የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን ሠራተኛ ጓደኞቹ በተራቡ ፍልስጤማውያን ላይ ሲተኩሱ መመልከቱን ለቢቢሲ ተናገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጋዛ አወዛጋቢ የሆነው እና በእስራኤል እና አሜሪካ የሚደገፈው የሰብዓዊ ፋውንዴሽን የደህንነት ሠራተኛ የነበረ ግለሰብ ባልደረቦቹ ምንም ዓይነት ስጋት በማይፈጥሩ የተራቡ ፍልስጤማውያን ላይ በተደጋጋሚ ተኩስ ሲከፍቱ መመልከቱን ለቢቢሲ ተናገረ።
በአንድ ወቅት ሴቶች፣ ሕጻናትና አረጋውያን ከእርዳታ ማከፋፈያው በጣም በዝግታ እየሄዱ ሳለ በማማው ላይ የነበረ ጠባቂ የተኩስ እሩምታ እንደከፈተባቸው አስረድቷል።
የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን ለቀረበው ውንጀላ ምላሽ እንዲሰጥ ሲጠየቅ ሙሉ በሙሉ ውሸት ነው ሲል አስተባብሏል።
በ ፋውንዴሽኑ የእርዳታ ማከፋፈያ ቦታዎች አንድም ሰላማዊ ሰው ላይ አልተተኮሰበትም ብሏል።
በደቡባዊ እና መካከለኛው ጋዛ በርካታ ስፍራዎች እርዳታ ተቋርጦ ከቆየበኋላ የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን በግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ማከፋፈል ጀምሯል።
ይህ ሊሆን የቻለው እስራኤል ለ11 ሳምንታት አጠቃላይ በጋዛን የጣለችውን የሰብዓዊ እርዳታ ማዕቀብ ተከትሎ ምንም አይነት ምግብ ወደ ግዛቱ ሳይገባ በመቅረቱ ነበር።
የእርዳታ አቅርቦት ስርዓቱ እጅግ በጣም ብዙ ሰዎችን በውግያ ቀጠናዎች በሚገኙ ጥቂት የእርዳታ ማከፋፈያዎች እንዲሄዱ በማስገደዱ ትችቶች ይቀርቡበታል።
የሰብዓዊ ፋውንዴሽኑ እርዳታ ማከፋፈል ከጀመረ ጊዜ አንስቶ የእስራኤል ወታደሮች ከጣቢያዎቹ የእርዳታ እህል ለመውሰድ የተሰበሰቡ ከ400 በላይ ፍልስጤማውያንን ገድለዋል ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአገር ውስጥ ዶክተሮች ተናግረዋል።
እስራኤል አዲሱ የእርዳታ ማከፋፈያ ዘዴ ወደ ሐማስ የሚደርሰው እርዳታ አስቁሟል ብላለች።
የድርጅቱ የቀድሞ ሠራተኛ በአንድ የፋውንዴሽኑ የእርዳታ ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ ስለተከሰተው ሲናገር በርከት ብለው በተሰበሰቡ ፍልስጤማውያን ላይ ጠባቂዎች ተኩሰዋል ብሏል።
"ያ እየሆነ ባለበት፣ በቦታው ላይ ያለ ሌላ የደህንነት ባልደረባ፣ የጣብያው መውጫ በር ላይ በማነጣጠር ፣ ከ 15 እስከ 20 ጥይቶችን በተሰበሰበው ሕዝቡ ላይ ተኩሷል።"
"አንድ ፍልስጤማዊ ተመትቶ ወድያው ወደቀ። እና እዚያ ቆሞ የነበረው ሌላው ባልደረባ " 'ቲሽ፣ አንዱን ሳታገኘው አልቀረህም ' ካለ በኋላ ተሳሳቁ።"
ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው ይህ የደህንነት ባለሙያ የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን ኃላፊዎች ስለተፈጠረው ያቀረበውን ሪፖርት ይህ ፍልስጤማዊ "ተደናቀፎ" ወይም "ደክሞት ራሱን ስቶ ሊሆን ይችላል" በማለት ማጣጠላቸውን ተናግሯል።
ፋውንዴሽኑ እነዚህን ውንጀላዎች ያቀረበው ግለሰብ በሥነ ምግባር ጉድለት በመባረሩ "የተከፋ የቀድሞ ባልደረባ" ነው ብሏል። ግለሰቡ ግን ይህንን ያስተባብላል።
ሥራውን ከለቀቀ በኋላ ለሁለት ሳምንታት ደመወዝ ይከፈለው እንደነበር የሚያሳይ መረጃዎችን ለቢቢሲ አሳይቷል።
በአራቱም የ ፋውንዴሽኑ የእርዳታ ማከፋፈያዎች እንደሰራ የሚናገረው ይህ ግለሰብ፣ በስፍራው ጥቂት መመርያዎች ወይም ቁጥጥሮች መኖራቸውን በመግለጽ ተጠያቂነት አለመኖሩን ይናገራል።
የደህንነት ባለሙያው ምንም ግልጽ የሆነ መመርያ እንዳልተሰጣቸው በመግለጽ አንድ የቡድን መሪ "አደጋ ከተሰማችሁ ተኩሱ፤ ለመግደል ተኩሱ እና በኋላ ጥያቄዎችን ትጠይቃላችሁ" ማለቱን ይነጋራል።
በኩባንያው ውስጥ ያለው ባህል "ወደ ጋዛ እንሄዳለን፤ ስለዚህ ምንም ደንብ አይደለም፤ የምትፈልጉትን አድርጉ" የሚል ይመስላል።
"አንድ ፍልስጤማዊ ከቦታው እየሄደ ምንም ዓይነት አደጋ የማድረስ ዝንባሌ ሳያሳይ እና ምንም ይሁን ምን የማስጠንቀቂያ ጥይቶችን ከተኮስንበት ተሳስተናል፤ ቸልተኛ በመሆን ጥፋተኛ ነን" ይላል።
እያንዳንዱ የእርዳታ ማከፋፈያ በአካባቢው ያለውን እንቅስቃሴ የሚከታተል የደህንነት ካሜራ እንደተገጠመለት በመግለጽም የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን ማንም የተጎዳ ወይም የተተኮሰበት የለም ማለቱ "ፍፁም ያፈጠጠ ውሸት ነው" ብሏል።
ፋውንዴሽኑ ለቢቢሲ የደረሰው ተንቀሳቃሽ ምስል ውስጥ የሚሰማው የተኩስ ድምጽ ከእስራኤል ኃይሎች የተተኮሰ ነው ብሏል።
የቡድን መሪዎች ፍልስጤማውያኑን የ"ዞምቢዎች ስብስብ" ናቸው ሲሉ የሚጠሯቸው መሆኑን የተናገረው የቀድሞው የደህንነት ባልደረባ ይህም "እነዚህ ሰዎች ምንም ዋጋ እንደሌላቸው ለማሳየት" ነው ብሏል።
ግለሰቡ አክሎም ፍልስጤማውያን በፋውንዴሽኑ የእርዳታ ማከፋፈያዎች በተለያዩ መንገዶች ጉዳት እንደሚደርስባቸው ሲያብራራ በፍርስራሾች መመታት፣ በግፊያ መካከል ወደ ሽቦዎች በመገፍተር ጉዳት እንደሚደርስባቸው አብራርቷል።
በተደጋጋሚ ፍልስጤማውያን ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው መመልከቱን የሚናገረው የቀድሞው የድርጅቱ ባልደረባ፣ አንድ ግለሰብ ፊቱ ላይ ሙሉ በሙሉ ፔፐር ስፕሬይ ተደፍቶበት መመልከቱን፣ አንዲት ሴት በተተኳሽ ብረት ተመታ ማየቱን እና አለ አግባብ በተሰበሰበው ሕዝበ ላይ ሲተኮስ መታዘቡን ያስረዳል።
"ይህ የብረት ቁራጭ በቀጥታ ጭንቅላቷን መትቷት መሬት ላይ ወደቀች። ምንም እንቅስቃሴ አልነበራትም" ብሏል።
" መሞቷን አላውቅም። ራሷን ስታ እና ሙሉ በሙሉ ድንዛዜ ውስጥ እንደነበረች ግን አውቃለሁ።"
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ከ170 በላይ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን እንዲዘጋ ጠይቀዋል።
ኦክስፋም እና ሴቭ ዘ ችልድረንን ጨምሮ ድርጅቶቹ የእስራኤል ጦር እና ታጣቂ ቡድኖች እርዳታ በሚፈልጉ ፍልስጤማውያን ላይ "በተደጋጋሚ" ተኩስ ይከፍታሉ ብለዋል።
እስራኤል ወታደሮቿ ሆን ብለው እርዳታ የሚቀበሉ ሰዎች ላይ ተኩሰዋል መባሉን አስተባብላ፣ የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን ስርዓት የሐማስን ጣልቃ ገብነት በማለፍ በቀጥታ እርዳታ ለሚፈልጉ ሰዎች እያከፋፈለ ነው ብላለች።
የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን በአምስት ሳምንታት ውስጥ ከ52 ሚሊዮን በላይ ምግብ እንዳከደፋፈለ እና ሌሎች ድርጅቶችም "እርዳታቸው ሲዘረፍ አቅመ ቢስ ሆነው ተመልክተዋል" ብሏል።
መስከረም 26 2016 ዓ.ም. ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት አድርሶ 1,200 ሰዎች ከገደለ እና 251 ካገተ በኋላ ምላሽ ለመስጠት የእስራኤል ጦር በጋዛ ዘመቻ ከፍቷል።
በግዛቱ የሐማስ አስተዳደር የጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጋዛ ቢያንስ 57,130 ሰዎች ተገድለዋል።















