በጋዛ ያለው የምግብ እጥረት በአስጊ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የዓለም ጤና ድርጅት አስጠነቀቀ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የዓለም ጤና ድርጅት በጋዛ እርዳታ ከአየር እየተጣለ ባለበት በአሁኑ ወቅት በሰርጡ ያለው የምግብ እጥረት "አስፈሪ ደረጃ" ላይ ደርሷል ሲል አስጠነቀቀ።
እስራኤል በጋዛ የምታካሂደው ጦርነት ላይ "ስልታዊ ፋታ" ማድረጓን እሁድ ዕለት ከገለፀች በኋላ ዮርዳኖስ ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ጋር በመተባበር 25 ቶን እርዳታ ከአየር ላይ መጣሏን አስታውቃለች።
እስራኤል፤ በቀን ለ10 ሰዓታት በጋዛ አንዳንድ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን እንደምታቆም እና ለተባበሩት መንግሥታት ተሽከርካሪዎች የእርዳታ ኮሪደሮችን እንደምትፈቅድ ተናግራለች።
ሐማስ "የራሱን ምስል እያጸዳ ነው" ስትል ከስሳ፣ እስራኤል "ሆን ብላ ታስርባለች የሚለውን ሐሰተኛ ውንጀላ አንቀበለውም" ብላለች።
የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ኃላፊ ቶም ፍሌቸር እሁድ ዕለት እንደገለጹት፤ በእስራኤል ተጥለው የነበሩ አንዳንድ የእንቅስቃሴ ገደቦች አሁን የቀለሉ ይመስላሉ።
ፍሌቸር፤ የመጀመሪያዎቹ ከ100 በላይ የጭነት ተሽከርካሪዎች የእርዳታ ቁሳቁስ ጭነው ወደ ጋዛ ለመግባት መተላለፍያ ድንበሮቹ ላይ መሰብሰባቸውን እንደተናገሩ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
"ይህ ለውጥ ነው"፤ "ግን ረሃብንና አስከፊ የጤና ቀውስን ለመከላከል ከፍተኛ መጠን ያለው እርዳታ ያስፈልጋል" ብለዋል።
እሁድ ዕለት የእስራኤል መከላከያ ኃይል ዱቄት፣ስኳር እና የታሸጉ ምግቦችን ያያዙ ሰባት ጥቅሎችን ከአየር ላይ ለጋዛ ነዋሪዎች መጣሉን አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የእስራኤል ወታደሮች በማዕከላዊ ጋዛ የእርዳታ ተሽከርካሪዎች በሚያልፉበት መንገድ አቅራቢያ የተሰባሰቡ ሰዎች ላይ ተኩስ በመክፈት ዘጠኝ ሰዎች ገድለው፣ 54 ነዋሪዎችን ማቁሰላቸውን የሕክምና ባለሙያዎች አስታውቀዋል።
ቅዳሜ ዕለት 'ስልታዊ ፋታው' ከጀመረ ከአንድ ሰዓት በኋላ በተፈጸመ የአየር ድብደባ የመኖሪያ አካባቢዎች ተመትተዋል።
ዓይን እማኞች፤ የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታ ተሽከርካሪዎችን በመጠባበቅ ላይ የነበሩ በርካታ ሰላማዊ ዜጎች በተሰበሰቡበት ማዕከላዊ ጋዛ፣ ሳላህ አልዲን ጎዳና፣ በኔትዛሪም ኮሪደር ዘጠኝ ሰዎች በጥይት ተመተው መሞታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ወታደሮቹ ወደ እነርሱ በቀረበ "የተጠርጣሪዎች ስብስብ" ላይ "የማስጠንቀቂያ ተኩስ ተኩሰዋል" ብሏል።
በሰው ሕይወት ላይ ስለደረሰ ጉዳት ምንም አይነት መረጃ እንደሌለው ተናግሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቢቢሲ ቬሪፋይ በምዕራብ ጋዛ ከተማ አልሪማል ዲስትሪክት ሚድሃት አል ዋሂዲ ጎዳና ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሙን መለየት ችሏል።
እስራኤል ከአንድ ሰአት በፊት አካባቢውን ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች የሚቆሙበት በሚል ለይታው ነበር።
ቢቢሲ ይህንን ማረጋገጥ የቻለው እሁድ ዕለት የዓይን እማኞች ሰጡትን ምስክርነት በማድረግ እንዲሁም ሁለት ቪዲዮዎችን የተቀረፁበትን ስፍራ በማመልከት ነው።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት፤ የአቅጣጫ መለያ ኮኦርድኔቶቹን ከተመለከተ በኋላ የአየር ድብደባ ስለመፈጸሙ መረጃው የለኝም ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከሁለት ሚሊዮን የጋዛ ሕዝብ አንድ ሦስተኛው ለብዙ ቀናት ምግብ የማይመገብ መሆኑን እና ከአራቱ አንዱ "ረሃብን የሚመስሉ ሁኔታዎችን እየተጋፈጠ ነው" ብሏል።
ባለፉት ቀናት ከ100 በላይ ሰዎች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት መሞታቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በእስራኤል እና በአሜሪካ በሚደገፈው የጋዛ ሰብአዊ ፋውንዴሽን (GHF) ከሚተዳደሩ የእርዳታ ምግብ ማከፋፈያዎች ምግብ ለመቀበል ሲሞክሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ በተከፈተባቸው ተኩስ መሞታቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል። እስራኤል ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ አድርጋለች መባሉን አስተባብላለች።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተጨማሪ እርዳታ ወደ ጋዛ እንደሚልኩ ተናግረው ይህ ግን "ዓለም አቀፍ ችግር ነው፤ የአሜሪካ ችግር አይደለም" ብለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ፤ "ከአየር የሚጣሉ እርዳታዎች አስከፊውን ስቃይ ለመቅረፍ ቢረዱም፣ የተሽከርካሪ መንገዶች ወደ ጋዛ ርዳታ ለማቅረብ ብቸኛው አዋጭ እና ዘላቂነት ያለው አማራጭ ሆነው ያገለግላሉ" ብለዋል ።

የፎቶው ባለመብት, EPA
የጋዛ ነዋሪዎች ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት በሚል የተደረገውን 'ጊዜያዊ ፋታ' የሚመለከቱት በጥንቃቄ ነው።
በጋዛ ከተማ የአራት ልጆች እናት የሆነችው ራሻ አል ሼክ ካሊል፤ "በእርግጥ እንደገና ትንሽ ተስፋ ይሰማኛል፤ ነገር ግን ፋታው ካበቃ በኋላ ረሃቡ እንደሚቀጥል ሳስብ እጨነቃለሁ" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
የስድስት ልጆች እናት የሆነችው ኔቨን ሳሌህ ደግሞ ቤተሰቦቿ "ባለፉት አራት ወራት ውስጥ አንድም አትክልትና ፍራፍሬ" እንዳልበሉ ተናግራለች።
"ዶሮ፣ ሥጋ፣ እንቁላል የለም" ስትል አክላለች።
"ብዙውን ጊዜ የምናገኘው ጊዜያቸው ያለፈባቸው የታሸጉ ምግቦች እና ዱቄት ነው" ትላለች።
ከደቡብ ጋዛ የመጣው ጋዜጠኛ ኢማድ ኩዳያ፣ አብዛኛው ከአየር የሚጣሉ የእርዳታ ጥቅሎች፣ ነዋሪዎች ለቅቀዋቸው በወጡ አካባቢዎች እና በእስራኤል ቁጥጥር ስር ባሉት ከወታደራዊ እንቅስቀሴ ነፃ በሆኑ ቦታዎች ወድቀዋል ብሏል።
ስለዚህ "ወደዚያ ከሄድክ ራስህን በጣም ትልቅ አደጋ ውስጥ ትጥላለህ" ሲል ያለውን አደጋ ያስረዳል።
እስራኤል ከሐማስ ጋር የጀመረችው ጦርነት እንደቀጠለ ነው። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አገራቸው "ውግያውን ትቀጥላለች" ብለዋል፧
"ሁሉንም የጦር ግቦቻችንን እስክናሳካ፣ ሙሉ ድል እስክንቀዳጅ ድረስ እርምጃችንን እንቀጥላለን።"
በጋዛ የሚገኘው የሐማስ መሪ ካሊል አልሃያ እሁድ ዕለት ከእስራኤል ጋር የሚደረግ የተኩስ አቁም ድርድር "እገዳ እስከቀጠለ ድረስ እና ረሃብ እስካለ ትርጉም የለሽ ነው" ብለዋል ።
እሁድ ዕለት የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም የእስራኤልን እርምጃ እንደሚቀበል ተናግሯል።
ነገር ግን የተራቡ ሰዎችን ያለ ምንም መዘግየት እርዳታ እንዲያገኙ ፍሰቱን "መጨመር" እንደሚያስፈልግ ተናግሯል። ዩኒሴፍም ተጨማሪ የሰብዓዊነት ኮሪደሮች ያስፈልጋሉ ብሏል።
ኔታንያሁ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ መንግሥታቸውን እንደወነጀለ ተናግረዋል።
"ደህንነታቸው የተጠበቁ መንገዶች አሉ፤ ሁልጊዜም ነበሩ፤ ዛሬ ግን ይፋዊ ሆነዋል" ብለዋል።
በአዲሱ እርምጃ እስራኤል ሕዝብ በሚበዛባቸው ሦስት የጋዛ አካባቢዎች ለ10 ሰዓታት የምታደርገውን ጦርነት እንደምታቆም እና ለእርዳታ አቅርቦት አስተማማኝ መንገዶችን እንደምትከፍት ተናግራለች።
የእስራኤል ጦር የእርዳታ ኮሪደሮቹ የተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎች ድርጅቶች ምግብ እና መድሃኒት ወደ ጋዛ እንዲያደርሱ ያስችላቸዋል ብሏል።
ሐማስ በደቡብ እስራኤል መስከረም 26 2016 ዓ.ም. ድንገተኛ ጥቃት አድርሶ 1200 እስራኤላውያንን ከገደለ እና 251 ካገተ በኋላ የእስራኤል ጦር በጋዛ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍቷል።
በዚህም በሐማስ የሚመራው የጡና ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ እስካሁን ድረስ ከ59,000 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።















