"ልጆች ነበሩ"- እርዳታ እየተጠባበቁ በእስራኤል ጥቃት ልጆቿ የተገደሉባት ፍልስጤማዊት እናት

በእስራኤል ጥቃት ሁለት ልጆቿ የተገደሉባት ኢማን አል ኑሪ
የምስሉ መግለጫ, በእስራኤል ጥቃት ሁለት ልጆቿ የተገደሉባት ኢማን አል ኑሪ

እስራኤል የማያባራ ጥቃት በምትፈጽምባት ጋዛ የኢማን አል ኑሪ ትንሹ ልጅ ሲራጅ እያለቀሰ ነበር ከእንቅልፉ የነቃው።

ረሃብ ትንሿን ሆዱን ሞርሙሮት ነበር ያለቀሰው።

ከተነሳም በኋላ ሲራጅ የምግብ ማሟያ (ኒውትሪሽናል ሰፕልመንት) እንዲሰጠው ጠየቀ።

የሲራጅ የአጎት ልጅ የ14 ዓመቷ ሳማ ሲራጅን እንዲሁም ሁለቱን ታላላቅ ወንድሞቹን፤ የዘጠኝ ዓመቱን ኦማር እና የአምስት አመቱ አሚርን የምግብ ማሟያ ወደሚቀበሉበት ስፍራ እወስዳቸዋለሁ አለች።

ሐሙስ፣ ሐምሌ 3/2017 ዓ.ም. ሳማ ልጆቹን ይዛ በመካከለኛው ጋዛ፣ ዴይር አል ባላህ ከተማ አልታያራ የጤና ክሊኒክ ወሰደቸቻው።

ሲደርሱም "የጤና ማዕከሉ ተዘግቶ ስለነበር የእግረኛ መንገድ ላይ ቁጭ ብለው መጠበቅ ጀመሩ። ወዲያውኑ በድንገት የጥቃት ድምጽ ሰማን" ስትል ኢማን ለቢቢሲ ለሚሠራ የጋዛ ጋዜጠኛ ተናግራለች።

"ሃቲም! ወደ ባለቤቴም ሄጄ ልጆችህ ወደ ማዕከሉ ሄደዋል አልኩት።"

በእስራኤል ጥቃት የተገደለው የአምስት አመቱ አሚር

የፎቶው ባለመብት, Family handout

የምስሉ መግለጫ, በእስራኤል ጥቃት የተገደለው የአምስት ዓመቱ አሚር

ማስጠንቀቂያ፦ ይህ ጽሁፍ የህጻናትን ግድያ ሥዕላዊ መግለጫዎችን ይዟል

የአምስት ልጆች እናት የሆነችው የ32 ዓመቷ ኢማን የእስራኤል ጥቃት ወደተፈጸመበት ስፍራ እየተጣደፈች ሄደች።

ስፍራው ላይ ስትደርስ ልጆቿ እና የእህቷ ልጅ በጋሪ ላይ ተንጋለው አየቻቸው።

በጋዛ አምቡላንሶች ባለመኖሩ እስራኤል በምትፈጽማቸው ጥቃቶች የሚገደሉ ወይም የሚጎዱ ሰዎችን ወደ ሆስፒታል ለማጓጓዝ በአህያ የሚጎተት ጋሪን ይጠቀማሉ።

አሚር እና ሳማ ሲገደሉ፤ ኦማር እና ሲራጅ ደግሞ በጸና ቆሰሉ።

"ኦማር ትንሽ እስትንፋስ ነበረው። ሊያስነሱት ሞከሩ" ትላለች ኢማን።

"ኦማር ደም ያስፈልገው ነበር፤ እናም ለማግኘት አንድ ሰዓት ወሰደባቸው። ደም ቢሰጡትም ከንቱ ነበር። ሞተ" ትላለች እናት።

"ለምን ሞቱ? ለምን? ምን አጠፉ?" ስትል በሐዘን የተሰበረችው እናት ትጠይቃለች።

"በዓለም ላይ እንዳሉ ሌሎች ልጆች ህልሞች ነበራቸው። አሻንጉሊት ከሰጠሃቸው በጣም ያስደስታቸዋል። ገና ልጆች ነበሩ" ብላለች።

በእስራኤል ጥቃት የተገደለው የዘጠኝ አመቱ ኦማር (በቀኝ በኩል) ከታላቅ ወንድሙ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Family handout

የምስሉ መግለጫ, በእስራኤል ጥቃት የተገደለው የዘጠኝ አመቱ ኦማር (በቀኝ በኩል) ከታላቅ ወንድሙ ጋር

የሁለት ዓመት ልጇ በተፈጸመበት ጥቃት ዓይኑ እንደጠፋ እና ከጭንቅላቱ ደም እየፈሰሰው የነበረ ሲሆን፣ ይህንን አሰቃቂ ምሥል ከጭንቅላቷ በፍጹም ማውጣት አልቻለችም።

"ጭንቅላቱ እንደተሰበረ፤ ከጭንቅላቱ ደም መፍሰስ ብቻ ሳይሆን በአንጎሉ ውስጥ ከፍተኛ ደም መፍስስ ተከስቷል ሲል ዶክተሩ ነገረን" ትላለች።

በጽኑ ሕመም ውስጥ ያለው የሁለት ዓመቱ ሲራጅ "በኦክስጅን እየታገዘ እስከ መቼ እንደዚህ ሊቆይ ይችላል? ሁለቱ ተገድለዋል። ምነው ይሄኛውን አምላክ ትንሽ እንዲቆይ ቢረዳኝ" ስትል በሐዘን የተሰበረችው እናት አምላኳን ትማጸናለች።

በሚያሳዝን ሁኔታ ዶክተሮች ሲራጅን ማከም እንደማይችሉ ተናግረዋል።

"ከትናንት ጀምሮ እስከ ዛሬ አንድ ሰዓት [ቅዳሜ ሐምሌ 5/ 2017] በተመሳሳይ የጤና ሁኔታ ላይ ነው። አሁንም እየተነፈሰ ነው። ደረቱ ወደ ላይ ከፍና ዝቅ ይላል፤ አሁንም እስትንፋስ አለው፤ አድኑት" ስትል እናት ተማጽናለች።

በእስራኤል ጥቃት በጽኑ ቆስሎ በህክምና ላይ የሚገኘው የሁለት ዓመቱ ሲራጅ

የፎቶው ባለመብት, Family handout

የምስሉ መግለጫ, በእስራኤል ጥቃት በጽኑ ቆስሎ በሕክምና ላይ የሚገኘው የሁለት ዓመቱ ሲራጅ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአልታያራ ክሊኒክን የሚያስተዳድረው 'ፕሮጄክት ሆፕ' የተሰኘው የአሜሪካ የእርዳታ ቡድን ቃል አቀባይ ጥቃቱ ሐሙስ፣ ሐምሌ 3/2015 ዓ.ም. ከጠዋቱ 1፡15 መፈጸሙን አስታውቋል።

ክሊኒኩ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ሲሆን የሚከፈተው የሥነ ምግብ እና ሌሎች ጤና አገልግሎቶችን በቅድሚያ ለማግኘት ሴቶች እና እናቶች ተሰልፈው ውጪ ሆነው እየተጠባበቁ እንደነበር ቃል አቀባዩ ዶክተር ሚትቃል አቡጠሃ ገልጸዋል።

የእስራኤል የአየር ጥቃትን የሚያሳይ የደኅንነት ካሜራ ምሥል ሴቶቹ እና ሕጻናት ከሚጠብቁበት በጥቂት ሜትሮች ራቅ ብሎ ሁለት ወንዶች መንገድ ላይ ሲራመዱ ይታያል።

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ከግለሰቦቹ አጠገብ ፍንዳታ የተሰማ ሲሆን፣ አየሩም በአቧራ እና በጪስ ተሞላ።

ከሆስፒታሉ የተገኘው ቪዲዮ የበርካታ ሕጻናት አስክሬኖች ወለል ላይ ተዘርግተው፤ እንዲሁም ሌሎች የቆሰሉ በርካቶችንም የሕክምና ባለሙያዎች እርዳታ ሲያደርጉላቸው አሳይተዋል።

"እባካችሁ ለልጄ አምቡላንስ ጥሩልኝ" የምትል እናት ሕጻን ልጇን በሕይወት ለማቆየት ስትታገል ትታያለች። በርካቶች ግን እርዳታ ሳይደርስላቸው ሕይወታቸው ተቀጥፏል።

ዶክተር አቡጠሃ እንደሚሉ በዚህ የእስራኤል ጥቃት አስር ሕጻናት እና ሦስት ሴቶችን ጨምሮ 16 ሰዎች ተገድለዋል።

የእስራኤል ጦር ጥቃቱ በአካባቢው "የሐማስ አሸባሪ" ላይ ያነጣጠረ ነው ብሏል።

"ተሳትፎ በሌላቸው ግለሰቦች ላይ ለሚደርሱ ማንኛውም ጉዳቶች ማዘኑን" ገልጾ፤ ጥቃቱ እየተገመገመ ነው ብሏል።

ፕሮጀክት ሆፕ በበኩሉ ጥቃቱ "የዓለም አቀፉን የሰብዓዊነት ሕግ በግልጽ የጣሰ እና በጋዛ ውስጥ ማንኛውም ሰው ሆነ የትኛውም ቦታ ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዳልሆነ የሚያሳይ በመሆኑ የሚያሳስብ ነው" ብሏል።

"መሠረታዊ እና ሰብዓዊ ፍጆታዎችን ለማግኘት እየጠበቁ ያሉ ሰዎችን መገደል መቀበል" የማይችሉት እንደሆነ ዶክተር አቡጠሃ ተናግረዋል።

የእስራኤል ጦር ጥቃቱን አስመልክቶ የሰጠውን መግለጫ የተቹት ዶክተሩ "እነዚህን ታካሚዎች፣ እነዚህን ሰዎች ወደ ሕይወት መመለስ አይችልም" ብለዋል።

ክሊኒኩ በተባበሩት መንግሥታት ዕውቅና ያለውና "ከግጭት ውጪ የሆነ ሰብዓዊ አገልግሎት መስጫ ተቋም" አንደሆነ ገልጸው፤ በአካባቢው ምንም ዓይነት ወታደራዊ እርምጃዎች መወሰድ እንደሌለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢማን እሷም ሆነ ባለቤቷ ልጆቻቸውን መመገብ ስላልቻሉ ልጆቿ በየሁለት እና ሦስት ቀናት ልዩነት ወደ ክሊኒኩ በመሄድ የምግብ ማሟያ (ኒውትሪሽን ሰፕልመንት) ይቀበሉ እንደነበር ትናገራለች።

"አባታቸው ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ ዱቄት ያመጣላቸዋል። ኔትዛሪም ወደተሰኘችው ስፍራ ሁልጊዜም ሲሄድ ልቤ ይሰበራል። ከዚያም ምግብ ወይም ዱቄት ያመጣላቸዋል" ትላለች።

አክላም "እዚህ ምንም የለንም፤ ምንም ምግብ የለንም። ልጆች አንድ ነገር ካልፈለጉ ለምንስ ያለቅሳሉ?" ስትል እናት ትጠይቃለች።

እርዳታ እየተጠባበቁ ያሉ ፍልስጤማውያን

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እርዳታ እየተጠባበቁ ያሉ ፍልስጤማውያን

እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን እርዳታ እንዳይደርሳቸው ከመጋቢት ጀምሮ ሙሉ እገዳ ጥላለች። ለሁለት ወራት የቆየው የተኩስ አቁም መፍረሱን ተከትሎ በጋዛ የማያባራ ጥቃት እያካሄደች ነው።

የእስራኤል ጦር ይሄንን ሁሉ የሚያደርገው ሐማስ የቀሩ ታጋቾችን እንዲለቅ ጫና ለማድረግ ነው ይላል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጋዛ ረሃብ እያንዣበበ ነው የሚል ማስጠንቀቂያ በተደጋጋሚ ማሰማቱን ተከትሎ እገዳው በከፊል ቢላላም አሁንም ፍልስጤማውያኑ በከፍተኛ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የነዳጅ እጥረት እየተፈተኑ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ (ኡንርዋ) በሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል ብሏል።

በየቀኑም ይህ ቁጥር እየጨመረ እንደሆነም ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ዶክተር አቡጠሃ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በጋዛ ያላስተዋሉትን በአዋቂዎች ላይ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተቋማቸው ፕሮጀክት ሆፕ ማስተዋሉን ገልጸዋል።

ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተወሰኑ የእርዳታ መኪኖች በተጨማሪ፤ እስራኤል እና አሜሪካ ለፍልስጤማውያን እርዳታ እናከፋፍላለን በሚል 'የጋዛ ሂውማኒታሪያን ፋውንዴሽን' (ጂኤችኤፍ) የተሰኘ አወዛጋቢ ተቋም አቋቁመዋል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እርዳታ ሲጠባበቁ ባሉ ፍልስጤማውያን ላይ በየቀኑ በሚባል ሁኔታ የእስራኤል ጦር በሚከፍተው ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።

እስካሁን ድረስ የእስራኤል ጦር በእርዳታ ጠባቂ ፍልስጤማውያን ላይ በከፈተው ተኩስ 798 ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ አርብ ዕለት አስታውቋል።

ከእነዚህ ውስጥም 615 ግድያዎች የተፈጸሙት በጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽን ግቢ ውስጥ ነው።

ፋውንዴሽኑን የሚያስተዳድረው የአሜሪካ የግል የጥበቃ ቡድን ሲሆኑ ማዕከላቱ የሚገኙትም በደቡብ እና መከካከለኛው ጋዛ ወታደራዊ ቀጣናዎች ውስጥ ነው።

ሌሎች 183 ግድያዎች ደግሞ የተፈጸሙት በተባበሩት መንግሥታት እና በሌሎች የእርዳታ መኪኖች አቅራቢያ ነው።

ሁለት ልጆቿ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉባት ኢማን ከቀሪዎቹ ቤተሰቦቿ ጋር
የምስሉ መግለጫ, ሁለት ልጆቿ በእስራኤል ጥቃት የተገደሉባት ኢማን ከቀሪዎቹ ቤተሰቦቿ ጋር

የእስራኤል ጦር በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳቶች መድረሳቸውን አምኖ "በተቻለ መጠን በሕዝቡ እና [በእስራኤል] ጦሩ መካከል ሊኖር የሚችለውን ውጥረት ለመቀነስ እየሠራ መሆኑን" ተናግሯል።

ፋውንዴሽኑ በበኩሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሐማስ የሚመራውን የጤና ሚኒስቴር "ሐሰተኛ እና አሳሳች" አሐዝን ይጠቀማል ሲል ወንጅሏል።

ዶክተር አቡጣሃ "ሁሉም ሰው ሰብዓዊነቱ በተከበረ ሁኔታ ሕይወቱን እንዲመራ"፤ በጋዛ ውስጥ ላሉ ፍልስጤማውያን መሠረታዊ ሰብዓዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት በቂ ምግብ፣ መድኃኒት እና ነዳጅ እንዲገባ እስራኤል እንድትፈቅድ ጠይቀዋል።

እስራኤል እና ሐማስ በቅርቡ የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ሊደርሱ ይችላሉ በሚል "ሐሰተኛ ተስፋ" በርካቶች እምነታቸውን መጣላቸውን ስጋት እንዳሳደረባቸው ዶክተሩ ገልጸዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሐሙስ ዕለት ለ60 ቀናት የሚቆይ የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት በቀናት ውስጥ ሊደረስ እንደሚችል ተናግረው ነበር።

ነገር ግን በኳታር፣ ዶሃ እየተደረጉ ያሉት ቀጥተኛ ያልሆኑ ውይይቶች ሊፋረሱ ቋፍ ላይ መሆናቸውን የፍልስጤም ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ጉልህ ክፍተት ታይቷል የተባለ ሲሆን፣ የእስራኤል ጦር ከያዛቸው ግዛቶች ለቆ መውጣት እንዲሁም የእስራኤል ጦር መላውን የጋዛን ሕዝብ አፈናቅሎ በራፋህ በሚዘጋጅ መጠለያ ለማስፈር የያዘው ዕቅድ ከሐማስ በኩል ተቀባይነት አላገኘም።

"በየቀኑ ስለ ተኩስ አቁም ይወራል፤ የት አለ?" ስትል ኢማን ትጠይቃለች።

አክላም "እነሱ [የእስራኤል ጦር] በረሃብ፣ በጥይት፣ በቦምብ፣ በአየር ጥቃቶች እየገደሉን ነው። በሁሉም መንገድ እየገደሉን ነው" ብላለች።

"አምላክን መሻት ይሻላል። አምላክ ትዕግስቱን ስጠኝ" በማለት የቀራት ተስፋ ፈጣሪዋ ላይ መሆኑን ተናግራለች።