በእስራኤል ጥቃት ዘጠኝ ልጆቹ የተገደሉበት አባት ህይወቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተነገረ

የሃሚድ አል ናጃር ሆስፒታል ውስጥ ዘመዶቹ ሲጎበኙት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሃሚድ አል ናጃር ሆስፒታል ውስጥ ዘመዶቹ ሲጎበኙት

በጋዛ ሰርጥ ፍልስጤማዊ ዶክተር ባለቤት የሆነው እና እስራኤል አርብ ዕለት በፈጸመችው ጥቃት ልጆቹ የተደሉበት አባት ህይወቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ህክምና የሚያደርግለት ሆስፒታል ገለጸ።

ኻን ዩኒስ በሚገኘው ናስር ሆስፒታል የምትሰራው ቡልጋሪያዊት ሀኪም ዶ/ር ሚሌና አንጀሎቫ ቺ ለቢቢሲ እንደተናገረችው የሃሚድ አል ናጃር "ህይወት አደጋ ውስጥ" ነው።

የእስራኤል ጥቃት ጥንዶቹ ካሏቸው አስር ልጆች ውስጥ ዘጠኙን ገድሎ፤ አባት እና የ11 ዓመት ልጁን ለጉዳት ዳርጓል። የእስራኤል ሠራዊት ክስተቱ እየተጣራ መሆኑን አስታውቋል።

ቀይ መስቀል በበኩሉ ኻን ዩኒስ በሚገኘው ቤታቸው የነበሩ ሁለት ሰራተኞቹ ቅዳሜ ዕለት በደረሰ ጥቃት መገደላቸውን ገልጿል።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፤ የመሳሪያ ማምከን መኮንን ኢብራሂም ኢድ እና በራፋ የሚገኘው ሬድ ክሮስ ፊልድ ሆስፒታል ጥበቃ አህመድ አቡ ሂላል መገደል "በጋዛ ያለውን ሊታለፍ የማይችል የንጹሃን ሞት እንደሚያመለክት" በመግለጽ በድጋሚ የተኩስ አቁም ጥሪ አቅርቧል።

በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር፤ የእስራኤል የአየር ጥቃት የነፍስ አድን አገልግሎት ኃላፊ እና ጋዜጠኛን ጨምሮ እስከ ንጋት ድረስ 23 ሰዎችን መግደሉን እሁድ ዕለት ገልጿል።

የጋዛ የህዝብ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ከፍተኛ ኃላፊ አሽራፍ አቡ ናር እና ባለቤቱ የተገደሉት በማዕከላዊ ጋዛ በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ እንደሆነ ሚኒስቴሩ ተናግሯል።

ጋዜጠኛ ሀሰን መጂድ አቡ ዋርዳ እና በርካታ የቤተሰብ አባላቱ ደግሞ በሰሜናዊ ጋዛ ጃባሊያ በሚገኘው ቤታቸው ላይ በተፈጸመ ጥቃት መገደላቸውን አክሏል።

እንደ ባለቤቱ ሁሉ ሀኪም የሆነው ሃሚድ አል ናጃር በቅዳሜ ዕለቱ ጥቃት አዕምሮው፣ ሳንባ፣ ቀኝ እጅ እና ኩላሊቱ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ዶ/ር አንጀሎቫ ቺ ተናግራለች። በሆስፒታሉ "የምንችለውን ሁሉ እያደረግንለት ነው" ብላለች።

በህይወት የተረፈው የጥንዶቹ ልጅ አደምም ጉዳት ደርሶበታል። ዶ/ር አንጀሎቫ ቺ፤ "በደህና ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ" ከባልደረቦቿ መስማቷን ገልጻለች።

ባለቤቱ ዶ/ር አላ አል ናጃር የእስራኤል ጥቃት ሲፈጸም በናስር ሆስፒታል ስራ ላይ ነበረች። የጤና ሚኒስስቴር ዳይሬክተር ዶ/ር ሙኒር አልቦርሽ ያጋሩት እና ቢቢሲ ያረጋገጠው አንድ ቪድዮ የተቃጠሉ ህጻናት አስከሬን ከፍርስራሽ ውስጥ ሲነሳ ያሳያል።

ያህያ፣ ራካን፣ ራስላን፣ ገብራን፣ ኢቭ፣ ሪቫል፣ ሳይደን፣ ሉክማን እና ሲድራ የተባሉት ዘጠኝ ልጆች ከጥቂት ወራት እስከ 12 ዓመት እድሜ ያላቸው ናቸው።

ዶ/ር አንጀሎቫ ቺ፤ የስራ ባልደረባዋ "የማይነገር ስቃይ" እንደደረሰባት ተናግራለች።

በአሁኑ ሰዓት አላ "ቅድሚያ የምትሰጠው ለቤተሰቧ" መሆኑን የገለጸችው ዶ/ር አንጀሎቫ ቺ፤ "ይህ የደረሰባት እርሷ ብቻ አይደለችም፤ ብዙ ቤተሰቦቹ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ናቸው" ብላለች።

"ሁሉም ሰው በጣም ደንግጧል፤ ምክንያቱም ይህ [ድርጊት] ለ18 ወራት ቀጥሏል፤ በማያቋርጥ የሞት ስጋት፣ የማያቋርጥ መዛወር እና መፈናቀል የታጀበም ነው" ስትል በብዙ ሰዎች ላይ የተፈጠረውን ስጋት ገልጻለች።

በህይወት የተረፈው ብቸኛ ልጅ አደም (ግራ፤ በእስራኤል ጥቃት ከተገደሉት እህቶቹ ሲድራ እና ሪቫል (ቀኝ) ጋር

የፎቶው ባለመብት, al-Najjar family

የምስሉ መግለጫ, በህይወት የተረፈው ብቸኛ ልጅ አደም (ግራ፤ በእስራኤል ጥቃት ከተገደሉት እህቶቹ ሲድራ እና ሪቫል (ቀኝ) ጋር
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት፤ "በኻን ዩኒስ የእስራኤል ወታደሮች የሚገኙበት አካባቢ አጎራባች በሆነ ህንጻ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ በርካታ ተጠርጣሪዎች አየር ጥቃት እንደተፈጸመባቸው" ቅዳሜ ዕለት አስታውቋል።

ኻን ዩኒስ "አደገኛ የጦርነት ቀጣና" መሆኑን የገለጸው ሠራዊቱ፤ ሰዎች ለራሳቸው ደህንነት ሲባል አካባቢውንእንዲለቅቁ እንደተናገረ ገልጿል።

መከላከያ ሠራዊቱ፤ ኻን ዩኒስ አካባቢ የሚገኙ ሰዎች "ከዚህ ቀደም ያልታየ ጥቃት" ከመፈጸሙ በፊት ለቅቀው እንዲወጡ ሰኞ ዕለት አስጠንቅቆ ነበር። ይህ በቅርብ ወራት ከተላለፉ የመፈናቀል ትዕዛዞች ትልቁ ነው።

የተወሰኑ ፍልስጤማውያን "መሄጃ ቦታ ባለመኖሩ" እንዳልለቀቁ ለቢቢሲ ተናግረዋል። እንደ የተባበሩት መንግስታት ከሆነ የግዛቱ 81 በመቶ በእስራኤል የልቀቁ ትዕዛዝ ተላልፎበታል ወይም "መንቀሳቀስ የተከለከለበት" ወታደራዊ ቀጣና ሆኗል።

እስራኤል ሌላኛውን ዙር የተቀናጀ የአየር እና የምድር ጥቃት ከጀመረችበት መጋቢትጀምሮ 3,785 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።

በጋዛ ታግታ የነበረች አንዲት እስራኤላዊት ሴት የአል ናጃርን ዘጠኝ ልጆች ከተገደሉ በኋላ በቴል አቪቭ ሰልፍ ላይ ባደረገችው ንግግር፤ እገታ ላይ እያለ እጅጉን ያስፈራት የነበረው የአየር ጥቃት እንደሆነ አስታውሳለች።

በመስከረም 26ቱ የሃማስ ጥቃት ከታገቱ አምስት ሴት የስለላ ወታደሮች አንዷ የሆነችው ናማ ሌቪ፤ የአየር ጥቃት በጀመረባቸው ቁጥር እንደምትሞት እርግጠኛ እንደነበረች ተናግራለች። አሁንም በጋዛ ተይዘው ላሉት ታጋቾች ህይወት እንደምትሰጋም አክላለች።

እስራኤል፤ በደረሳት የረሃብ ስጋት ማስጠንቀቂያዎች እና ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ቁጣ ምክንያት የተወሰነ እርዳታ ወደ ግዛቱ እንዲገባ ከመፍቀዷ በፊት ከየካቲት መጨረሻ አንስቶ ለ11 ሳምንታት ጋዛን ከበባ ውስጥ አስገብታ።

በግዛቱ ውስጥ የመንግስት ስራን የሚያስተባብረው የእስራኤል ሠራዊት ክፍል፤ ከሰኞ ጀምሮ እርዳታ የጫኑ 388 ተሽከርካሪዎች መግባታቸውን ቅዳሜ ዕለት ተናግሯል። የተባበሩት መንግስታት በየቀኑ ከ500 እስከ 600 መኪና እርዳታ እንደሚያስፈልግ አስታውቋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለቢቢሲ እንደተናገረው፤ ከቅዳሜ ጀምሮ ምንም ተሽከርካሪ ወደ ጋዛ አልገባም። መጋገሪያዎች ባጋጠማቸው "ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት" ምክንያት የዳቦ ስርጭት መቋረጡንም ገልጿል።

ቃል አቀባዩ፤ "አሁን በተጣለው ሁኔታ ውስጥ ስራ ማከናወን አይቻልም" ብለዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር ሲንዲ ማክኔን፤ "ጋዛ ውስጥ ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ያጋጠማቸው 500 ሺህ ሰዎች ስለሚገኙ እና ካሉበት ሁኔታ ለማውጣት እገዛ የማይደረግ ከሆነ ረሃብ አፋፍ ላይ ሊሆኑ ስለሚችሉ"፤ ተጨማሪ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ መግባት እንደለባቸው በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

የእስራኤል በከፊል እገዳ ከተነሳ ጀምሮ የእርዳታ ተሽከርካሪዎች በንጹሃን ሰዎች እየተዘረፉ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፤ ይህንን የሚፈጽሙትን ሰዎች "እጅግ እጅግ እጅግ ተስፋ የቆረጡ ድሃ ነፍሶች" በማለት ገልጸዋቸዋል።

ዶ/ር አንጀሎቫ ቺ፤ የስራ ባልደረቦቿ በሆስፒታል ውስጥ እየሰሩ ያሉት "እየተራቡ" መሆኑን የገለጸች ሲሆን ቅዳሜ ዕለት አንድ ባልደረባዋ ጥቂት የቴምር ብስኩቶች ብቻ እንደቀሩት መናገሩን አስታውሳለች።

እስራኤል ተግባራዊ ያደረገችው ሃማስ ታጋቾችን እንዲለቅቅ ግፊት ለማድረግ ቢሆንም የፍልስጤሙ ታታቂ ቡድን አሁንም ታጋቾቹን በጋዛ እንደያዘ ነው። በተጨማሪም እስራኤል ሃማስ እርዳታዎችን እየዘረፈ ነው የሚል ትከሳለች። ቡድኑ ግን ይህንን አስተባብሏል።

እሁድ ዕለት በኻን ዩኒስ የሚገኙ ወታደሮችን የጎበኙት የእስራኤል ሠራዊት አዛዥ ኤያል ዛሚር፤ "ማለቂያ የሌለው ጦርነት አይደለም" ሲሉ ለወታደሮቹ መናገራቸውን ሠራዊቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ሃማስ አብዛኛውን ሀብት እና አቅሙን እንዳጣ መግለጻቸውንም አክሏል።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከ53 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

ሐማስ ባለፈው ዓመት መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።

እስራኤል በጋዛ ጦርነት በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመች ነው ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለጹ ይታወሳል። እስራኤል ይህንን አልተቀበለችውም።