እስራኤል በጋዛ መኖሪያ ቤት በፈጸመችው ጥቃት የሆስፒታል ዳይሬክተር ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Gaza Ministry of Health
እስራኤል በጋዛ የኢንዶኔዥያ ሆስፒታል ዳይሬክተር መኖሪያ ቤት ላይ በፈጸመችው ጥቃት እሳቸውን ጨምሮ በርካታ የቤተሰቦቻቸው አባላት መገደላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
ዶ/ር ማርዋን ሱልጣን በህክምናው ዘርፍ ለረጅም ጊዜ እንዳገለገሉ ያስታወቀው በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ጥቃቱን "በህክምና አባሎቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለ አሰቃቂ ወንጀል" ሲል አውግዞታል።
የእስራኤል ጦር በበኩሉ በጋዛ ከተማ "ቁልፍ አሸባሪ" መምታቱን እና በጥቃቱ "ተሳትፎ የሌላቸው ሰላማዊ ዜጎች" በመጎዳታቸው እየገመገምኩ ነው ብሏል።
እስራኤል በተጨማሪም አል ማዋሲ በተሰኘው "ደህንነቱ የተጠበቀ ዞን" ላይ በፈጸመችው ጥቃት ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ አምስት ሰዎች ሲጎደሉ ሌሎች ደግሞ መቁሰላቸውን የዜና ወኪሎች ዘግበዋል።
ዶክተር ሱልጣን ሙያቸው በርህራሄ የተሞላ ነው ሲል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጾ "ህዝባችን በተከታታይ ጥቃት በሚፈተንባቸው እነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያቶች እሳቸውም በፈታኝ ሁኔታ የትጋት፣ የጽናት እና የቅንነት ተምሳሌት ነበሩ" ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት የኢንዶኔዥያ ሆስፒታል "በእስራኤል ተደጋጋሚ ጥቃቶች መዋቅራዊ ጉዳት እንደደረሰበት" መግለጹን ተከትሎ ፤ዳይሬክተሩ ዶክተር ሱልጣን በሆስፒታሉ አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን ሚኒስቴሩ አክሏል።
የእስራኤል መከላከያ በበኩሉ በአካባቢው "የአሸባሪ መሰረተ ልማት ቦታዎችን" እያጠቃሁ ነው ይላል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰሜን ጋዛ አገልግሎት የሚሰጥ ሆስፒታል እንደሌለ ገልጿል።
የእስራኤል ጦር የህክምና እና የሰብዓዊ ረድዔት አባላትን ኢላማ አድርጋለች ሲል የጤና ሚኒስትሩ ከሷል።
የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት በሰጠው ምላሽ "ተሳትፎ በሌላቸው ግለሰቦች ላይ የሚደርስ ማንኛውም ጉዳት ያሳዝናል" ሲል በእነሱ ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን በተቻለ መጠን ለመቀነስ እንደሚሰራ ተናግሯል።
ጦሩ በተጨማሪ ሐማስ "የሲቪል መሰረተ ልማቶችን ለሽብር ተግባር እንዲሁም ሰላማዊ ዜጎችን እንደ ጋሻ በመጠቀም የአለም አቀፍ ህግን ጥሷል" ብሏል።
ነገር ግን የዶክተር ሱልጣን ልጅ ሉብና አል ሱልጣን የእስራኤል "ኤፍ 16 ሚሳኤል በአባቴ መኝታ ክፍል ላይ አነጣጥሮ በቀጥታ ጥቃት አድርሶበታል" ስትል ተናግራለች።
"በቤቱ ውስጥ ያሉ ክፍሎች በሙሉ ጉዳት ሳይደርስባቸው የሱ መኝታ ክፍል ነው በሚሳኤል የተመታው። አባቴ ሰማዕት ሆኗል" ስትል ለአሶሺዬትድ ፕሬስ ተናግራለች።
" አባቴ ከየትኛውም እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት የለውም፤ በጦርነቱ ጊዜ የሚያስፈራው የሚያክማቸው ህመምተኞች ህይወት ብቻ ነው" ብላለች።
በባለፉት 24 ሰዓታት እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 139 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጤና ሚኒስቴሩ አክሎ ገልጿል።
በኻን ዩኒስ አል ማዋሲ የተሰኘ አካባቢ ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸውን ሌሎች ደግሞ መቁሰላቸውን የዜና ወኪሎች ዘግበዋል።
እስራኤል ይህንን ጥቃት የፈጸመችው የተፈናቀሉ ሰዎች መጠለያ ብለው በሰሩት ድንኳን ላይ ነው።
የቤተሰብ አባላት የተገደሉባቸው ግለሰቦች እንደተናገሩት ጥቃቱ የተፈጸመው ከሌሊቱ 6፡40 ላይ ሲሆን በወቅቱም ተኝተው እንደነበር ተናግረዋል።















