በቦምብ የወደሙ ቤቶችን ከመሬት ጋር ለማመሳሰል የሚያገለግሉ ተሽካርካሪዎችን ማቅረባቸው በሪፖርቱ ተካቷል።

በዚህ ዝርዝር የፋይናንስ ተቋማትም የገቡ ሲሆን ከነዚህም ቢኤንቢ ፓሪባስ እና ባርክሌይ በጦርነቱ ወቅት የእስራኤልን መንግሥት ቦንድ እንደገዙ ተጠቅሷል።

ቢቢሲ በዚህ ሪፖርት የተጠቀሱትን ኩባንያዎችን አስተያየታቸውን ጠይቋል።

ሎክሄድ ማርቲን ኩባንያ በሰጠው ምላሽ ከውጭ አገራት የሚደረጉ የመሳሪያ ሽያጮች መንግሥት ከመንግሥት ጋር የሚያደርጋቸው ግብይቶች ናቸው፤ እናም በዚህ ጉዳይ ላይ የአሜሪካ መንግሥት ምላሽ ቢሰጥበት የተሻለ እንደሆነ ገልጿል።

ቮልቮ በበኩሉ የአልባኔዝን ትችት እንደማይቀበለው ገልጾ ሪፖርቱ "በቂ ባልሆነ እና በከፊል በተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሰረተ ነው" ብሏል።

ሰብዓዊ መብቶችን በማክበር ቁርጠኛ እንደሆነ እና ክትትሉንም ለማጠናከር እንደሚሰራ አክሏል።

ነገር ግን ምርቶቹ ረጅም እድሜ ያላቸው እና ባለቤቶቻቸውም የሚቀያየሩ በመሆኑ "በሚያሳዝን ሁኔታ ምርቶቻችን በቆይታቸው ሁሉ እንዴት እና የት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ቁጥጥርም ሆነ ተጽእኖ ውስንነት አለ" ሲል አክሏል።

የተጠቀሱት ኩባንያዎች ንግዳቸው ትርፋማ እንደሆነ እስራኤል ጦርነቱን እንድትቀጥል እንደሚያግዝ ሪፖርቱ ገልጿል። አልባኔዝ ሁሉም ኩባንያዎች ከእስራኤል ጋር የሚያደርጉትን የንግድ ግንኙነት በአስቸኳይ ማቆም አለባቸው ብለዋል።