"ጋዛን ጎብኝተን ልባችን ተሰብሯል" የኦርቶዶክስ እና የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት አባቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢየሩሳሌም የቤተ ክርስቲያን አባቶች በጦርነት በወደመችው ጋዛ ያዩት ነገር "ልባቸውን እንደሰበረው" ተናግረዋል።
የግሪክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ ሳልሳዊ እና የላቲን የካቶሊክ ቤተ ከርስቲያን ፓትርያርክ ካርዲናል ቢየርባቲስታ ፒዛባላ ከጋዛ በተጨማሪ እስራኤል በወረራ በያዘቻት ዌስት ባንክ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ክርስቲያኖች በሰፋሪዎች እየደረሰባቸው ያለውን ጥቃት ከምዕመናኑ ሰምተዋል።
ጋዛን የጎበኙት የሃይማኖት አባቶች በረሃብ የገረጡ ፍልስጤማውያንን እንዲሁም ሕጻናት የቦምብ ድምጽ መላመዳቸውን አይተዋል።
በርካታ ወንዶች የሚበላ ነገር ለማግኘት "በጠራራ ፀሐይ እጃቸውን ዘርግተው ለሰዓታት ተቀምጠው" መመልከታቸውን ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
"ይህንን ውርደት በዓይን ማየት በጣም ከባድ ነው። ከሞራል አኳያ ተቀባይነት የሌለው እና ምንም ምክንያት ሊሰጠው የሚችል አይደለም" ብለዋል።
አቡነ ቴዎፍሎስ ሳልሳዊ በበኩላቸው ቤተ ክርስቲያናቸው "ከመላው የጋዛ ሕዝብ ጋር በአንድነት ትቆማለች" ብለዋል።
ሁለቱ የሃይማኖት አባቶች ባልተለመደ ሁኔታ በጦርነት የወደመችውን የጋዛ ሰርጥን የጎበኙት እስራኤል በከተማዋ በምትገኘው ሆሊ ፋሚሊ የተሰኘችው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ላይ ጥቃት ፈጽማ ሁለት ሴቶች እና አንድ ወንድ መገደላቸውን ተከትሎ ነው።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የደወሉላቸው በቁጣ መሆኑ ተዘግቧል።
ከዚያም ቀደም ብሎ የእስራኤል ሰፋሪዎች እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ በምትገኘው ታይቤህ በተሰኘችው የክርስቲያኖች መንደር የምትገኝ በአምስተኛው ክፍለ ዘመን የተቆረቆረች ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን ላይ እሳት መልቀቃቸው ተዘግቧል።
በተጨማሪም እነዚህ ሰፋሪዎች ታጥቀው በመምጣት ፍልስጤማውያን ክርስቲያኖች ላይ ጥቃት መፈጸማቸው እና ነዋሪዎች መገደላቸው ሪፖርት ተደርጓል።
የኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ጦራቸው በጋዛ ቤተ ክርስቲያን ላይ የፈጸመው ጥቃት በጥልቅ እንዳሳዘነው ገልጾ "ተባራራሪ ጥይት" ነው ሲል ፈርጆታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ይሁን እንጂ ፍልስጤማውያን ክርስቲያኖች ጥቃቱ የአምልኮ ስፍራዎች ላይ ሆን ብሎ ስለማነጣጠሩ ማንሳታቸው አልቀረም።
እስራኤል በአስገዳጅ ሁኔታ ከጋዛ ቀያቸውን ለቀው እንዲወጡ የምታወጣውን ትዕዛዝ ተከትሎ በሆሊ ፋሚሊ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያኗ ግቢ ውስጥ 400 ፍልስጤማውያን ተጠልለው ይገኛሉ።
የሃይማኖት አባቶቹ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የላቲን ፓትርያርክ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ ክርስቲያን ፍልስጤማውያን እንደ ሌሎች ፍልስጤማውያን በተመሳሳይ ሁኔታ ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
"በአሁኑ [የቤተ ክርስቲያኗ] ጥቃት ሦስት ምዕመናን ተገድለዋል፤ ነገር ግን በሺዎች የሚቆጠሩ በጋዛ ተገድለዋል" ሲሉም ተናግረዋል።
ካርዲናሉ በቅርቡ በታይቤህ የተፈጸመውን የእስራኤል ሰፋሪዎች ጥቃት በመጥቀስም በዌስት ባንክ እየተካሄደ ያለው ሰፊ ክስተት አካል መሆኑን ጠቀውመው "ሕግ አልባ መሬት" ሆኗል ሲሉ ወቅሰዋል።
የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሃይማኖት አባቶቹ 500 ቶን እርዳታ ጭነው መግባታቸውን ቢያስታውቅም ካርዲናሉ ግን በሎጂስቲክ ጉዳይ "አንዲት ግራም ይዘን መግባት አልቻልንም" ብለዋል።
እርዳታ ለመቀበል ወደ ቤተ ክርስቲያኗ የመጡ ምዕመናን ምንም ነገር መስጠት አለመቻላቸው እንዳሳዘናቸው የካቶሊኩ ካርዲናል ገልጸዋል።
21 ወራት ባስቆጠረው የጋዛ ጦርነት በከፍተኛ ሁኔታ የተራቡ ሰዎችን እንዳገኙ እንዲሁም ያዩትን አጠቃላይ ውድመትን በተመለከቱ የግሪክ ኦርቶዶክሱ ፓትርያርክ እና የላቲን ካቶሊክ ካርዲናል ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
"የፈራረሱ ሕንጻዎችን እያለፍን በአቧራ ውስጥ እንዲሁም በድንኳኖች መካከል ተመላለስን። አውራ ጎዳናዎችን፣ ግቢዎችን፣ ባሕር ዳርቻዎችን ጫፍ ድረስ ሄደን አይተናል። ሁሉ ነገራቸውን ያጡ ድንኳኖችን መኖሪያቸው አድርገዋል" ሲሉ የአራት ቀናት ጉብኝታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ካርዲናል ፒዛባላ ተናግረዋል።
ሁለቱ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ቀደም ብለው ወደ ሰሜናዊ ራማላህ ታይቤህ የክርስቲያን መንደር የውጭ ዲፕሎማቶች የልዑካን ቡድንን በመምራት አቅንተው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Jimmy Michael / BBC
ነዋሪዎች እና የአካባቢው ካህናት በእስራኤል ሰፋሪዎች የሚፈጸምባቸውን በርካታ ጥቃቶች ተናግረዋል። ከእነዚህም መካከል በባዛይታን ዘመን በተሠራው እና እንደ ቅርስ በሚታየው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የተለኮሰው እሳት ተጠቅሷል።
የእስራኤል ፖሊስ ልዩ የምርመራ ክፍል አቋቁሞ አደረግኩት ባለው ምርመራ "ከአሳሳች ሪፖርቶች በተጻራሪ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ የደረሰ ጉዳት የለም" በማለት ከሰሞኑ መግለጫ አውጥቷል።
እሳቱ በአቅራቢያው ባለው ክፍት ቦታ ላይ ተወስኖ የነበረ ነው፤ ያለው መግለጫው ሆን ተበሎ እሳቱ መለኮሱን በተመለከተ አለመረጋገጡን አትቷል።
ሆኖም አንድ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የእስራኤል ሰፋሪዎች እሳቱን እንዳያያዙ ተናግረዋል። ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ደግሞ ቅሬታቸውን ለእስራኤል የፀጥታ ኃይሎች ቢያቀርቡም ምንም ምላሽ አልሰጡንም ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ሠፋሪዎች በዚህች ጥንታዊ ቤተክርስቲያን ላይ እሳት መለኮሳቸውን ተከትሎ የከተማው ካህናት ዓለም አቀፍ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርበው ነበር።
እነዚህ ሰፋሪዎች የመንደሪቷን ነዋሪዎች ገፍተው በታይቤህ ዳርቻዎች ያሉ መሬታቸውን እንደነጠቋቸው እና በየጊዜውም እንግልት እንደሚፈጽሙባቸው ነዋሪዎቹ አስረድተዋል።
ሰፋሪዎቹ ከብቶቻቸውን እያመጡ የወይራ ዛፎቻቸውን እንደሚያስበሉባቸውም ነው የተናገሩት።
"እየሆነ ያለው ነገር በጣም አሳዛኝ ነው። ነዋሪዎቻችን እየተገፉ እየወጡ እስራኤላውያንን መሬታችንን እየያዙ ነው" ሲሉ የቀድሞ ከንቲባ እና ታይቤህ የተሰኘ ቢራ ፋብሪካ አንደኛው መሥራች ዳውድ ክሆሪ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
የቀድሞው ከንቲባ እንደሚናገሩት እነዚህ ጽንፈኛ ሰፋሪዎች እየፈጸሟቸው ያሉ ጥቃቶች እና የጋዛ ጦርነት ከተጀመረበት ወቅት ጀምሮ ያለው የምጣኔ ሃብት መንኮታኮት በርካታ ፍልስጤማውያን ክርስቲያኖች እንዲሰደዱ ያስገድዳቸዋል ብለዋል።
ባልተለመደ ሁኔታ የታይቤህ መንደርን ከጎበኙት መካከል በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሃካቢ አንዱ ነበሩ።
አምባሳደሩ በቤተክርስቲያኗ አቅራቢያ የተፈጸመውን ጥቃት "የሽብር ተግባር" ሲሉ አውግዘው፤ ይህንን የፈጸሙ "ከፍ ያለ ቅጣት" እንዲከተላቸው ጠይቀዋል።
ሃካቤ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገወጥ ተብለው የተፈረጁ የአይሁድ ሰፈራዎችን የሚደግፉ ጠንከር ያሉ መግለጫዎችን በማውጣት ይታወቃሉ።
ሆኖም የኢቫንጀሊካል ፓስተሩ "አምባሳደር ቤተ ክርስቲያንን፣ መስጊድ ወይም ምኩራብን ማዋረድ በሰብዓዊነት እንዲሁም በአምላክ ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
ለእስራኤል ፓሊስ መግለጫ ምላሽ የሰጡት አምባሳደሩ እሳቱን ያስነሳው ቡድን ማን እንደሆነ አለመጥቀሳቸውን ገልጸው ሆኖም "ምንም ይሁን ምን ድርጊቱ ወንጀል ነው እናም ቅጣት ሊከተል ይገባል" ብለዋል።
እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1967 በተደረገው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ነው የፍልስጤማውያኑ ግዛት የሆኑትን ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን የተቆጣጠረችው።
ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ለ700 ሺህ አይሁዳውያን መኖሪያ የሚሆኑ 160 ሰፈራዎችን ገንብታለች። በዌስት ባንክ 3.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ይኖራሉ።
አብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እስራኤል እያደረገችው ያለውን ሰፈራ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገወጥ ነው ሲል ይኮንናል።
እስራኤል ይህንን አትቀበልም።
በእስራኤል በተከታታይ የመጡ አስተዳደሮች ሰፈራዎች እንዲስፋፉ አድርገዋል።
ይሁን እንጂ ሰፈራን የሚደግፈው የቅኝ ክንፍ አክራሪ ጥምረት የሆነውን መንግሥት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድጋሚ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ሰፈራዎች እየተስፋፉ ይገኛሉ።
የጋዛ ጦርነትም እንዲሁ ለእነዚህ ሰፈራዎች መጨመር በር መክፈቱም ተነግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በእየሩሳሌም በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ አቡነ ቴዎፍሎስ ሳልሳዊ ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑት ፍልስጤማውያን ክርስቲያኖች በታሪካዊው ቅዱስ ስፍራቸው በጋዛ እንዲቆዩ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል።
በዚህ ጉብኝታቸው ወቅት አባ ፒዛባላ ከአንድ የጣሊያን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ በግዛቲቷ ውስጥ "ምንም ቢከሰት" የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በስፍራው ትቆያለች ብለዋል።
ሁለቱ የሃይማኖት አባቶች የካቶሊኩ ጳጳስን ጨምሮ በርካታ የዓለም መሪዎች እያደረጉ እንዳሉት በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ እንዲሁም በሐማስ የተያዙ ቀሪ ታጋቾቸ እንዲለቀቁ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
"የእስራኤል ተቃራኒ አይደለንም" ያሉት በተለያዩ ሃይማኖች መካከል ውይይት እንዲደረግ ድጋፍ በማድረግ የሚታወቁት ካርዲናል ፒዛባላ፤ "ነገር ግን በቅንነት እና በግልጽነት መናገር ያለብን የእስራኤል መንግሥት በጋዛ ያለው ፖሊሲ ተቀባይነት የሌለው እና ከሞራል አንጻር ምክንያት ሊፈጠርለት የሚችል አይደለም" ብለዋል።
እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን እርዳታ እንዳይደርሳቸው ከመጋቢት ጀምሮ ሙሉ እገዳ ጥላለች። ለሁለት ወራት የቆየው የተኩስ አቁም መፍረሱን ተከትሎ በጋዛ የማያባራ ጥቃት እያካሄደች ነው።
የእስራኤል ጦር ይሄንን ሁሉ የሚያደርገው ሐማስ የቀሩ ታጋቾችን እንዲለቅ ጫና ለማድረግ ነው ይላል።
ከ100 በላይ ዓለም አቀፍ የረድዔት እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች "የምግብ ፍጆታዎች አቅርቦቶች በሙሉ እየተሟጠጡ የረድዔት ድርጅቶች የራሳቸው ሠራተኞች ሲረግፉ ዓይናቸው እያየ ነው" ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ ኮሚሽነር ጄነራል ፊሊፔ ላዛሪኒ ሐሙስ ዕለት በሰጡት መግለጫ "ከ100 በላይ የሚሆኑ ፍልስጤማውያን አብዛኞቹ ሕጻናት በረሃብ መሞታቸው ሪፖርት መደረጉን" ጠቅሰዋል።
"ሕጻናት መንምነው አጥንታቸው እያገጠጠ መሆኑን ቡድናችን እየተመለከተ ነው። ሕጻናቱ አቅማቸው እየደከመ እና የሚያስፈልጋቸውን ምግብ እና ሕክምና ካላገኙ በከፍተኛ ሁኔታ ለሞት ይጋለጣሉ" ያሉት ላዛሪኒ እስራኤል "የሰብዓዊ አጋሮች ያልተገደበ እና ያልተቆራረጠ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲያስገቡ እንድትፈቅድ" ተማጽነዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ አንድ አራተኛው የጋዛ ሕዝብ በረሃብ እየተፈተነ መሆኑን ባደረገው ግምገማ ገልጿል።
"የጅምላ ረሃብ ከማለት ውጪ ሌላ ምን እንደምትሉት አላውቅም፤ ይህም በሰው ሠራሽ ምክንያት የተፈጠረ ነው" ሲሉ የተቋሙ ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ገብረ ኢየሱስ ረቡዕ ዕለት ተናግረዋል።
"ይህም መንስዔው በጣም ግልጽ ነው፤ በእገዳው ምክንያት ነው" ብለዋል።
እስራኤል እና አሜሪካ ለፍልስጤማውያን እርዳታ እናከፋፍላለን በሚል 'የጋዛ ሂውማኒታሪያን ፋውንዴሽን' (ጂኤችኤፍ) የተሰኘ አወዛጋቢ ድርጅት ያቋቋሙ ሲሆን፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እርዳታ ሲጠባበቁ ባሉ ፍልስጤማውያን ላይ በየቀኑ በሚባል ሁኔታ የእስራኤል ጦር በሚከፍተው ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።
በባለፉት ሁለት ወራት የእስራኤል ጦር በእርዳታ ጠባቂ ፍልስጤማውያን ላይ በከፈተው ተኩስ ከ1,000 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ አስታውቋል።
ከእነዚህ ውስጥም 766 ግድያዎች የተፈጸሙት በጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽን ግቢ ውስጥ ነው።
ቀሪዎቹ 288 ፍልስጤማውያን ደግሞ የተገደሉት የተፈጸሙት በተባበሩት መንግሥታት እና በሌሎች የእርዳታ መኪኖች አቅራቢያ ነው።















