እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት በትንሹ 81 ሰዎች መሞታቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስራኤል እስከ ቅዳሜ ዕኩለ ቀን ድረስ ባለት 24 ሰዓታት ውስጥ በጋዛ በፈጸመችው የአየር ድብደባ በትንሹ 81 ፍልስጤማውያን ሲገደሉ ከ400 በላይ መቁሰላቸውን በሃማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በጋዛ ከተማ ስታዲየም አካባቢ በተፈጸመ ጥቃት ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 11 ሰዎች መገደላቸውን የአል ሺፋ ሆስፒታል ሠራተኞች እና ዓይን እማኞች ለዜና አውታሮች ተናግረዋል።
ስታዲየሙ የተፈናቀሉ፣ በድንኳን ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ለማስጠለል የዋለ ነው።
ቢቢሲ የተመለከታቸውን እና ያረጋገጣቸው ምስል ሰዎች ሬሳ ለማውጣት በባዶ እጃቸው እና በአካፋ አሸዋ ሲቆፍሩ ያሳያል።
ቢቢሲ የእስራኤልን ጦር አስተየየት የጠየቀ ቢሆንም ወድያውኑ ምላሽ አላገኘም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥለው ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ሊደረግ ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
የኳታር አሸማጋዮች ኤሪካ የምታሳድረው ጫና ውጤት ያስገኛል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
በመጋቢት ወር እስራኤል በጋዛ ላይ አዲስ ጥቃት ስትሰነዝር ለሁለት ወራት የቆየው የተኩስ አቁም ፈርሷል።
በጥር 19 የጀመረው የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሦስት እርከኖችን እንዲይዝ ሆኖ የተዘጋጀ ቢሆንም የመጀመሪያውን ደረጃ ማለፍ ግን ሳይችል ቀርቷል።
በዚያ የተኩስ አቁም ስምምነት ውስጥ በሁለተኛነት ቋሚ የተኩስ አቁም ላይ መድረስ፣ በእስራኤል ውስጥ በታሰሩ ፍልስጤማውያን ምትክ በጋዛ የታገቱትን መልቀቅ እና የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ መውጣትን የሚሉትን ያካትት ነበር።
ሐሙስ እለት አንድ የሐማስ ከፍተኛ ባለስልጣን ለቢቢሲ አደራዳሪዎቹ አዲስ የተኩስ አቁም ላይ እንዲደረስ እና የታገቱት እንዲለቀቁ ይረታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።
ነገርግን ከእስራኤል ጋር የሚደረገው ድርድር ቆሟል።
ቅዳሜ አመሻሽ ላይ በቴል አቪቭ በተካሄደ ሠልፍ በጋዛ በሐማስ የተያዙ ቀሪ እስራኤላውያን ታጋቾችን እንዲለቀቁ ከስምምነት እንዲደረስ ተጠይቋል።
የሠልፉ አዘጋጆቹ "ጦርነቱን አቁሞ ሁሉንም ታጋቾች ወደ ቤታቸው ለመመለስ ጊዜው አሁን ነው" ብለዋል ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ጥቃት በጋዛ ቀጥሏል። አርብ ማምሻውን በጋዛ ስታዲየም አቅራቢያ በተካሄደው ጥቃት በትንሹ 11 ሰዎች መሞታቸውን የሆስፒታሉ ሠራተኞች እና የዓይን እማኞች ተናግረዋል።
አንድ የዓይን እማኝ ተቀምጠው ሳለ "በድንገት ከፍተኛ ፍንዳታ ሰማን" ብለዋል።
አህመድ ኪሻዊ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት "ይህ ቦታ በድንኳኖች የተሞላ ነበር። አሁን ድንኳኖቹ ከአሸዋ በታች ተቀብረዋል።"
"እዚህ ምንም የሚፈለጉ ሰዎች የሉም፤ ወይም እነሱ [እስራኤላውያን] እንደሚሉት አሸባሪዎች የሉም፤...ያለ ርህራሄ የተጠቁ ሰላማዊ ነዋሪዎች፣ ሕጻናት ብቻ ናቸው ያሉት" ብሏል።
ቢቢሲ ሰላማዊ ዜጎች እና የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አሸዋማውን መሬት በእጃቸው እና ዶማ ሬሳ ለማግኘት ሲቆፍሩ የሚያሳዩ ምስሎችን ተመልክቶ እውነተኛነታቸውን አረጋግጧል።
በአል ማዋሲ አካባቢ በሚገኝ አፓርትመንት እና ድንኳን ላይ በተፈጸመ ጥቃት 14 ተጨማሪ ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።
በአል ማዋሲ በተካሄደው የአየር ድብደባ ሥስት ሕጻናትን እና ወላጆቻቸውን መገደላቸውን ዘመዶቻቸው ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግረዋል።
የልጆቹ አያት ሱአድ አቡ ተኢማ "እነዚህ ልጆች ምን አደረጓቸው? ጥፋታቸው ምንድን ነው?" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ቅዳሜ ከሰአት በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን በተጠለሉበት በጃፋ ትምህርት ቤት አቅራቢያ በሚገኘው ቱፋህ ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት መገደላቸው ተዘግቧል።
በአድማው አምስት ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ ስምንት ሰዎች መሞታቸውን የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የዓይን እማኝ የሆኑት መሀመድ ሀቡብ ለሮይተርስ እንደተናገሩት በአድማው የወንድሞቹ ልጆች፣ አባታቸው እና የጎረቤቶቻቸው ልጆች ተገድለዋል።
"ምንም አላደረግንባቸውም፤ ለምን ይጎዱናል፣ ጎዳናቸው? እኛ ሰላማዊ ሰዎች ነን" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስቴሩ በአንዳንድ አካባቢዎች መንቀሳቀስ ባለመቻሉ አምቡላንስ እና ሲቪል መከላከያ ሠራዊት በፍርስራሽ እና በመንገዶች ላይ የወደቁ በርካታ ተጎጂዎችን ለማንሳት ተቸግረው እንደነበር ተናግሯል።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ስላደረሰው ጥቃት እስካሁን የሰጠው መግለጫ የለም።
የእስራኤል መከላከያ ቅዳሜ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ በጋዛ ከተማ ሳብራ አካባቢ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ከፍተኛ አመራር የሆነውን ሃክሃም ሙሀመድ ኢሳ አል ኢሳን መግደሉን አስታውቋል።
የእስራኤል መከላከያ ግለሰቡ የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ መስራች አባላት መካከል አንዱ መሆኑን ተናግሯል።
የሐማስ አጠቃላይ የደህንነት ምክር ቤት አባል፣ እና በመስከረም 26 2016 ጥቃት "እቅድ እና አፈጻጸም ውስጥ ጉልህ ሚና" እንደነበረው ተናግሯል።
በዚህ ጥቃት 1,200 እስራኤላውያን ሲገደሉ 251 የታገቱ ሲሆን የእስራኤል ጦር ከዚህ ጥቃቱ በኋላ በጋዛ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ጀምሯል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በጋዛ ከ56,000 በላይ ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።















