ኢትዮጵያ የተጠቀሰችበት ፍልስጤማውያንን ወደ ሌላ አገር የማስፈር ዕቅድ

የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጋዛ የጦር አውድማ ከሆነች ሁለት ዓመት ሊሞላ እየተቃረበ ነው። ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ነዋሪዋ በጦርነት እሳት እየተለበለበ በረሃብ እየተሰቃየ ይገኛል።

እስራኤል እያካሄደችው ባለው የምድር፣ የባሕር እና የአየር ጥቃት የጋዛ አብዛኛው ክፍል ወድሟል። ነዋሪዎች በፍርስራሽ እና በድንኳን ውስጥ እየኖሩ ባሉበት ሁኔታ ባለፈው የካቲት ትራምፕ ያልተጠበቀ እና አዲስ ሃሳብ አቅርበዋል።

ፕሬዝዳንቱ በጋዛ የሚካሄደውን ጦርነት ለማብቃት በሚል አገራቸው አሜሪካ ጋዛን በቁጥጥሯ ሥር አድርጋ መልሳ በመገንባት ቅንጡ የመኖሪያ እና የመዝናኛ ስፍራ እንደምታደርገው በይፋ ካሳወቁ በኋላ ጉዳዩ መነጋገሪያ ሆኗል።

በዚህ ሂደትም በጦርነት የተጎሳቆሉት የጋዛ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው ወደ ሌላ አገር እንዲሰፍሩ እንደሚደረግ እና የመመለስ መብት እንደሌላቸው ተነግሯል።

ይህም ጋዛን ከፍልስጤማውያን ይዞታነት በማውጣት ዜጎቿንም ስደተኛ የሚያደርግ ነው የሚል ተቃውሞ ቀርቦበታል።

ይህንን የትራምፕ ሃሳብ በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ወዳጅ የሆኑ አገራትን ጨምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሳይቀር ያወገዙት ሲሆን፣ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ግን ዕቅዱን አድንቀው እንሚደግፉት ገልጸዋል።

ተፈናቃይ የጋዛ ነዋሪዎች በመንገድ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ባለፈው ጥር የተኩስ አቁም በተደረሰበት ጊዜ በጦርነቱ የተፈናቀሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ከደቡባዊ ጋዛ ወደ ስሜን ሲመለሱ

ጋዛ

በዓለም ታሪክ ውስጥ ተጠቃሽ ሚና ባለው የመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ያለችው ጋዛ ሰርጥ የ45 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 10 ኪሎ ሜትር ስፋት አላት። በሰሜን እና በምሥራቅ ከእስራኤል፣ በደቡብ ከግብፅ እንዲሁም በምዕራብ የሜዲትራኒያን ባሕር ያዋስኗታል።

የግብፅ ፈርዖኖች፣ ባቢሎናውያን፣ ፍልስጤማውያን፣ ታላቁ አሌክሳንደር እና ሌሎችም አካባቢውን ለመቆጣጠር ተፋልመዋል። በኋላም ሮማውያን፣ ሞንጎሎች፣ የመስቀል ጦረኞች እና የሙስሊም ሠራዊቶች ጋዛን ወርረው ነበር።

ከ16ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ አስከ አውሮፓውያኑ 1917 ድረስም ጋዛ የኦቶማን ቱርኮች ግዛት መንግሥት አካል ሆና ቆይታለች።

ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት ጋር ጋዛ በብሪታኒያ ወታደሮች ቁጥጥር ስር ወድቃ ከቀረው የፍልስጤም ግዛት ጋር በብሪታኒያ ስር ስትተዳደር ነበር።

ከዚያም በኋላ ጋዛ ከብሪታኒያ እጅ ወጥታ በግብፅ ቀጥሎም በእስራኤል ቁጥጥር ስር እንዲሁም በፍልስጤም አስተዳደር ውስጥ ቆይታለች። በአሁኑ ወቅት የጦር አውድማ የሆነችው ጋዛ በአጥር ተከብባ አብዛኞቹ ስደተኛ የሆኑ የ2.3 ሚሊዮን ፍልስጤማውያን መኖሪያ ናት።

ከብሪታኒያ ቀጥላ ጋዛን በወረራ ይዛ የነበረችው ግብፅ የነበረች ሲሆን፣ የ1967ቱን በእስራኤል እና በአረብ አገራት መካከል የተካሄደውን የስድስት ቀናቱን ጦርነት ተከትሎ በእስራኤል እጅ ገብታ ቆይታለች።

ምንም እንኳን እስራኤል በአውሮፓውያኑ 2005 የአይሁድ ሰፈራዎችን አፍርሳ ሠራዊቷን ብታስወጣም አጥር ገንብታ የአየር፣ የምድር እና የባሕር መግቢያ መውጫዎቿን ዘግታ በጥብቅ ቁጥጥር ስር አቆይታታለች።

ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ መኖሪያ የሆነችው ጋዛ የሐማስ እና የእስራኤል ጦርነት ከጀመረበት ከመስከረም 26/2016 ዓ.ም. ወዲህ የነዋሪዋ ቁጥር በስድስት በመቶ መቀነሱን የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።

ለዚህም ምክንያቱ ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ጦርነት በመሸሽ ግዛቲቱን ለቀው ሲወጡ፣ ወደ 60 ሺህ የሚልቁት ደግሞ በጦርነቱ ሳቢያ ሞተዋል ተብሎ እንደሚታመን የፍልስጤም ስታትስቲክስ ጽህፈት ቤት ገልጿል።

ኔታኒያሁ እና ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ የካቲት ላይ ዋሽንግተንን በጎበኙበት ወቅት ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር

የትራምፕ ዕቅድ

እስራኤል ባካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ አብዛኛው ክፍሏ የወደመው ጋዛ በአሁኑ ወቅት የፍርስራሾች ክምር ሆናለች። የመኖሪያ ሕንጻዎች፣ ተቋማት እና ሌሎች መሠረተ ልማቶቿ በእስራኤል የአየር እና የከባድ መሳሪያ ጥቃት ወድሟል።

ጦርነቱን በመሸሽ እዚያው ጋዛ ውስጥ በፍርስራሾች ስር እና በድንኳኖች ውስጥ የሚኖሩት የጋዛ ነዋሪዎች ጦርነቱ ቆሞ ሰላማዊ ኑሯቸው የሚቀጥልበትን ጊዜ እየተጠባበቁ ነው። ነገር ግን አሜሪካ እና እስራኤል የጋዛ ነዋሪዎችን ወደ ሌላ አገር የማዞር ዕቅድ እና ፍላጎት እንዳላቸው ይፋ አድርገዋል።

በተለይ ባለፈው ጥር መጨረሻ ላይ ትራምፕ ይፋ ያደረጉት ሃሳብ ብዙ እያነጋገረ ነው። ጋዛን ከእስራኤል በመረከብ ነዋሪዎቿን አስወጥቶ ቅንጡ የባሕር ዳርቻ የመኖሪያ እና የመዝናኛ ስፍራ የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው ፕሬዝዳንቱ አሳውቀዋል።

የትራምፕ ዕቅድ የጋዛ የተራረፉ ግንባታዎችን እና ፍርስራሾችን ብቻ ሳይሆን ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎችን ከግዛቲቱ በማፈናቀል በተለያዩ አገራት ውስጥ ማስፈር እና በዓመታት የመልሶ ግንባታ ጋዛን ከሥር መሠረቷ መቀየር ነው።

ፍልስጤማውያንን ከጋዛ መንቀል የሚለው ሐሳብ የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት ተቃውሞ ገጥሞታል። ዕቅዱ በጦርነት በተጎሳቆሉት ጋዛውያን ላይ የዘር ማጽዳት ወንጀል ነው በማለት የመብት ተሟጋቾች ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።

ባለፈው ጥር የወጣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪፖርት እንደሚያመለክተው እየተካሄደ ባለው ጦርነት በጋዛ ውስጥ ካሉት ቤቶች ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ጉዳት ደርሶባቸዋል ወይም ወድመዋል። ከግዛቲቱ ነዋሪዎች መካከል 1.9 ሚሊዮን የሚሆኑት ተፈናቃይ ሆነዋል።

ካርታ

የጋዛ ነዋሪዎች ወዴት ይሄዳሉ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በፕሬዝዳንት ትራምፕ ዕቅድ መሠረት ጋዛን ወደ ቅንጡ የባሕር ዳርቻ መዝናኛ ሥፍራ ለመቀየር ነዋሪዎቿ በግብፅ እና በዮርዳኖስ እንደሚሰፍሩ የተነገረ ሲሆን፣ ኋላ ላይም የሌሎች አገራት ስም ተካቷል።

የእስራኤሉ የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች ፍልስጤማውያኑን ለማስፈር የሚያስችሉ አገራትን የመለየት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ባለፈው መጋቢት ወር ከመግለጻቸው በተጨማሪ፣ ይህንን ሥራ የሚከታተል ትልቅ ክፍል በእስራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ እየተዘጋጀ ነው ብለው ነበር።

የጋዛ ነዋሪዎችን ወደ ሌላ አገር የማዘዋወሩ ዕቅድ ከተሰማ በኋላ አሜሪካ እና እስራኤል ሥራ መጀመራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ (አኤፒ) የአገራቱን ባለሥልጣናት ጠቅሶ ዘግቧል።

ለዚሁ ተግባርም አሜሪካ እና እስራኤል የሱዳን፣ የሶማሊያ እና ነጻ አገርነቷን ያወጀችው የሶማሊላንድ ባለሥልጣናትን ማነጋጋራቸውን ኤፒ ከዲፕሎማቲክ ምንጮች መረጃ ምግኘቱን ገልጾ ነበር።

ከጋዛ የሚነሱትን ፍልስጤማውያን ተቀብለው ለሚያሰፍሩ አገራት እስራኤል እና አሜሪካ የገንዘብ፣ የዲፕሎማሲ እና የደኅንነት ድጋፍ እንደሚሰጡም እየተነገረ ነው።

ሁለት የሱዳን ባለሥልጣናት ለአል ጀዚራ እንዳረጋገጡት የትራምፕ አስተዳደር ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጋር እየተዋጋ ያለውን ወታደራዊውን መንግሥት ፍልስጤማውያንን በተመለከተ አነጋግሯል። ለዚህም ወታደራዊ፣ የመልሶ ግንባታ እና ሌሎች ድጋፎችን ለመስጠት እንደሚፈልግ አሳውቋል።

ነገር ግን ሱዳን የቀረበላትን ሃሳብ ወዲያውኑ ውድቅ እንዳደረገችው ባለሥልጣናቱ የተናገሩ ሲሆን፣ ገዳዩም መልሶ አልተነሳም።

ከሶማሊያ ተለይታ የራሷ መንግሥት ያላት እና ዓለም አቀፍ ዕውቅናን የምትሻው የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዲራህማን ዳሂር አዳን ጉዳዩን በተመለከተ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናግረዋል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ስሟ የተነሳው የሶማሊያ በአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ዳሂር ሐሳን ለሲቢኤስ ኒውስ በሰጡት ምላሽ፣ የአሜሪካም ሆነ የእስራኤል ባለሥልጣናት በዕቅዳቸው ዙሪያ ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ግንኙነት አላደረጉም ሲሉ አስተባብለዋል።

የፈራረሰችው ጋዛ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የፈራረሰችው ጋዛ

ፍልስጤማውያንን የሚቀበል አገር ፍለጋ

ከጋዛ የሚነሱ ፍልስጤማውያንን ይቀበላሉ ተብለው ቀደም ብሎ ስማቸው የተነሳው አገራት ጉዳዩን እንደማያውቁት በይፋ ሲያሳውቁ ሌሎች ደግሞ ዝምታን መርጠው ቢቆዩም፣ የትራምፕ ዕቅድ ግን ተግባራዊ እንደሚደረግ ሲገልጽ ቆይቷል።

ከሳምንት በፊት አክሲዮስ የተባለው የአሜሪካ ድረ ገጽ ያወጣው ዜና ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ሁለት አገራት ፍልስጤማውያንን ለማስፈር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እስራኤል ንግግር እያደረገች መሆኑን የሚያመለክት ዘገባ አውጥቷል።

ጉዳዩን በተመለከተ የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት ሞሳድ ኃላፊ የሆኑት ዴቪድ ባርኒ ዋሽንግተን ውስጥ ከትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ጋር በነበራቸው ውይይት ፍልስጤማውያኑን ለማስፈር ከሦስት አገራት ጋር እየተናገሩ መሆናቸው እና አሜሪካ ድጋፍ እንድትሰጣቸው ጠይቀዋል ብሏል።

ሁለት ጉዳዩን የሚያውቁ ምንጮች ነገሩኝ ብሎ አክሲዮስ እንደዘገበው የሞሳድ ኃላፊው እስራኤል በተለይ ከኢትዮጵያ፣ ከኢንዶኔዢያ እና ከሊቢያ ጋር ግንኙነት ማድረጓን እና አገራቱ ከጋዛ የሚወጡትን ፍልስጤማውያን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆናቸውን እንደገለጹ ተናግረዋል።

በአሜሪካ እና በእስራኤል ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል በነበረው ንግግር ባርኒ አሜሪካ ለአገራቱ ማበረታቻ በመስጠት በጉዳዩ ላይ እስራኤል ማሳመን እንድትችል እንድትረዳ ጠይቀዋል ተብሏል።

ነገር ግን ጉዳዩን በሚመለከት ስማቸው የተጠቀሰው ሦስቱ አገራት የሰጡት አስተያየት የሌለ ሲሆን፣ ቢቢሲ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ ምላሽ አላገኘም።

የዚህን ዜና መውጣት ተከትሎ የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል የሆኑት ክሪስ ቫን ሆለን እስራኤል ፍልስጤማውያንን ከጋዛ በማስወጣት በሌላ አገር ለማስፈር የአሜሪካንን ድጋፍ መጠየቋን ተቃውመዋል።

ሴናተር ቫን ሆለን የእስራኤል የስለላ ድርጅት ኃላፊ እና የትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ተገናኝተው በጉዳዩ ላይ መመካከራቸውን በተመለከተ የወጣውን ዘገባ ተከትሎ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ዕቅዱን የዘር ማጽዳት ድርጊት ነው ብለውታል።

"የጋዛ ነዋሪዎች ላይ በሚፈጸም የዘር ማጽዳት ተግባር ላይ የመንግሥትን እና የግብር ከፋዮችን ገንዘብ በመጠቀም አሜሪካ ተሳታፊ መሆን የለባትም። ይህንን ልንታገሰው አንችልም" ሲሉ ነው ተቃውሟቸውን ያሰፈሩት።

በአሁኑ ወቅት በረሃብ እየተሰቃዩ በሚፈጸሙ ጥቃቶች እየተገደሉ ያሉትን የጋዛ ነዋሪዎች ወደ ሌላ አገር በማዘዋወር ሰርጡን በአሜሪካ ተቆጣጣሪነት የማልማቱ ሥራ ከተለያዩ መንግሥታት እና ተቋማት ጠንካራ ተቃውሞ ገጥሞታል።

ዕቅዱን ለማስፈጸም ከፕሬዝዳንት ትራምፕ እና ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በኩል ጠንካራ ፍላጎት ቢኖርም እስካሁን ያልለየው ፍልስጤማውያኑ ወደየት ተወስደው እንደሚሰፍሩ ነው።