በእስራኤል ጥቃት ዘጠኝ ልጆቹ የተገደሉበት የጋዛ ሀኪም በደረሰበት ጉዳት ህይወቱ አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል ግንቦት 25 ባደረሰችው ጥቃት ልጆቹ የተገደሉበት ፍልስጤማዊ ዶክተር በዚያው ጥቃት በደረሰበት ጉዳት ህይወቱ ማለፉን የጤና ኃላፊዎች ተናገሩ።
የ40 ዓመቱ ሀኪም ዶ/ር ሃሚድ አል ናጃር በኻን ዩኒስ የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ጥቃት የደረሰበት ባለቤቱን ሁለቱም ጥንዶች ወደሚሰሩበት ናስር ሆስፒታል አድርሶ ከተመለሰ በኋላ ነበር። ጥንዶቹ ካሏቸው አስር ልጆች ውስጥ ዘጠኙ የተገደሉ ሲሆን በህይወት የተረፈው አንዱ ልጅም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል።
ሃሚድ ሆስፒታል ውስጥ የአንጎል እና የውጣዊ አካላት ጉዳቶች ህክምና ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም ቅዳሜ ዕለት ህይወቱ አልፏል።
ባለቤቱ አላ እና ሆስፒታል ውስጥ ያለው የ11 ዓመት ልጃቸው አደም 12 አባላት ከነበሩት ቤተሰብ የተረፉ ብቸኛ ሰዎች ሆነዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ክስተቱን እየተመለከተ እንደሚገኝ በወቅቱ ገልጾ ነበር።
ሃሚድ፤ ከባለቤቱ ጋር የመሰረቱት እና በኻን ዩኒስ የሚገኘው የግል የህክምና ማዕከል ኃላፊ ነበር።
ወንድሙ ዶ/ር አሊ አል ናጀር፤ ድሃ ታማሚዎችን በነጻ የሚያክም፤ ልጆቹን የሚወድ አባት ሲል ይገልጸዋል።
ያህያ፣ ራካን፣ ራስላን፣ ገብራን፣ ኢቭ፣ ሪቫል፣ ሳይደን፣ ሉክማን እና ሲድራ የተባሉት ዘጠኝ ልጆቻቸው በጥቃቱ ተገድለዋል።
የመጀመሪያ ልጃቸው 12 ዓመት፤ የመጨረሻ ልጃቸው ደግሞ የስድስር ወራት እድሜ እንደነበራቸው የኃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ሃሚድ በጥቃቱ አንጎሉ፣ ሳንባዎቹ፣ ቀኝ እጁ እና ኩላሊቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት በናስር ሆስፒታል የምትሰራው ቡልጋሪያዊት ሀኪም ዶ/ር ሚሌና አንጀሎቫ ቺ ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ ተናግራ ነበር።
በሆስፒታሉ የቀዶ ጥገና ሀኪም የሆኑት እና የተረፈው ልጅ አደም ያከሙት ብሪታኒያዊው ግሬይም ግሩም፤ የህጻናት ሀኪሟ ሆና ለዓመታት ልጆችን ስትንከባከብ የነበረችው እናት አላ በአንድ ጥቃት ሁሉንም በሚባል ሁኔታ ልጆቿን ማጣቷ "ሊቋቋሙ የማይችሉት ጭካኔ" ነው በማለት ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአደም "ግራ እጅ እንዲሁ ተንጠልጥሎ፣ ፊቱም በፍንጥርጣሪ በደረሰ ጉዳት ተሸፍኖ እና በርካታ ጉልህ ቁስሎችም እንደነበሩት" ተናግረዋል።
"ሁለቱም ወላጆች ሀኪሞች በመሆናቸው በጋዛ ውስጥ ልዩ ጥቅም ካላቸው ቡድኖች ውስጥ የሚካተቱ ይመስላል ነገር ግን አንስተን የቀዶ ህክምና ጠረጴዛ ላይ ስናስቀምጠው እድሜው ከ11 ዓመት እጅጉን እንደሚያንስ ነበር የተሰማን" ብለዋል።
የጣልያን መንግስት ሐሙስ ዕለት አደምን ለማከም ጥያቄ አቅርቧል። የሃገሪቱ መንግሥት ይህንን ያደረገው የልጁ አጎት ዶ/ር አሊ አል ናጃር ናስር ሆስፒታል አደምን ለማከም በበቂ አቅርቦት እንደሌለው ለላ ሪፐብሊካ ጋዜጣ በመናገር ያቀረበውን ተማጽኖ ተከትሎ ነው።
"አፋጣኝ ከጋዛ ሰርጥ ውጪ ወደሚገኝ ትክክለኛ ሆስፒታል መወሰድ አለበት። የጣልያን መንግሥት አንድ ነገር እንዲያደርግ እለምናለሁ፤ ውሰዱት፣ ጣልያናውን አድኑት" ብሎ ነበር።
የጣልያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ "ጣልያን መንግሥት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበትን ልጅ ወደ ጣልያን ለማዘዋወር ፍቃደኝነቱን ይገልጻል" ብሏል። የተግባራዊነት እቅድ ጥናት እያካሄደ መሆኑንም አክሏል።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በወቅቱ ጥቃቱን በተመለከተ ለወጡ ዘገባዎች በሰጠው ምላሽ "ለነዋሪዎች ለራሳቸው ጥበቃ ሲባል አስቀድመው ለቅቀው እንዲወጡ በተደረገበት አደገኛው የውጊያ ቀጣና ኻን ዩኒስ፤ የእስራኤል ወታደሮች የሚገኙበት አካባቢ አጎራባች በሆነ ህንጻ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ እና በሠራዊቱ የተለዩ በርካታ ተጠርጣሪዎች አየር ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።
ተሳትፎ ያልነበራቸው ግለሰቦች ላይ ደርሷል የሚባለው ጥቃት እየተመረመረ ነው" ብሎ ነበር።















