"አንድ ዘገባ እንኳን መሥራት ተስኖኛል፤ ረሃቡ ያዞረኛል" የጋዛ የቢቢሲ ፍሪላንስ ዘጋቢ

የጋዛ ረሃብ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

ለቢቢሲ ከጋዛ በፍሪላንስ ዘጋቢነት የሚሠሩ ሦስት ፍልስጤማውያን ጋዜጠኞች ቤተሰቦቻቸውን መመገብ እንደተሳናቸው እና እነሱም ያለ ምግብ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ቀናትን ለማሳለፍ እንደተገዱ ይናገራሉ።

እነዚህ ፍልስጤማውያን ጋዜጠኞች ናቸው ለቢቢሲ ከጋዛ የዘገባ ሽፋን የሚሰጡት።

እነዚህ ጋዜጠኞች የቅርብ ዘመዶቻቸው በእስራኤል ጥቃት በተገደሉበት ወቅት፣ መኖሪያ ቤታቸው በጥቃት በፈረሰበት ወቅት ወይም ከእስራኤል ጥቃት ለማምለጥ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሚሸሹበት ወቅት እንኳን ካሜራዎቻቸውን አልሰቀሉም።

ፎቶዎችን ያነሳሉ፣ አስፈላጊ የሚባሉ ቪዲዮዎችን ለቢቢሲ ይልካሉ፤ ታሪክን ይመዘግባሉ።

የእስራኤል ጦር በጋዛ ጦርነት 200 የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ጋዜጠኞችን ገድሏል።

አንደኛው የቢቢሲ ፍሪላንስ ጋዜጠኛ ቀደም ሲል በሥራ ላይ እያለ በእስራኤል የቦምብ ጥቃት የከፋ ጉዳት ደርሶበት ነበር።

ነገር ግን የአሁኑ ወቅት "ከተወለድኩበት ጊዜ ጀምሮ ካሳለፍኳው በጣም ፈታኙ ወቅት ነው። የስቃይ፣ የማጣት ታላቁ ቀውስ ነው" ይላል።

የዓለም የምግብ ዋስትና ባለሙያዎች በጋዛ ያለውን ሁኔታ ረሃብ ተከስቷል በሚል ባይፈርጁትም፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች ሰው ሰራሽ፣ የጅምላ ረሃብ እየተከሰተ ስለመሆኑ አስጠንቅቀዋል።

ኤጀንሲዎቹ ለረሃቡ ወደ ጋዛ የሚገቡ እርዳታዎችን እና የሸቀጥ ፍጆታዎችን የምትቆጣጠረው እስራኤልን ተጠያቂ ቢያደርጉም እስራኤል ግን ኃላፊነቱን አልተቀበለችም።

ቢቢሲ ለደኅንነታቸው በማሰብ የጋዜጠኞቹን ስም ከመጥቀስ ተቆጥቧል።

ጋዜጠኞቹ በተለይም የሚወዷቸው ትንንሽ ልጆቻቸውን መመገብ አለመቻል የበለጠ መከራ እንደሆነባቸው ያስረዳሉ።

"ልጄ የኦቲዝም ተጠቂ ነው እናም በዙሪያው የሚከናወነውን ነገር አያውቅም። ጦርነት ውስጥ መሆናችንን አያውቅም፤ እናም አይናገርም" ይላል በጋዛ ከተማ የአራት ልጆች አባት የሆነው የቢቢሲ ፍሪላንስ የካሜራ ባለሙያ።

"በቅርብ ቀናት ውስጥ በጣም ስለራበው ምግብ እንደሚፈልግ ለማሳየት ሆዱን በእጁ መምታት ጀምሯል" ይላል።

በደቡባዊ ጋዛ ነዋሪ የሆነው ከሌሎቹ ትንሹ የቢቢሲ ጋዜጠኛ በበኩሉ ወላጆቹን፣ ወንድሞቹ እና እህቶቹን አስተዳዳሪ ነው።

"ለቤተሰቤ ምግብ እንዴት ማግኘት እንደምችል ያለማቋረጥ አስባለሁ" የሚለው ጋዜጠኛ "የ13 ዓመቷ ታናሽ እህቴ ምግብ እና ውሃ ትጠይቃለች ልናገኝላት አልቻልንም" ይላል።

በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያን ጋዜጠኞች ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን መመገብ የማይችሉበት የከፋ ሁኔታ ላይ መድረሳቸውን ቢቢሲ እና ሦስት የዜና ኤጀንሲዎች አስጠንቅቀው መግለጫ አውጥተዋል።

የፍልስጤም ጋዜጠኞች በጋዛ ምድር ላይ እየሆነ ላለው ነገር የዓለም አይን እና ጆሮ ሆነው ቆይተዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የፍልስጤም ጋዜጠኞች በጋዛ ምድር ላይ እየሆነ ላለው ነገር የዓለም አይን እና ጆሮ ሆነው ቆይተዋል

እስራኤል በጋዛ እያደረሰችውን ያለውን የማያባራ ጥቃት እየዘገቡ ያሉ ፍልስጤማውያን ጋዜጠኞች ለረሃብ "ከቀረው ፍልስጤማውያን ጋር በከፋ ሁኔታ መጋለጣቸውን" ቢቢሲ፣ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፣ አሶሺዬትድ ፕሬስ እና ሮይተርስ በጋራ ባወጡት መግለጫ አትተዋል።

ሚዲያዎቹ "ለበርካታ ወራት እነዚህ ነጻ ጋዜጠኞች በጋዛ ምድር ላይ እየሆነ ላለው ነገር የዓለም ዓይን እና ጆሮ ሆነው ቆይተዋል" ብለዋል በመግለጫቸው።

በርካታ መከራዎችን ተቋቁመው እየሠሩ ያሉ ጋዜጠኞች ረሃብ መጨመሩ ዘገባዎችን ለመሥራት ፈታኝ እንዳደረገባቸው ነው የሚገልጹት።

"ሁልጊዜም መዛል እና በከፍተኛ ሁኔታ ይደከመኛል። ያዞረኛል እንዲሁም መሬት ላይ የሚጥለኝ ስሜት ይሰማኛል" ይላል በጋዛ ከተማ ለቢቢሲ የፍሪላንስ ዘጋቢ የሆነው አንጋፋው ጋዜጠኛ።

ከእሱ በተጨማሪም ከሁለት ዓመት እስከ 16 ዕድሜያቸው የሆኑ አምስት ልጆችን፣ እናቱንና እና እህቶቹንም መመገብ የእሱ ኃላፊነት ነው።

ጋዜጠኛው 21 ወራት ባስቆጠረው የጋዛ ጦርነት 30 ኪሎ ግራም ቀንሷል።

"ብዙ የዜና ዘገባዎችን በከፍተኛ ፍጥነት ነበር የምጨርሰው አሁን ግን በጤናዬ እና በተጫነኝ የሥነ ልቦና ሁኔታ የምሥራው ቀስ ብዬ ነው" ይላል።

አክሎም "ግራ መጋባት እና ከፍተኛ ድካም ተጫጭኖኛል" ይላል።

ከእስራኤል ጥቃት ለማምለጥ የምትሞክር ህጻን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የደቡባዊ ጋዛ የቢቢሲ ካሜራ ባለሙያ ደግሞ "የሚሰማኝን ስሜት በቃላት መግለጽ ተስኖኛል" ሲል ያስረዳል።

"ሆዴ በረሃብ ሲላወስ ይሰማኛል፤ ራስ ህመም አለኝ እንዲሁም መንምኜያለሁ። ደካማ ሆኛለሁ፤ ከጥዋቱ እስከ ምሽት አራት ሰዓት ድረስ እሠራ ነበር። አሁን ግን አንድ ዘገባ መሥራት ተስኖኛል። ረሃቡ ያዞረኛል" ይላል።

በቅርብ ቀናት ውስጥ እየቀረጸ እያለ ራሱን ስቶ የወደቀ ቢሆንም ከሳምንት በኋላ ሥራውን ጀምሯል።

በጦርነት ወቅት የምግብ እጥረት ማጋጠም በተደጋጋሚ የሚያጋጥም ችግር ቢሆንም ቀደም ሲል በነበሩ ጊዜያት ከውጭ ደመወዛቸውን የሚያገኙ ገበያዎች ላይ ሄደው መሠረታዊ ፍጆታዎችን በማይቀመስ ዋጋም ቢሆን መሸመት ይችሉ ነበር።

በአሁኑ ወቅት ገበያዎች በአብዛኛው ባዶ ሆነዋል።

"በአሁኑ ወቅት ኪችን ከተሰኘው በጎ አድራጎት ድርጅት ምግብ የመቀበል ደረጃ ላይ ደርሻለሁ። ይህም ማለት ልጆቼ ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ውስን የሆኑ እንደ ምስር፣ ሩዝ እና ፓስታ መመገብ ይችሉ ነበር" ይላል የአራት ትንንሽ ልጆች አባት የሆነው የጋዛው ጋዜጠኛ።

ሁለቱ ጋዜጠኞች ረሃባቸውን ለመግታት ውሃ ከትንሽ ጨው ጋር ቀላቅለው መጠጣት መጀመራቸውን ይናገራሉ።

አንደኛው ጋዜጠኛ ደግሞ ለዕለት ምግቡ 50 ግራም ብስኩት በዘጠኝ ዶላር (1 ሺህ 241 ብር ገደማ) ይገዛል። በጋዛ ገንዘብ ማግኘት በራሱ ከባድ ፈተና ሆኗል።

ባንኮች በተዘጉባት ጋዛ በአሁኑ ወቅት ገንዘብ ለማግኘት በነጋዴዎች በኩል ማለፍ ግዴታ ሆኗል።

"ጥሬ ገንዘብ ብፈልግ ብዙ ጊዜ አላገኝም። ነገር ግን ሲገኝ 45 በመቶ የማውጫ ክፍያ ከፍዬ ነው ገንዘቤን የማገኘው" ይላል አንደኛው የጋዛ ከተማ የካሜራ ባለሙያ።

"አንድ ሺህ ዶላር ለማውጣት ከሄድኩኝ የማገኘው 550 ዶላር ነው። አጠቃላይ ሂደቱ አድካሚ ነው፤ ሁሉም ሻጮች ጥሬ ገንዘብ ይፈልጋሉ" ይላል።

"ችግሩ የመጣው በባንኮች መዘጋት ምክንያት ነው። እንደነዚህ ዓይነት የገንዘብ ዝውውሮች ከረሃባችን በተጨማሪ ሌላ የስቃይ መንስዔ ሆነዋል" ይላል በደቡባዊ ጋዛ ያለው የቢቢሲ የሥራ ባልደረባ።

ቀደም ባሉ ጊዜያት እንደ እኔ ላሉ በእስራኤል ዕውቅና የተሰጣቸው የቢቢሲ ጋዜጠኞች በጦርነት ጊዜም ቢሆን ወደ ጋዛ አዘውትረው በመሄድ መዘገብ ይችሉ ነበር።

ነገር ግን 21 ወራት ባስቆጠረው የጋዛ ጦርነት የራፋህ መሸጋገሪያ ክፍት በነበረበት ወቅት እንኳን እስራኤል ከግብፅ ጋር በመሆን የውጭ አገር ጋዜጠኞች ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዳይገቡ ከልክላለች።

ፍቃድ የተገኘው በእስራኤል ጦር ታጅበው ለገቡ ጋዜጠኞች ብቻ ነው።

በጋዛ ከተማ በእስራኤል ጥቃት የተገደለ ጋዜጠኛ ቀብር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ጦር በጋዛ ጦርነት 200 የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ጋዜጠኞችን ገድሏል

ቢቢሲ እና ሌሎች የዜና ወኪሎች በጋራ ባወጡት መግለጫ "የእስራኤል ባለሥልጣናት ጋዛ ውስጥ ጋዜጠኞች እንዲገቡ እንዲፈቅዱ በድጋሚ እናሳስባለን" ብለዋል።

በዚህ ሳምንት ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ 28 አገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ "የጋዛ ጦርነት አሁን መቋጨት አለበት" ብለዋል።

አገራቱ እስራኤል በዓለም አቀፍ ሕግ የተጣለባትን ግዴታ እንድትወጣና እርዳታ "በጠብታ" እንዲገባ የምታደርገውን አካሄድ እንድታቆም ጠይቀዋል።

ረቡዕ ዕለት ከ100 በላይ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በበኩላቸው "የምግብ ፍጆታዎች አቅርቦቶች በሙሉ እየተሟጠጡ የረድዔት ድርጅቶች የራሳቸው ሠራተኞች ሲረግፉ ዓይናቸው እያየ ነው" ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ ኮሚሽነር ጄነራል ፊሊፔ ላዛሪኒ ሐሙስ ዕለት በሰጡት መግለጫ "ከ100 በላይ የሚሆኑ ፍልስጤማውያን አብዛኞቹ ሕጻናት በረሃብ መሞታቸው ሪፖርት መደረጉን" ጠቅሰዋል።

"ሕጻናት መንምነው አጥንታቸው እያገጠጠ መሆኑን ቡድናችን እየተመለከተ ነው። ሕጻናቱ አቅማቸው እየደከመ እና የሚያስፈልጋቸውን ምግብ እና ሕክምና ካላገኙ በከፍተኛ ሁኔታ ለሞት ይጋለጣሉ" ያሉት ላዛሪኒ እስራኤል "የሰብዓዊ አጋሮች ያልተገደበ እና ያልተቆራረጠ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲያስገቡ እንድትፈቅድ" ተማጽነዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች "በሥራ ላይ እያሉ በረሃብ ተዳክመው ራሳቸውን እየሳቱ ነው" ሲሉ የተናገሩት ላዛሪኒ አክለውም "እርዳታ በመስጠት ላይ የተሰማሩ በቂ ምግብ ማጣት አጠቃላይ የሰብዓዊነት ሥርዓቱ መፈራረሱ ማሳያ ነው" ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ አንድ አራተኛው የጋዛ ሕዝብ በረሃብ እየተፈተነ መሆኑን ባደረገው ግምገማ ገልጿል።

"የጅምላ ረሃብ ከማለት ውጪ ሌላ ምን እንደምትሉት አላውቅም፤ ይህም በሰው ሠራሽ ምክንያት የተፈጠረ ነው" ሲሉ የተቋሙ ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ገብረ ኢየሱስ ረቡዕ ዕለት ተናግረዋል።

"ይህም መንስዔው በጣም ግልጽ ነው፤ በእገዳው ምክንያት ነው" ብለዋል።

የጋዛ ረሃብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የመገናኛ ብዙኃኑ በበኩላቸው "ጋዜጠኞች በጦርነት ቀጣና ውስጥ በርካታ ፈተናዎች እና መከራዎችን ይቋቋማሉ። የረሃብ ስጋት ከእነዚህ ውስጥ አንዱ መሆኑ በጣም አሳሳቢ ነው" ሲሉ በመግለጫቸው አትተዋል።

በአሁኑ ወቅት የቢቢሲ ጋዜጠኞች ሕዝባቸው እያለፈበትን ያለውን መከራ ለዓለም ለመንገር ያለባቸውን ኃላፊነት ለራሳቸውን እንዲሁም ለቤተሰቦቻቸውን ምግብ መፈለግ ጋር ተደማምሮ እያንዳንዷን ቀን ፈታኝ አድርጓታል።

"በአሁኑ ጊዜ ያለው ሁኔታ አስከፊ ነው። ረሃብ በየቤቱ ገብቷል። የሞት ፍርድ ያህል ነው" ብሏል አንደኛው ጋዜጠኛ።

እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን እርዳታ እንዳይደርሳቸው ከመጋቢት ጀምሮ ሙሉ እገዳ ጥላለች። ለሁለት ወራት የቆየው የተኩስ አቁም መፍረሱን ተከትሎ በጋዛ የማያባራ ጥቃት እያካሄደች ነው።

የእስራኤል ጦር ይሄንን ሁሉ የሚያደርገው ሐማስ የቀሩ ታጋቾችን እንዲለቅ ጫና ለማድረግ ነው ይላል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጋዛ ረሃብ እያንዣበበ ነው የሚል ማስጠንቀቂያ በተደጋጋሚ ማሰማቱን ተከትሎ እገዳው በከፊል ቢላላም አሁንም ፍልስጤማውያኑ በከፍተኛ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የነዳጅ እጥረት እየተፈተኑ ነው።

ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተወሰኑ የእርዳታ መኪኖች በተጨማሪ፤ እስራኤል እና አሜሪካ ለፍልስጤማውያን እርዳታ እናከፋፍላለን በሚል 'የጋዛ ሂውማኒታሪያን ፋውንዴሽን' (ጂኤችኤፍ) የተሰኘ አወዛጋቢ ድርጅት አቋቁመዋል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እርዳታ ሲጠባበቁ ባሉ ፍልስጤማውያን ላይ በየቀኑ በሚባል ሁኔታ የእስራኤል ጦር በሚከፍተው ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።

በባለፉት ሁለት ወራት የእስራኤል ጦር በእርዳታ ጠባቂ ፍልስጤማውያን ላይ በከፈተው ተኩስ ከ1,000 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ አስታውቋል።

ከእነዚህ ውስጥም 766 ግድያዎች የተፈጸሙት በጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽን ግቢ ውስጥ ነው።

ቀሪዎቹ 288 ፍልስጤማውያን ደግሞ የተገደሉት የተፈጸሙት በተባበሩት መንግሥታት እና በሌሎች የእርዳታ መኪኖች አቅራቢያ ነው።