ትራምፕ የተኩስ አቁም እንዲደረስ ጥረት እያደረጉ ባለበት ወቅት እስራኤል ነዋሪዎች ከሰሜን ጋዛ እንዲለቁ አዘዘች

ቁሳቁሶቻቸውን በጋሪ የጫኑ ፍልስጤማውያን በጋዛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ግፊት እያደረጉ ባለበት ወቅት እስራኤል ፍልስጤማውያን ከሰሜናዊ የጋዛ ክፍል ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላለፈች።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል "ወደ ደቡብ ጥቃቱን እያጠናከረ እና እያሰፋ በመሆኑ" በጋዛ ከተማ እና በጃባሊያ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ወደ ደቡብ ወደ አል ማዋሲ የባሕር ዳርቻ አካባቢ እንዲሄዱ ተነግሯቸዋል።

እሁድ ዕለት ከቀትር በፊት በነበሩት 24 ሰዓታት ውስጥ እስራኤል በፈፀመችው ጥቃት ቢያንስ 86 ሰዎች መሞታቸውን በሐማስ የሚመራ የጤና ሚኒስቴር አስታወቋል።

በአል ማዋሲ "ደኅንነቱ የተጠበቀ ዞን" ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተፈፀመው ጥቃት ከተገደሉት መካከል ሦስቱ ሕጻናት መሆናቸውን ወላጆቻቸው ተናግረዋል።

ትራምፕ "በጋዛ ስምምነት እንዲደረስ" እና "ታጋቾች እንዲለቀቁ" ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

ቅዳሜ ዕለት ትራምፕ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከሐማስ ጋር "አሁን" ለመደራደር በሂደት ላይ መሆናቸውን በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ጽፈው ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ አቪሻይ አድራይ እሁድ ዕለት እንደተናገሩት የእስራኤል ጦር በሰሜን ጋዛ "አሸባሪዎችን እና የሽብር መሠረተ ልማቶችን ለማጥፋት" እየተንቀሳቀሰ ነው።

የሕክምና ባለሙያዎች እና ነዋሪዎች ለሮይተርስ እንደተናገሩት እሁድ ማለዳ በጋዛ የሚፈጸሙት የቦምብ ድብደባዎች በመጨመራቸው በርካታ ቤቶችን ወድመዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በጋዛ ሐማስ የሚመራ የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ ለመገናኛ ብዙኃን እንደገለፀው እሁድ ዕለት ብቻ በትንሹ 23 ሰዎች ተገድለዋል።

በደቡባዊ ጋዛ ኻን ዮኒስ አቅራቢያ በሚገኘው አል ማውሲ የተፈናቀሉ ሰዎች በሚኖሩበት ድንኳን ላይ የእስራኤል ጦር በፈፀመው የአየር ድብደባ አምስት ሰዎች መሞታቸውን የሕክምና ባለሙያዎች ገልጸዋል።

ሦስት ሕጻናትን ጨምሮ አምስት የማዓሩፍ ቤተሰብ አባላት ተገድለዋል።

እናታቸው ኢማን አቡ ማዓሩፍ "መሬት ላይ ተኝተን ሳለን ነው በቦምብ የደበደቡን" ስትል ተናግራለች። ምንም ጥፋት አልሠራንም። ልጆቼ ተገድለዋል፣ የተቀሩት ደግሞ በፅኑ ሕክምና ክፍል ውስጥ ናቸው።"

አባታቸው ዘያድ አቡ ማዓሩፍ ለሮይተርስ እንደተናገሩት ቤተሰቡ "ደኅንነቱ ወደ የተጠበቀ ዞን" ከወር በፊት እስራኤል ወደ አል ማውሲ እንዲሄዱ ካዘዘች በኋላ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

የእስራኤል መከላከያ ስለ ተፈጸመው ጥቃት ቢቢሲ ላቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ ያለ ተጨማሪ መረጃ የተለየ ምላሽ መስጠት እንደማይችል ተናግሯል።

ነገር ግን "ዓለም አቀፍ ሕግን በመከተል በሲቪሎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ተጨባጭ ጥንቃቄዎች ይደረጋሉ" ብሏል።

እንዲሁም እሁድ ዕለት የ20 ዓመቱ የመከላከያ ሠራዊት አባል ሳጅን ይስራኤል ናታን ሮዝንፌልድ በሰሜን ጋዛ ተገድሏል።

እስራኤል በጋዛ የምታካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻ በቀጠለችበት በዚህ ወቅት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ሊደረግ ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የኳታር አሸማጋዮች አሜሪካ የምታሳድረው ጫና ውጤት ያስገኛል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

እስራኤል በመጋቢት ወር በጋዛ ላይ አዲስ ጥቃት ስትሰነዝር ለሁለት ወራት የቆየው የተኩስ አቁም ፈርሷል።

በጥር 19 የጀመረው የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሦስት እርከኖችን እንዲይዝ ሆኖ የተዘጋጀ ቢሆንም የመጀመሪያውን ደረጃ ማለፍ ግን ሳይችል ቀርቷል።

በዚያ የተኩስ አቁም ስምምነት ውስጥ በሁለተኛነት ቋሚ የተኩስ አቁም ላይ መድረስ፣ በእስራኤል ውስጥ በታሰሩ ፍልስጤማውያን ምትክ በጋዛ የታገቱትን መልቀቅ እና የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ መውጣትን የሚሉትን ያካትት ነበር።

ሐሙስ ዕለት አንድ የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለቢቢሲ አደራዳሪዎቹ አዲስ የተኩስ አቁም ላይ እንዲደረስ እና የታገቱት እንዲለቀቁ ጥረታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

ነገር ግን ከእስራኤል ጋር የሚደረገው ድርድር ቆሟል።

እስራኤል በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻ የጀመረችው ሐማስ መስከረም 26/2016 ጥቃት ፈጽሞ 1,200 እስራኤላውያን ከገደለ እና 251 ካገተ በኋላ ነው።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጋዛ ከ56 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።