በጋዛ እርዳታ ሲጠብቁ የነበሩ 46 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጦር መገደላቸውን ተመድ አወገዘ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በማዕከላዊ እና ደቡባዊ ጋዛ በሁለት የተለያዩ ክስተቶች በእስራኤል ወታደሮች በተከፈተ ተኩስ እርዳታ ሲጠባበቁ የነበሩ ቢያንስ 46 ፍልስጤማውን መገደላቸውን የነፍስ አድን ሰራተኞች እና ሆስፒታል ገልጿል።
በአሜሪካ እና እስራኤል በሚደገፈው በዚህ የእርዳታ ስርጭት ወቀት የተፈጠረውን ክስተት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት "ጸያፍ ድርጊት" ሲል የጠራው ሲሆን "የሞት ወጥመድ" ሲልም አክሏል።
ይህ አይነቱ ለጋዛ ነዋሪዎች ሞት ምክንያት የሆነ ክስተት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየዕለቱ በተደጋጋሚ የሚፈጠር ቢሆንም እስራኤል ከሳምንት በፊት ኢራን ላይ በፈጸመችው ጥቃት ምክንያት እምብዛም ትኩረት አላገኘም።
የተባበሩት መንግሥታት በዚህ ወር መግቢያ የጋዛ ሰብዓዊ እርዳታ ፋውንዴሽን ከተቋቋመበት ጊዜ ወዲህ ባሉ ጊዜያት ትናንት የተፈጸመውን ክስተት ሳይጨምር በእስራኤል በቀጥታ በተከፈተ ተኩስ ወይም ሰዎችን እንደ ከለላ በመጠቀም ከ410 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ገልጿል።
ልጇ ለቤተሰቡ እርዳታ ለማምጣት ሄዶ በተከፈተበት ተኩስ የተጎዳባት ኡማ ሬድ የተባለች እናት "የልጆቻችን ህይወት እንዲህ የረከሰው ለምንድን ነው?" ስትል ጠይቃለች።
"ልጄ እህትና ወንድሞቹ የሚመገቡትን ዱቄት ለማምጣት ነበር ከቤት የወጣው ፤አሁን ግን ሆስፒታል ውስጥ በጽኑ ህሙማን ክፍል ነው የሚገኘው" ስትል አክላለች።
ከአልዋዳ ሆስፒታል የወጣ ቪዲዮ በተኩስ ጉዳት የደረሰበት እና በደም የተሸፈነ አንድ ወጣት ወደ ሆስፒታሉ ሲደርስ የተፈጠረውን የንፍስ አድን ግርግር አሳይቷል።
ወዲያውም የሆስፒታሉ አልጋዎች እና ወለሉ በተጎዱ ሰዎች ተሞልቶ ታይቷል።
በዚሁ ቪዲዮ አንድ ሽማግሌ በተቀመጡበት ህይወታቸው አልፎ የሚታይ ሲሆን ባለቤታቸው ፊታቸውን እየነኩ በከፍተኛ ሀዘን ውስጥ ሆነው ታይተዋል።
የሆስፒታል አመራሮች እና በሃመስ የሚመራ ተቋም ቢያንስ 21 ሰዎች እንደሞቱ እና 150 ሰዎች ደግሞ እንደቆሰሉ ገልጸዋል።
በጋዛ የሰብአዊ እርዳታ ፈንድ የቀረበውን እርዳታ ለመቀበል በእስራኤል ወታደራዊ ዞን ውስጥ ተሰብስበው የነበሩ ፍልስጤማውያን ላይ የእስራኤል ወታደሮች ተኩስ ከፍተዋል።
የእስራኤል ጦር ፍልስጤማውያኑ የተሰባሰቡት የእስራኤል ወታደሮች 'ኦፕሬሽን' ከሚያከናውኑበት ሰፍራ አቅራቢያ ነበር ብሏል።
ጨምሮም የእስራኤል ወታደሮች በከፈቱት ተኩስ የተጎዱ ሰዎች እንዳሉ ሪፖርት እንዳለ ገልጾ ሞት ስለመኖሩ እየተጣራ ነው ብሏል።
የእርዳታ ፋውንዴሽኑ ግን "በኛ ጣቢያ አቅራቢያ የተፈጠረ ክስተት የለም" ብሏል።
የጤና ባለሙያዎች እና የነፍስ አድን ሠራተኞች ግን ቢያንስ በደቡባዊ ጋዛ 25 ሰዎች ከፋውንዴሽኑ ጣቢያ ትናንት ማክሰኞ መገደላቸውን ገልጿል።
ሃትም ኣቡ ረጃል የተባለ የዓይን እማኝ የእስራኤል ወታደሮች በሲቪል ሰዎች ላይ ሲተኩሱ እንደነበረ እና ደም በየቦታው ይታይ ነበር ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።
"በዙሪያችን የነበረ እያንዳንዱ ሰው ተጎድቶ ነበር። ምን አልባት ወደ 30 የሚሆኑ ሰዎች ተጎድተው የሚረዳቸው ሰው አልነበረም። ለማትረፍ ስንረባረበው የነበረው ዘመዶቻችን ነው" ብሏል።
የእስራኤል ጦር ግን ከሚባለው ነገር በተቃራኒ በራፋ የእርዳታ ጣቢያ ስለተፈጠረው ክስተት መረጃ የለኝም ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።
እስራኤል ጋዛ ላይ የጣለችውን ሙሉ ከበባ ባለፈው ወር ካላላች እና ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ እስራኤል የተመሰረተው የእርዳታ ፋውንዴሽን ባለፈው ሳምንት ሥራ መጀመሩ ተገልጿል።












