በእርዳታ ማከፋፈያው አቅራቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን የተገደሉበት ድርጅት "ሥራዬን በአግባቡ እየሰራሁ" ነው አለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአሜሪካ እና በእስራኤል የሚደገፈው አወዛጋቢው የእርዳታ ድርጅት ኃላፊ በተደጋጋሚ እርዳታ በመጠባበቅ ላይ በሚገኙ ፍልስጤማውያን ላይ በእስራኤል ጥቃት ግድያ እና ጉዳት ከተፈፀመ በኋላ "ሥራቸውን በአግባቡ እየሰሩ" እንደሆነ ተናገሩ።
ጋዛ ሂውማኒቴሪያል ፋውንዴሽን (ጂኤችኤፍ) የተባለው ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ጆኒ ሙር ለቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ኒውስአዎር ሲናገሩ በእርዳታ ማከፋፈያ ቦታዎች አቅራቢያ የተፈፀመውን ግድያ ባይክዱም፤ ሁሉም ክስተቶች ያጋጠሙት ለእርዳታ ጣቢያው ቅርበት ባላቸው ሥፍራዎች ነው መባሉ ሀሰት ነው ብለዋል።
ኃላፊው የተባበሩት መንግሥታትን እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶችንም "ማረጋገጥ ያልቻሉትን መረጃ በማሰራጨት" ከሰዋል።
የጂኤችኤፍ የእርዳታ ሥርዓት በተባበሩት መንግሥትታት ተቋማት የተወገዘ ሲሆን አርብ ዕለት የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የእርዳታ ሥርዓቱን "ደኅንነቱ ያልተጠበቀ" ብለውታል።
" ምግብ የሚፈልጉ ሰላማዊ ሰዎችን ወደ ጦር ቀጠናዎች የሚወስድ ማንኛውም ሥራ በባህርይው ደኅንነቱ የተጠበቀ አይደለም። ምግብ ፍለጋ የሞት ፍርድ መሆን አይገባም" ብለዋል ዋና ጸሐፊው።
በጋዛ በሐማስ የሚተዳደረው የጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው ጂኤችኤፍ እርዳታ ማከፋፈል ከጀመረ አንስቶ እርዳታ ለመቀበል ሲሄዱ የነበሩ ከ500 በላይ ፍልስጤማውያን የተገደሉ ሲሆን 4 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የእርዳታ አከፋፋዩ ግንቦት ወር ላይ ሥራ ከጀመረ በኋላ በቀናት ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት በተፈፀሙ ጥቃቶች በርካታ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የተባበሩት መንግሥታት እና የእርዳታ ሰጭ ቡድኖች በየቀኑ በሚባል ደረጃ በእስራኤል የጦር ቀጠናዎች ውስጥ በሚገኘው የጂኤችኤፍ የእርዳታ ማከፋፈያ ጣቢያ ፍልስጤማውያን መገደላቸው እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
የዓይን እማኞች እና የጤና ባለሙያዎችም በተለያዩ ጊዜያት የእስራኤል ኃይሎች በእርዳታ ጣቢያው አቅራቢያ በተሰባሰቡ ፍልስጤማውያን ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ተናግረዋል።
ሃርትዝ የተባለው የእስራኤል ጋዜጣ አርብ ዕለት ባወጣው አንድ ጽሑፍ ስማቸው ያልተገለጸ የእስራኤል መከላከያ ኃይል አባላት በእርዳታ ማከፋፈያ ጣቢያው አቅራቢያ የተሰባሰቡ ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎችን ለመበተን አሊያም ለማባረር ተኩስ እንዲከፍቱ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው መግለጻቸውን አስነብቧል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ግን የቀረበውን ክስ " ተንኮል ያዘለ ውሸት" ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ለቢቢሲ በላከው መግለጫም " ወደ እርዳታ ማከፋፋያ ጣቢያው በሚመጡ ሰዎች ላይ ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ እንዲተኩሱ ለአባላቶቼ ትዕዛዝ አልሰጠሁም" ብሏል።
ጨምሮም በእርዳታ ማከፋፈያ ጣቢያዎች እየሰጠ ያለውን ምላሽ ለማሻሻል እየሰራ እንደነበር ገልጾ፤ በቅርቡም አዲስ አጥር እና ምልክቶችን መጨመሩን እንዲሁም ወደ ጣቢያው የሚወስዱ አዳዲስ መንገዶችንም እንደከፈተ ጠቅሷል።
የእርዳታ ድርጅቱ- ጂኤችኤፍ ኃላፊ በበኩላቸው "የደረሰው ጉዳት ሙሉ በሙሉ በእስራኤል መከላከያ ኃይል የተፈፀመ ነው የሚለው እስከምናውቀው ድረስ ከእውነት የራቀ ነው" ብለዋል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ባለፈው ወር በሰጣቸው መግለጫዎቹ " ተጠርጣሪዎች" በማለት የገለጻቸው ወይም ስጋት ፈጥረዋል ያላቸው ግለሰቦች ላይ "የማስጠንቀቂያ ተኩስ" መተኮሱን ደጋግሞ ገልጿል።
" የሆነ ነገር ተከስቶ ከሆነ የመከሰት እድሉን የምንቀንስበት መንገድ ካለ በሚል በትክክል የሆነው ምንድን ነው የሚለውን ለመረዳት ብዙ ጊዜ እናጠፋለን" ያሉት ሙር በአብዛኞቹ ሁኔታዎች ላይ ምን እንደተከሰተ መለየት እንዳልቻሉ ገልጸዋል።
" ወደ ጂኤችኤፍ የእርዳታ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሚሄዱ ሰዎች ይገደላሉ የሚለው ሀሰተኛ መረጃ እንደሆነ ሰዎች ሊረዱ ይገባል። እነዚያ ክስተቶች ከእርዳታ ጣቢያዎቹ አቅራቢያ የተከሰቱ ለመሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ የለም" ሲሉም አክለዋል።
እስራኤል ቢቢሲን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የዜና ድርጅቶች ጋዜጠኞቻቸውን ወደ ጋዛ እንዲልኩ አትፈቅድም። ይህም በግዛቱ ውስጥ እየሆነ ያለውን ነገር ከሥፍራው ለማረጋገጥ የምንችልበትን አቅም ውስን አድርጎታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሙር ጂኤችኤፍ እርዳታ ማከፋፈል ሳይጀምር በፊት የተባበሩት መንግሥታት እርዳታ ጫኑ ተሽከርካሪዎች መታገታቸውን ገልጸው ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት ግን የእርዳታ ተሽከርካሪዎቹ መጠለፋቸውን የሚያሳይ ምንም መረጃ የለም ብሏል። ሙር ይህ በተነገራቸው ጊዜም " የተባበሩት መንግሥታት ታማኝ አይደለም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
እስራኤል ወደ ጋዛ እርዳታ እንዳይገባ ለ11 ሳምንታት የጣለችውን እገዳ ባለፈው ወር በከፊል ብታነሳም አሁንም ወደ ጋዛ የሚገባው የእርዳታ መጠን በቂ አይደለም።
ግዛቲቱ በረሃብ አፋፍ ላይ እንደምትገኝም ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።
ጂኤችኤፍ በጋዛ እርዳታ ማከፋፈል ከጀመረ አንስቶ 50 ሚሊዮን ምግቦች አከፋፍላለሁ ብሎ ተስፋ ያደረገ ሲሆን ይህም ለአንድ ሰው በአንድ ቀን ከአንድ ምግብ ያነሰ እንደማለት ነው።
ምግብ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች እርዳታው እየደረሰ እንደሆነ የተጠየቁት ሙር፣ በቂ አልመሆኑን ገልጸው ፤ ነገር ግን ከአንድ ወር በፊት ከነበረው የተሻለ እንደሆነ አስረድተዋል።
ጨምረውም ድርጅቱ ድጋፉን እንደሚጨምር እና እንደ የተባበሩት መንግሥታት ካሉ ድርጅቶች ጋር ለመስራት ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
" ተልዕኮው ግልጽ ነው፤ የምንፈልገው የጋዛ ነዋሪዎችን መመገብ ነው" ብለዋል።
ሐሙስ ዕለት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለጂኤችኤፍ 30 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል። ለእርዳታ ቡድኑ በቀጥታ ድጋፍ ማድረጉ ሲገለጽ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የእስራኤል ጦር በጋዛ ላይ ወታደራዊ ዘመቻ የጀመረው ከሁለት ዓመት በፊት መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ሐማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመፈፀም 1 ሺህ 200 ሰዎችን ከገደለ እና 251 ሰዎችን አግቶ ከወሰደ በኋላ ነበር።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጋዛ ከ56 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።















