አሸማጋዮች በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማምጣት ጥረታቸውን እያጠናከሩ መሆኑን የሃማስ ባለሥልጣን ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አንድ የሃማስ ከፍተኛ ባለስልጣን ሸምጋዮች በጋዛ አዲስ የተኩስ አቁም እና የታጋቾችን የመልቀቅ ስምምነት ለማድረግ ጥረታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።
ሃማስ ይህንን ቢልም ከእስራኤል ጋር የሚደረገው ድርድር ባለበት ቆሟል።
አስተያየቶቹ የተሰጡት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል እና ኢራን የ12 ቀን ጦርነት ባለፈው ማክሰኞ መቆሙን ተከትሎ "ታላቅ መሻሻል እየታየ ነው" ካሉ እና ልዩ መልዕክተኛቸው ስቲቭ ዊትኮፍ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ስምምነት ሊደረግ "በጣም የቀረበ ነው" ብለው እያሰቡ ባለበት ወቅት ነው።
ረቡዕ ዕለት በጋዛ ላይ በደረሰ የእስራኤል ጥቃት ዕርዳታ ፍለጋ የወጡ ሰዎችን ጨምሮ ቢያንስ 45 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሃማስ የሚመራ የጤና ሚኒስቴር አስታወቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል ሃማስ ኃላፊነቱን በወሰደበት የቦምብ ጥቃት ሰባት ወታደሮች መሞታቸውን አስታውቋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ "በጋዛ ላይ ትልቅ መሻሻል እየታየ ይመስለኛል፣ እኛ ባደረስነው ጥቃት ምክንያት ሳይሆን አይቀርም" ሲሉ በእስራኤል እና በኢራን መካከል በተፈጠረው ግጭት አሜሪካ በኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ የፈጸመችው የአየር ጥቃትን አስመልክተው ትናንት ረቡዕ በብራስልስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
"በጣም ጥሩ ዜና የሚኖረን ይመስለኛል። ከስቲቭ ዊትኮፍ ጋር እየተነጋገርኩ ነበር... [እና] በጋዛ የስምምነት በጣም ቅርብ እንደሆነ ነግሮኛል" ሲሉ አክለዋል።
ትራምፕ ይህን ከተናገሩ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የሃማስ ከፍተኛ ባለስልጣን አሸምጋዮች "የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ በማቀድ ጥብቅ ግንኙነት ፈጥረዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሆኖም ቡድኑ "እስካሁን ምንም ዓይነት አዲስ ሃሳብ አላገኘም" ሲሉ አክለዋል።
አንድ የእስራኤል ባለስልጣን ለሃሬትስ ጋዜጣ እንደተናገሩት በድርድሩ ምንም ዓይነት መሻሻል አለመኖሩን እና ዋና ዋና አለመግባባቶች እልባት አለማግኘታቸውን ተናግረዋል።
አሜሪካ፣ኳታር እና ግብፅ ለማሸማገል ያደረጉት ጥረት በግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ቆሞ የነበረ ሲሆን ዊትኮፍ ሃማስ በእስራኤል ድጋፍ የተቸረውን እና አሜሪካ ባቀረበችው የ60 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ሀሳብ ላይ "ፍፁም ተቀባይነት የሌለውን" ማሻሻያ ፈልጎ ነበር ብለዋል።
እስራኤል የሁለት ወር የተኩስ አቁም ስምምነትን በማፍረስ መጋቢት 18 ቀን በጋዛ ወታደራዊ ጥቃቷን ቀጥላለች።
ሃማስ ታጋቾቹን እንዲለቅ ጫና ማድረግ እንደምትፈልግ ተናግራለች። 50ዎቹ ታጋቾች አሁንም በጋዛ ይገኛሉ፣ ከእነዚህ ውስጥ ቢያንስ 20 ያህሉ በሕይወት እንዳሉ ይታመናል።
በተጨማሪም እስራኤል በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ወደ ጋዛ በሚደርሰው የሰብዓዊ እርዳታ ላይ አጠቃላይ እገዳ የጣለች ሲሆን ከ11 ሳምንታት በኋላ በአሜሪካ አጋሮች ግፊት እና ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ለረሃብ እየተጋለጡ መሆኑን የዓለም አቀፍ ተቋማት ማስጠንቀቂያ ከሰጡ በኋላ እገዳውን በከፊል አንስታለች።
በተመሳሳይ እስራኤል እና አሜሪካ ለፍልስጤማውያን ዋና እርዳታ አቅራቢ የሆነውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ወደ ጎን ለማድርግ ያቀደውን በጋዛ ሰብዓዊ እርዳታ ፋውንዴሽን የሚመራ አዲስ የዕርዳታ ማከፋፈያ ዘዴ ምስረታ ደግፈዋል።
የፋውንዴሽኑ ስርዓት እርዳታ በሃማስ እንዳይሰረቅ ያደርጋል ቡሉም ታጣቂ ቡድኑ ግን ከስርቆት ጋር በተያያዘ የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል።
የዩናይትድ ስቴትስ የግል ደህንነት ኮንትራክተሮችን የሚጠቀመው ፋውንዴሽን ሥራ ከጀመረ አንድ ወር በኋላ ከ44 ሚሊዮን በላይ ምግቦችን የያዙ የምግብ ፓኬጆችን አሰራጭቻለሁ ሲል ረቡዕ ዕለት በሶስት ጣብያዎች ከ2.4 ሚሊዮን በላይ ተሰጥቷል ብሏል።
ሆኖም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሌሎች የረድኤት ቡድኖች መሠረታዊ የሰብዓዊ መርሆችን በሚጻረር መልኩ ከእስራኤል ዓላማ ጋር ይተባበራል በሚል ከፋውንዴሽኑ ጋር አብሮ ለመስራት ፈቃደኛ አልሆኑም።
በእስራኤል ወታደራዊ ቀጠና ውስጥ በሚገኙት የቡድኑ ቦታዎች አቅራቢያ ፍልስጤማውያን እየተገደሉ እንደሆነ የሚገልጹ ሪፖርቶች በየቀኑ በሚባል ደረጃ በመውጣታቸው ስጋት እንዳላቸውም ገልጸዋል።
የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው፣ፋውንዴሽኑ ከአንድ ወር በፊት እአአ በግንቦት 26 ዕርዳታን ማከፋፈል ከጀመረ ወዲህ ዕርዳታ ለመቀበል ሲሞክሩ በትንሹ 549 ሰዎች ተገድለዋል 4,000 ቆስለዋል።
ረቡዕ ጠዋት በሃማስ የሚተዳደረው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት የእስራኤል ወታደሮች በማዕከላዊ ጋዛ የሚገኘው የፋውንዴሽኑ የምግብ ማከፋፈያ ማዕከል አቅራቢያ በሚጠብቁት ሰዎች ላይ በተኩስ ሩምታ ስድስት ሰዎች ተገድለዋል።
ሆኖም የእስራኤል ጦር "በእነዚያ አካባቢዎች ጉዳት የደረሰበትን ምንም ዓይነት ነገር አላውቅም" ሲል ፋውንዴሽኑ በበኩሉ በጣቢያዎቹ አቅራቢያ የተከሰቱት ሪፖርቶች ሀሰት ናቸው ብሏል።















