እስራኤል በታዋቂው የጋዛ የባህር ዳርቻ ካፌ በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 20 ፍልስጤማውያን ተገደሉ

እስራኤል የፈጸመችው ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto via Getty Images

እስራኤል በታዋቂው የጋዛ የባህር ዳርቻ ካፌ በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 20 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የህከምና ባለሙያዎች እና የዓይን እማኞች ገለጹ።

ካፌው በአብዛኛው በተማሪዎች፣ ጋዜጠኞች እና ተሟጋቾቸ የሚዘወተር ነው።

በባህር ዳርቻው አጠገብ ድንኳኖች ባሉት አል ባቃ ካፍቴሪያ በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉ ቢያንስ 20 የፍልስጤማውያን አስክሬን መውጣቱን በሐማስ የሚተዳደረው የጋዛ የሲቪል መከላከያ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከተገደሉት በተጨማሪ በርካታ ፍልስጤማውያን ቆስለዋል።

ጥቃቱ ባደረሰው ፍንዳታ በተፈጠረ ጥልቅ ጉድጓድ የገቡ ነዋሪዎችን ህይወት ለመታደግ የነፍስ አድን ሰራተኞች መሰማራታቸውንም አክለዋል።

" ድንገት ከባድ ፍንዳታ ስሰማ፤ ወደ ካፌው እየሄድኩ በጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ ነበርኩኝ " ሲል የፕሮዳክሽን ኩባንያ ባለቤት የሆነው የፎቶ ባለሙያው አዚስ አል አፊፊ ለቢቢሲ

"ወደ ስፍራው ሮጥኩኝ። ባልደረቦቼ፣ ሁልጊዜም የማገኛቸው ጓደኞቼ እዛው ነበሩ። ትዕይንቱ አሰቃቂ ነበር። አስክሬኖች በየቦታው ተበታትነው፤ በደም አበላ ተለውሰው። ጩኸት በየቦታው ይሰማ ነበር" ሲል ተናግሯል።

ከእስራኤል የጦር አውሮፕላን የተወነጨፈ ሚሳኤል አካባቢውን ሲመታ የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን ተሟጋቾች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ አጋርተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጥቃቱን ተከትሎ የወጡ ቪዲዮዎች አስክሬኖች በየስፍራው ተበታትነው ይታያሉ።

በጋዛ የሜዲትራንያን የባህር ዳርቻ ላይ የሚገኘው አል ባቃ ካፍቴሪያ የኢንተርኔት አገልግሎት እና መስሪያ ቦታ የሚሰጥ ሲሆን በጋዜጠኞች፣ በተሟጋቾች እንዲሁም በኦንላይን ስራቸውን በሚሰሩ ታዋቂነትን ያተረፈ ነው።

ከእስራኤል ጦር በኩል ጥቃቱን አስመልክቶ የተሰጠ አስተያየት የለም።

የካፌው ጥቃት የተሰማው የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ ላይ ተከታታይ የአየር ጥቃቶች ፈጽማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን መፈናቀላቸውን እማኞች ከተናገሩ በኋላ ነው።

የነፍስ አድን ቡድኖች የአምስት ፍልስጤማውያን አስክሬኖችን ያወጡ ሲሆን በርካታ የተጎዱ ሰላማዊ ዜጎች በጋዛ ከተማ ወደሚገኘው አል አህሉ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ከስፍራው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚደረገውን ጥረት ላይ እንዲያተኩሩ ከፍተኛ ጫናዎች እየጨመሩ ይገኛሉ።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኔታንያሁ ከሐማስ ጋር ለመደራደር "በአሁኑ ወቅት" እየሰሩ መሆናቸውን ቅዳሜ ዕለት በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አስፍረዋል።

ከዚያ ቀደም ብሎ አንድ የሐማስ ከፍተኛ ባለስልጣን አሸማጋዮች አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ጥረታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸው ፤ነገር ግን ከእስራኤል ጋር የሚደረገው ድርድር ቆሟል ብለዋል።

ለሁለት ወራት የቆየው የተኩስ አቁም ስምምነት እስራኤል በጋዛ ላይ አዲስ ጥቃት መጀመሯን ተከትሎ ፈርሷል። የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሶስት ምዕራፎች እንዲኖሩት የታሰበ ቢሆንም የመጀመሪያውን ማለፍ አልቻለም።

እስራኤል በተጨማሪም ወደ ጋዛ የሚደርሰውን የሰብዓዊ እርዳታ ሙሉ በሙሉ ዘግታ የነበረ ሲሆን በዓለም አቀፉ ደረጃ ማስጠንቀቂያዎች መሰጠቱን ተከትሎ ከ11 ሳምንት በኋላ በከፊል አላልታለች።

ለጋዛ እርዳታ ለማከፋፈል የተሰማራው በእስራኤል እና አሜሪካ የሚደገፈው አወዛጋቢው የጋዛ ሂውማኒታሪያን ፋውንዴሽን ስራውን ጀምሯል።

ሆኖም ከዚህ ድርጅት ጣቢያ አቅራቢያ እርዳታ ለመቀበል በተሰባሰቡ ፍልስጤማውያን ላይ የእስራኤል ጦር በሚከፍተው ተኩስ በየዕለቱ በርካታ ፍልስጤማውያን እየተገደሉ ቀጥለዋል።