ኔታንያሁ ወደ አሜሪካ አቅንተው ከትራምፕ ጋር በጋዛ ጦርነት ዙሪያ ተወያዩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ማክሰኞ አመሻሽ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ተገናኝተው በጋዛ ስላለው ጦርነት ተወያይተዋል።
መሪዎቹ የተገናኙት የትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እስራኤል እና ሃማስ ለ60 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት የሚስማሙበት አንድ ቀሪ ጉዳይ እንዳላቸው ከጠቆሙ በኋላ ነው።
ኔታንያሁ ለመገናኛ ብዙኃን ክፍት ላልነበረው ስብሰባ በነጩ ቤተ መንግስት የደረሱት ማክሰኞ ምሽት 3፡00 አካባቢ ነበር።
ቀደም ብሎ ማክሰኞ ኔታንያሁ ከምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ጋር ተገናኝተዋል።
ሰኞ እለት በዋይት ሀውስ በእራት ወቅት ከትራምፕ ጋር ለረዥም ሰዓታት ተወያይተዋል።
ከትራምፕ ሁለተኛ የስልጣን ዘመን ወዲህ ኔታንያሁ ወደ አሜሪካ ሲያቀኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።
የሁለቱ መሪዎች ስብሰባ ሁለት ሰአት ያህል ፈጅቷል።
ኔታንያሁ ከሪፐብሊካን የተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ማይክ ጆንሰን ጋርም ተገናኝተዋል።
ከዚያ ስብሰባ በኋላ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር እስራኤል በጋዛ ያካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ ተጠናቋል ብለው እንደማያምኑ ነገር ግን ተደራዳሪዎች የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ "በእርግጠኝነት እየሰሩ ናቸው" ብለዋል።
"አሁንም በጋዛ ያለውን ስራ መጨረስ አለብን፤ ታጋቾቻችንን በሙሉ ማስለቀቅ እንዲሁም የሃማስን ወታደራዊ እና አስተዳደራዊ አቅም ማጥፋት እና ማውደም አለብን" ብለዋል ኔታንያሁ።
ዊትኮፍ እስራኤል እና ሃማስ ከዚህ ቀደም ከስምምነት ላይ እንዳይደርሱ በከለከሏቸው ጉዳዮች ላይ ልዩነቶቻቸውን እያጠበቡ መሆናቸውን ገልፀው፤ በዚህ ሳምንት ጊዜያዊ የ60 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንደሚደረስ ተስፋ አድርገዋል።
"አራት ጉዳዮች ነበሩን እና አሁን ወደ አንድ ደረጃ ላይ ደርሰናል" በማለት ዊትኮፍ በድርድር ላይ ስላሉት ጥብቅ ነጥቦች ተናግረዋል።
በሂደት ላይ ያለው ስምምነት በህይወት ያሉ 10 ታጋቾችን እና የ9ኙን አስከሬን መለቀቅንም ይጨምራል ብለዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሰኞ ዕለት ከትራምፕ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት የኳታር የልዑካን ቡድን ወደ ዋይት ሀውስ በመምጣት ከባለሥልጣናቱ ጋር ለብዙ ሰዓታት መነጋገራቸውን አክሲዮስ ስለውይይት የሚያውቁ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
ትራምፕ ሰኞ ማምሻውን የተኩስ አቁም ድርድር ሂደቱ "በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ' መሆኑን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ነገር ግን በድርድሩ ላይ የአሸማጋይነት ሚና የተጫወተችው ኳታር ማክሰኞ ጠዋት ለድርድር ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ገልጻለች።
የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማጅድ አል-አንሳሪ "በአሁኑ ጊዜ ምንም አይነት የጊዜ ሰሌዳ መስጠት የምችል አይመስለኝም ፣ ግን ለዚህ ጊዜ እንደሚያስፈልገን አሁን መናገር እችላለሁ" ብለዋል ።
ውይይቶቹ ማክሰኞ ከመቀጠላቸው በፊት ውይይቱን የሚያውቁ የፍልስጤም ምንጭ ምንም አይነት ጉዞ አለማድረጋቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በሃማስ እና በእስራኤል መካከል የመጨረሻው ዙር ድርድር የጀመረው እሁድ እለት ነው።















