በጋዛ ቢያንስ 12 እርዳታ የሚጠባበቁ ሰዎች መገደላቸውን የሕክምና ባለሙያዎች ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቢያንስ 12 ፍልስጤማውያን በማዕከላዊ ጋዛ እርዳታ በመጠባበቅ ላይ እያሉ በእስራኤል ወታደሮች መገደላቸውን የነፍስ አድን ሠራተኞች እና የሕክምና ባለሙያዎች ገለጹ።
ግለሰቦቹ ባለፈው ሐሙስ በዩናይትድ ስቴትስ እና በእስራኤል በሚደገፈው የጋዛ ሰብአዊ ፋውንዴሽን (ጂኤችኤፍ) በሚተዳደረው የእርዳታ ማከፋፈያ አጠገብ በተከፈተ ተኩስ መሞታቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል።
የሰብኣዊ ፋውንዴሽኑ ግን ከጣቢያው አጠገብ ምንም ዓይነት ጥቃት አልተከሰተም ሲል አስተባብሏል።
የእስራኤል ጦር ለሮይተርስ እንደተናገረው "ተጠርጣሪዎች" በኔትዛሪም አካባቢ ወደሚገኘው ኃይሎች ለመቅረብ በመሞከራቸው ወታደሮች የማስጠንቀቂያ ተኩስ መተኮሳቸውን አስታውቋል።ሆኖም ጉዳት ስለመድረሱ መረጃው እንደሌለው ተናግሯል።
ክስተቱ በጋዛ በሚገኙ የእርዳታ ጣቢያዎች አቅራቢያ በየቀኑ ከሚደርሱ ጥቃቶች መካከል የቅርብ ጊዜው ነው።
ከግንቦት ወር መጨረሻ ጀምሮ በፋውንዴሽኑ የእርዳታ ማከፋፈያዎች አቅራብያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።
ከቅርብ ቀናት ወዲህ በጋዛ የሚደርሱ ጉዳቶች እና ሞቶች እስራኤል በሐማስ ዒላማዎች ላይ ከምታደርገው ጥቃት ይልቅ በእርዳታ አሰጣጥ ዙሪያ የሚከሰቱ ናቸው።
የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ሐሙስ ዕለት እንዳስታወቀው ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ እርዳታ ለመቀበል የሄዱ 12 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።
በሃማስ የሚተዳደረው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደገለጸው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በየቀኑ እርዳታ ለማግኘት በሚሰበሰቡበት በኔትዛሪም ኮሪደር አቅራቢያ ግለሰቦቹ ከእስራኤል ወታደሮች በተተኮሰ ጥይት ተገድለዋል።
የሲቪል መከላከያ ባለስልጣን መሀመድ አል ሙጋይርም በጥቃቱ 15 ሰዎች ሲገደሉ 60 ቆስለዋል ብለዋል።
እስራኤል ቢቢሲን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የዜና ማሰራጫዎችን ወደ ጋዛ ገብተው እንዲዘግቡ ስለማትፈቅድ የደረሰውን ጉዳት ለማጣራት አስቸጋሪ አድርጎታል።
በጋዛ ሰብዓዊ እርዳታ ፋውንዴሽን በሚደገፈው የእርዳታ ማከፋፈያ ቦታ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአንድ ጀምበር ተሰብስበው እንደነበር እና የእስራኤል ወታደሮች ተኩስ እንደከፈቱ የዓይን እማኞች ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።
"የሕዝቡ ብዛት ሰዎች ከተኩሱ ማምለጥ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል" ያሉት ዳይሬክተሩ "እኛ እንኳን ልንረዳቸው ራሳችንም ማምለጥ አልቻልንም" ብለዋል።
ሆኖም የጋዛ ሰብኣዊ እርዳታ ፋውንዴሽን ለቢቢሲ "በጣቢያችን አቅራቢያ ምንም አይነት ጥቃቶች አልነበሩም" ብሏል።
"ይህ አሁንም በጋዛ የጤና ሚኒስትር የሚነገር የውሸት እና አሳሳች ዘገባ ሌላ ምሳሌ ነው።"
ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊትን ጠይቋል።
ሮይተርስ እንደዘገበው የእስራኤል ወታደራዊ ሰዎች በአስጊ ሁኔታ እየቀረቧቸው ነበር ብሏል።
ሐማስ ረቡዕ እለት በቴሌግራም ገፁ ላይ በሰጠው መግለጫ በጋዛ ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የሰብዓዊ ኤጀንሲዎች ብቻ እርዳታ እንዲያከፋፍሉ ጥሪ አቅርቧል።
የተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎች የእርዳታ ቡድኖች በሰብዓዊ ፋውንዴሽኑ ከሚመራው አዲሱ የእርዳታ አሰጣጥ ስርዓት ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ አይደሉም።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስርዓቱ የገለልተኝነት፣ ያለማዳላት እና የነጻነት ሰብዓዊ መርሆችን ይቃረናል ብሏል።
የእስራኤል መከላከያ ሃማስ መስከረም 26/ 2016 ዓ.ም. ድንገታዊ ጥቃት ፈጽሞ 1200 ሰዎችን ከገደለ እና 251 ሰዎችን አግቶ ከወሰደ በኋላ በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻ ጀምሯል።
ከዚያን ግዜ ጀምሮ ቢያንስ 55,637 ሰዎች መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስትር መረጃ ያሳያል።















