በአሜሪካ እና በእስራኤል የሚደገፈው የጋዛ የእርዳታ ቡድን መዘጋት አለበት ሲሉ 170 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከ170 በላይ የተራድዖ ድርጅቶች እና ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በእስራኤል እና በአሜሪካ በሚደገፈው እና በጋዛ የሚገኘው እና በጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽን (GHF) የሚተዳደረው አወዛጋቢው የእርዳታ ስርጭት እንዲዘጋ ጠየቁ።
በግንቦት ወር መገባደጃ ላይ እስራኤል ለ11 ሳምንታት የቆየውን እቀባ በከፊል ካቃለለችበት ጊዜ ወዲህ እርዳታ ፍለጋ ወደ ፋውንዴሽኑ የእርዳታ ስርጭት ማዕከላት ያቀኑ ከ500 በላይ ፍልስጤማውያን እርዳታ ሲፈልጉ ተገድለዋል ሲል የጋራ መግለጫ ገልጿል።
ኦክስፋም እና ሴቭ ዘ ችልድረንን ጨምሮ ድርጅቶቹ የእስራኤል ጦር እና የታጠቁ ኃይሎች እርዳታ በሚሹ ፍልስጤማውያን ላይ "በተደጋጋሚ" ተኩስ ይከፍታሉ ብለዋል።
እስራኤል ወታደሮቿ ሆን ብለው እርዳታ በሚሹ ፍልስጤማውያን መተኮሳቸውን ስትክድ የፋውንዴሽኑ የእርዳታ ስርጭት ስርዓት የሐማስን ጣልቃ ገብነት በማለፍ በቀጥታ እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ጋር ይደርሳል ብላለች።
የጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽን በአምስት ሳምንታት ውስጥ ከ52 ሚሊዮን በላይ ምግብ እንዳቀረበ እና ሌሎች ድርጅቶች "እርዳታቸው እየተዘረፈ በአቅመ ቢስነት ቆመው ይመለከታሉ" ብሏል።
ማክሰኞ ዕለት በአንዳንድ የዓለም ታላላቅ በጎ አድራጎት ድርጅቶች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በጋራ የወጣው መግለጫ የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን ሁለት ሚሊዮን ሰዎችን በየቀኑ የተኩስ እሩምታ ወደሚገጥማቸው የተጨናነቁ እና በወታደራዊ ዞኖች ወደሚገኙ ማዕከላት እንዲሄዱ ማስገደድን ጨምሮ ሁሉንም የሰብዓዊ ሥራዎችን ደንቦች እየጣሰ ነው ብሏል።
ፋውንዴሽኑ በጋዛ ውስጥ እርዳታ ማሰራጨት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ የእስራኤል ወታደሮች በየቀኑ በሚባል ደረጃ በእነዚህ ጣቢያዎች እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎችን መግደላቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች ከሕክምና ባለሙያዎች፣ ከዓይን እማኞች እና ከግዛቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሲወጡ ነበር።
ማክሰኞ ሚኒስቴሩ ባወጣው ሪፖርት ከግንቦት ወር አጋማሽ ጀምሮ እርዳታ ሲፈልጉ የነበሩ 583 የተገደሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 408 የሚሆኑት የተገደሉት በፋውንዴሽኑ ማከፋፈያ ማዕከላት አቅራቢያ ነው።
የፋውንዴሽኑ ስርዓት በመጨረሻው ጊዜያዊ የእስራኤል ሐማስ የተኩስ አቁም ወቅት ይሰሩ የነበሩትን 400 የእርዳታ ማከፋፈያ ጣቢያዎች በእስራኤል ወታደራዊ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ እና በአሜሪካ የግል ደህንነት ተቋራጮች በሚተዳደሩ አራት የማከፋፈያ ጣቢያዎች ብቻ የተካቸው ሲሆን ሦስት በደቡብ ምዕራብ ጋዛ ቀሪው አንድ ጣቢያ ደግሞ በማዕከላዊ ጋዛ የሚገኝ ነው።
"ዛሬ በጋዛ ውስጥ የሚገኙ ፍልስጤማውያን የማይቻል ምርጫ ይገጥማቸዋል፡ በረሃብ ወይም ቤተሰቦቻቸውን ለመመገብ በሚያደርጉት ጥረት በጥይት መመታት" ሲሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጋራ መግለጫቸው አስጠንቅቀዋል።
"ወላጅ አልባ ሕጻናት እና ተንከባካቢዎች ከሟቾች መካከል ሲሆኑ ከእነዚህ ጣቢያዎች ውስጥ ጥቃት ከደረሰባቸው ንጹኃን ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሕጻናት ናቸው"
ለትችቱ ምላሽ የሰጡት የፋውንዴሽኑ ቃል አቀባይ "በአምስት ሳምንታት ውስጥ ከ 52 ሚሊዮን በላይ ምግቦችን አቅርበናል ። በወሬ ብቻ እና፤ አርዕስተ ዜና ሳይሆን ሳይሆን በየቀኑ የፍልስጤም ቤተሰቦችን የሚደርስ ምግብ ነው" ብለዋል።
"ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌሎች ድርጅቶች እርዳታቸዉ ሲዘረፍ አቅመ ቢስ ሆነው ቆመው ተመልክተዋል። በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲያከፋፍሉ ለመርዳት ጠይቀናቸዋል፣ እምቢ ብለዋል።"
አክለውም "የሰብዓዊ ማኅበረሰብ ወደ ዋና ተልዕኮው መመለስ አለበት፤ ሰዎችን መመገብ ላረጁ ያፈጁ ስርዓቶች ጥብቅና አለመቆም እና በለውጥ መረበሽን ማስወገድ አለበት"።
አርብ ዕለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽን የእርዳታ ስርጭት ስርዓትን "በተፈጥሮ ደህንነቱ ያልተጠበቀ" እና "ሰዎችን እየገደለ ያለ ነው" ሲሉ ጠርተውታል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከመጀመርያ ጀምሮ እቅዱ እርዳታን "ወታደራዊ" ያደርጋል በሚል ተቃውሞት ነበር፣ በሥራ ላይ ያለውን በተባበሩት መንግሥታት የሚመራው የማከፋፈያ አውታር በማቋረጥ ፍልስጤማውያንን በአደገኛ ክልል ውስጥ ምግብ ለማግኘት ረጅም ጉዞ እንዲያደርጉ ያስገድዳቸዋል።
የእስራኤል ጦር ፍልስጤማውያን ወደ ፋውንዴሽኑ የዕርዳታ ማከፋፈያ ማዕከላት ሲቃረቡ "ተጎዱ" የሚለውን ዘገባ እየመረመረ መሆኑን ገልጿል።
የእስራኤል ጋዜጣ ሃሬትዝ አርብ ዕለት ባወጣው ዘገባ መሰረት፣ ስማቸው ያልተገለጸ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት (አይዲኤፍ) ወታደሮች፣ በእርዳታ ማከፋፈያ ቦታዎች አካባቢ ያልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎችን ለማባረር ወይም ለመበተን እንዲተኮሱ ታዝዘዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሪፖርቱን አጥብቀው አልተቀበሉትም፤ ውንጀላውን "ተንኮል አዘል ውሸት" ሲሉ ጠርተውታል።
የእስራኤል ጦር ሰብዓዊ ርዳታ ለመሰብሰብ በሚጠባበቁ ፍልስጤማውያን ላይ ሆን ተብሎ የተኩስ ውንጀላውን አስተባብሏል።
የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን ለሃሬትዝ ዘገባ በሰጠው ምላሽ "በየትኛም የስርጭት ጣቢያችን ላይ ወይም በአቅራቢያው ምንም ዓይነት አደጋ ወይም ሞት የለም" ብሏል።
ከ170 በላይ የሆኑት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የፋውንዴሽኑ ስርዓት ለፍልስጤማውያን "ሰብዓዊ ምላሽ አይደለም" ብለዋል።
"በከፍተኛ ረሃብ እና ረሃብ መሰል ሁኔታዎች ውስጥ፣ ብዙ ቤተሰቦች አሁን ለምግብ ራሽን ተሽቀዳድሞ ለመውስድ አቅም እንዳነሳቸው ይነግሩናል" ብለዋል።















