ሐማስ ለአሜሪካ የጋዛ የተኩስ አቁም ዕቅድ 'አዎንታዊ ምላሽ ' መስጠቱን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሐማስ፤ አሜሪካ ላቀረበችው የጋዛ የተኩስ አቁም ዕቅድ "አዎንታዊ ምላሽ" ለአሸማጋዮች መስጠቱን አስታወቀ።
"ወደ ድርድሮች ወዲያውኑ ለመግባት ዝግጁ ነኝ" ብሏል ሐማስ ባወጣው መግለጫ።
ውይይቱን በቅርበት የሚያውቁ የፍልስጤም ከፍተኛ ባለስልጣን ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሐማስ አጠቃላይ ማዕቀፉን ቢቀበልም በርካታ ቁልፍ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ጠይቋል።
ከዚህም መካከል ለ20 ወራት የዘለቀውን ጦርነት በዘላቂነት ለመቋጨት የታሰበው ድርድር ካልተሳካ አሜሪካ የእስራኤል ጥቃት እንደማይቀጥል ዋስትና ልትሰጥ ይገባል የሚለው አንዱ ነው።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት በሚቀጥለው ሳምንት ሊደረስ ይችላል ሲሉ አርብ ዕለት ተናግረዋል።
ሐማስ በአሜሪካ አደራዳሪነት ለቀረበው የጋዛ የተኩስ አቁም ዕቅድ "በቀና መንፈስ" ምላሽ ሰጥቻለሁ ማለቱ መልካም መሆኑንም ትራምፕ አክለዋል።
ማክሰኞ ዕለት እስራኤል ለ60 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ዕቅድ "አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን" መቀበሏን ትራምፕ አስታውቀው ነበር።
በዚህ ወቀት እስራኤልና ሐማስ ጦርነቱን በዘላቂነት ለማስቆም እንደሚሰሩ ተገልጿል።
ትራምፕ "የመጨረሻው ዕቅድ" ሲሉ የጠሩትን ይህንን ስምምነት ሐማስ እንዲቀበል "ከዚህ የተሻለ ምንም የለም፤ የበለጠ የከፋ ይሆናል" በማለት አስጠንቅቀዋል።
በዚህም ዕቅድ መሰረት ሐማስ 10 የእስራኤል ታጋቾችን እና 18 የታጋቾች አስክሬን ለእስራኤል ሲሰጥ በምትኩ በእስራኤል እስር ቤት ያሉ ፍልስጤማውያን ይለቀቃሉ።
በጋዛ እስካሁን 50 ታጋቾች ሲኖሩ ከነዚህም ውስጥ 20ዎቹ በሕይወት እንዳሉ ይታመናል።
በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታትን እና አለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴን በማሳተፍ በቂ መጠን ያለው የሰብዓዊ እርዳታ ወዲያውኑ ወደ ጋዛ መግባት እንዲችል በስምምነት ዕቅዱ ተጠቅሷል።
ሐማስ ዕርዳታው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በአጋሮቹ ብቻ እንዲከፋፈል እና በእስራኤል እና በአሜሪካ በሚደገፈው የጋዛ ሰብዓዊ ፋውንዴሽን የሚመራው አወዛጋቢ የእርዳታ ክፍፍል በአስቸኳይ እንዲቆም መጠየቁን የፍልስጤም ከፍተኛ ባለስልጣን ገልጸዋል።
የሰብዓዊ ፋውንዴሽኑ እርዳታ ማከፋፈል ከጀመረ ጊዜ አንስቶ የእስራኤል ወታደሮች ከጣቢያዎቹ የእርዳታ እህል ለመውሰድ የተሰበሰቡ ከ400 በላይ ፍልስጤማውያንን ገድለዋል ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአገር ውስጥ ዶክተሮች ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ በበኩሉ በፋውንዴሽኑ የእርዳታ ማከፋፈያ ጣቢያዎች አቅራቢያ 509 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን እንዲሁም በእርዳታ መኪኖች አጠገብም እንዲሁም 104 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን አርብ ዕለት አስታውቋል።
ሌላው ሐማስ የጠየቀው ቁልፍ ማሻሻያ የእስራኤል ወታደሮች ከተቆጣጠሯቸው የጋዛ ግዛቶች እንዲወጡ መሆኑን እኚሁ የፍልስጤም ባለስልጣን አክለዋል።
የአሜሪካ ዕቅድ የእስራኤል ወታደሮች ከያዟቸው የሰሜን እና የደቡብ ጋዛ ይዞታዎች በምዕራፍ መውጣታቸውን ያካትታል ተብሎ ይታመናል።
ነገር ግን ባለስልጣኑ እንደሚሉት ሐማስ እስራኤል የመጨረሻው የተኩስ አቁም ስምምነት ከመፋረሱ በፊት ወደነበሩበት ስፍራ እንዲመለሱ አጥብቆ መጠየቁን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ባይሳካ እስራኤል በተቀናጀ ሁኔታ በምድር እና አየር ላይ በጋዛ የምትፈጽመውን ጥቃት እንደማትጀምር አሜሪካ ዋስትና እንድትሰጣቸው ሐማስ መጠየቁንም ባለስልጣኑ አመላክተዋል።
ሆኖም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ታጋቾች በሙሉ እስከሚለቀቁ እና የሐማስ ወታደራዊ እና አስተዳደራዊ አቅም እስኪንኮታኮት ድረስ ጦርነቱን አናቆምም ሲሉ ተደምጠዋል።
የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት እንደቀጠለ ነው።
የእስራኤል ጦር በፈጸመው ጥቃት ባለፉት 24 ሰዓታት ቢያንስ 138 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።















