በጋዛ ከ100 በላይ ፍልስጤማውያን አብዛኞቹ ህጻናት በረሃብ መሞታቸውን ሪፖርት መደረጉን ተመድ አስታወቀ

በጋዛ የተራቡ ህጻናት

በጋዛ ከ100 በላይ ፍልስጤማውያን አብዛኞቹ ህጻናት በረሃብ መሞታቸውን ሪፖርት መደረጉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።

በጋዛ ከአምስት ህጻናት አንዱ በምግብ እጥረት እንደሚሰቃይ እና ሁኔታዎች እየከፉ መሆኑንም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ ገልጿል።

የኤጀንሲው ኮሚሽነር ጄኔራል ፊሊፔ ላዛሪኒ ሐሙስ ዕለት "በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያን በሞት እና በህይወት መካከል ናቸው። በሞት ጥላ ስር ያሉ ናቸው" ሲል አንድ የስራ ባልደረባቸውን ዋቢ አድርገው በመግለጫው ተናግረዋል።

ከ100 በላይ አለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በጋዛ የፍልስጤም ህዝብ በከፋ ረሃብ እንደሚመታ አስጠንቅቀው መንግሥታት እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል።

ወደ ጋዛ የሚገቡ እርዳታዎችን እና የሸቀጥ ፍጆታዎችን የምትቆጣጠረው እስራኤል" ምንም አይነት ከበባ የለም "ስትል "ለምግብ እጥረቱ ሃማስን" ተጠያቂ አድርጋለች።

ሆኖም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ ወደ ጋዛ የሚደርሰው እርዳታ "ጠብታ" እንደሆነ ገልጾ በግዛቲቱ ያለው የረሃብ ቀውስ በእንዲህ አይነት መጠን አስከፊ ሆኖ አያውቅም ሲል አስጠንቅቋል።

ላዛሪኒ ሐሙስ ዕለት በሰጡት መግለጫ ከ100 በላይ የሚሆኑ ፍልስጤማውያን አብዛኞቹ ህጻናት በረሃብ መሞታቸው ሪፖርት መደረጉን" ጠቅሰዋል።

"ህጻናት መንምነው አጥንታቸው እየገጠጠ መሆናቸውን ቡድናችን እየተመለከተ ነው። ህጻናቱ አቅማቸው እየደከመ እና የሚያስፈልጋቸውን ምግብ እና ህክምና ካላገኙ በከፍተኛ ሁኔታ ለሞት ይጋለጣሉ" ያሉት ላዛሪኒ እስራኤል "የሰብዓዊ አጋሮች ያልተገደበ እና ያልተቆራረጠ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲያስገቡ እንድትፈቅድ" ተማጽነዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰራተኞች "በስራ ላይ እያሉ በረሃብ ተዳክመው ራሳቸውን እየሳቱ ነው" ሲሉ የተናገሩት ላዛሪኒ አክለውም " እርዳታ በመስጠት ላይ የተሰማሩ በቂ ምግብ ማጣት አጠቃላይ የሰብዓዊነት ስርዓቱ መፈራረሱ ማሳያ ነው" ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት አንድ አራተኛው የጋዛ ህዝብ በረሃብ እየተፈተነ መሆኑን ባደረገው ግምገማ ገልጿል።

"የጅምላ ረሃብ ከማለት ውጭ ሌላ ምን እንደምትሉት አላውቅም፤ ይህም በሰው ሰራሽ ምክንያት የተፈጠረ ነው" ሲሉ የተቋሙ ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ገብረ እየሱስ ረቡዕ ዕለት ተናግረዋል።

"ይህም መንስዔው በጣም ግልጽ ነው፤ በእገዳው ምክንያት ነው" ብለዋል።

በሰሜናዊ ጋዛ ነዋሪ የሆነችው ሃና አልማድሁን ገበያዎች ምግብም ሆነ ሌሎች ፍጆታዎች አቅርቦት እንደሌላቸው ትናገራለች።

"ድንገት ከተገኘም በማይቀመስ ዋጋ ነው" ስትል ለቢቢሲ ገልጻለች።

ዱቄት ከመወደዱ የተነሳ ሰዎች ለመግዛት ሲሉ "ወርቅ እና የግል ንብረቶቻቸውን" መሸጣቸውን ትናገራለች።

የሶስት ልጆች እናት የሆነችው ሃና "ህጻናት ምግብ ለማግኘት የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች ውስጥ ሲፈልጉ" በዓይኗ ማየቷን ትናገራለች።

እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን እርዳታ እንዳይደርሳቸው ከመጋቢት ጀምሮ ሙሉ እገዳ ጥላለች። ለሁለት ወራት የቆየው የተኩስ አቁም መፍረሱን ተከትሎ በጋዛ የማያባራ ጥቃት እያካሄደች ነው።

የእስራኤል ጦር ይሄንን ሁሉ የሚያደርገው ሐማስ የቀሩ ታጋቾችን እንዲለቅ ጫና ለማድረግ ነው ይላል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጋዛ ረሃብ እያንዣበበ ነው የሚል ማስጠንቀቂያ በተደጋጋሚ ማሰማቱን ተከትሎ እገዳው በከፊል ቢላላም አሁንም ፍልስጤማውያኑ በከፍተኛ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የነዳጅ እጥረት እየተፈተኑ ነው።

ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተወሰኑ የእርዳታ መኪኖች በተጨማሪ፤ እስራኤል እና አሜሪካ ለፍልስጤማውያን እርዳታ እናከፋፍላለን በሚል 'የጋዛ ሂውማኒታሪያን ፋውንዴሽን' (ጂኤችኤፍ) የተሰኘ አወዛጋቢ ተቋም አቋቁመዋል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እርዳታ ሲጠባበቁ ባሉ ፍልስጤማውያን ላይ በየቀኑ በሚባል ሁኔታ የእስራኤል ጦር በሚከፍተው ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።

በባለፉት ሁለት ወራት የእስራኤል ጦር በእርዳታ ጠባቂ ፍልስጤማውያን ላይ በከፈተው ተኩስ ከ1,000 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ አስታውቋል።

ከእነዚህ ውስጥም 766 ግድያዎች የተፈጸሙት በጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽን ግቢ ውስጥ ነው።

ቀሪዎቹ 288 ፍልስጤማውያን ደግሞ የተገደሉት የተፈጸሙት በተባበሩት መንግሥታት እና በሌሎች የእርዳታ መኪኖች አቅራቢያ ነው።