እስራኤል በቡልዶዘሮች ታግዛ በታቀደ ሁኔታ በሺዎች የሚቆጠሩ የጋዛ መኖሪያ ሕንጻዎችን እየደመሰሰች ነው

በጋዛ እየተካሄደ ያለው ፈረሳ

የእስራኤል ጦር በጋዛ ከሚፈጽማቸው ጥቃቶች በተጨማሪ በፍንዳታዎች፣ በቡልዶዘሮች እና በኤክስካቬተሮች ታግዞ ሕንጻዎችን እየደረመሰ ከመሬት ጋር እያመሳሰላቸው ነው።

በታቀደ ፈረሳም ሕንጻዎቹን ሙሉ ለሙሉ በማፈራረስ ለመጥረግ ከአሜሪካ ዲ9 የተሰኙ ቡልዶዘሮችንም አግኝቷል።

ለዚህም ተግባር ተቋራጮች ተቀጥረው የጋዛ ሕንጻዎች ወደ አፈርነት እንዲቀየሩ እየተደረጉ ነው።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ለፓርላማ አባላት በዝግ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር የእስራኤል መከላከያ ኃይል "በርካታ ቤቶችን እያወደመ ነው" ፍልስጤማውያን "የመመለሻ ቦታ የላቸውም" ሲሉ መናገራቸውን በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በሰፊው ተዘግቧል።

እስራኤል ሁለት ዓመት ሊጠጋው የተቃረበውን በጋዛ የምታካሂደው ጥቃት ከዓለም ዕይታ የተደበቁ አይደሉም።

ሕንጻዎች ወደ ፍርስራሽነት ሲቀየሩ ዓለም በቀጥታ አይቶ ታዝቧል።

ጋዛ ዩኒቨርስቲዎቿ፣ መስጊዶቿ፣ አብያተ ክርስቲያናቷ፣ ሆስፒታሎቿ ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል።

እስራኤል ከሐማስ ጋር የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ከፈረሰ ከመጋቢት በኋላ አቅዳ ፈረሳ እየፈጸመች ሲሆን፣ በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ሕንጻዎች ወድመዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

መኖሪያ ሰፈሮች እና ከተሞች እንዳልነበሩ ሆነዋል።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ይኖሩባቸው የነበሩ መኖሪያ ሕንጻዎች ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ወድመው ከመሬት ጋር እንዲመሳሰሉ ተደርገዋል።

የእስራኤል ጦር "በኦፕሬሽን ቁጥጥር ስር" አድርጌያቸዋለሁ በሚላቸው የጋዛ ይዞታዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ውድመት እንደደረሰም የሳተላይት ምሥሎች ያሳያሉ።

እነዚህ ወደ መሬትነት የተቀየሩ ሕንጻዎች እስራኤል ሆን ብላ አቅዳ በምትፈጽማቸው ፈረሳዎች ነው።

እየተካሄደ ያለው የታቀደ ፈረሳ እስራኤል እያካሄደችው ባለው የከባድ መሳሪያ እና የአየር ድብደባ የተጎዱ እንዲሁም ምንም ባልተነኩ ሕንጻዎች ላይ ነው።

እስራኤል እየፈጸመችው ያለው ውድመት መጠን ከግብፅ ድንበር አቅራቢያ ባለችው የራፋህ ከተማ በግልጽ ይታያል።

በቅርብ ሳምንታት የእስራኤል ጦር እና ኮንትራክተሮች በራፋህ ያሉ ሕንጻዎችን ወደ መሬትነት ቀይረዋቸዋል።

ጦሩ ፍንዳታዎች፣ ኤክስካቬተሮች እና ቡልዶዘሮችን በመጠቀም ነው ሕንጻዎቹን ወደ ከመሬት ጋር እያመሳሰላቻቸው ያለው።

ቢቢሲ ያረጋገጠው ቪዲዮ የእስራኤል ጦር በመኖሪያ ሕንጻዎች፣ በትምህርት ቤቶች እና በሌሎች መሠረተ ልማቶችን ከመሬት ጋር ለማመሳሰል በሚያደርገው ፈረሳ ትላልቅ ፍንዳታዎች ሲፈጠሩ ያሳያል።

እስራኤል በኃይል በተያዙ ግዛቶች ያሉ መሠረተ ልማቶችን ማውደም የሚከለክለውን የጄኔቫ ኮንቬንሽን በመጣስ የጦር ወንጀሎችን ፈጽማ ሊሆን እንደሚችል በርካታ የሕግ ባለሙያዎች ለቢቢሲ ቬሪፋይ ተናግረዋል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ በበኩላቸው በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት እየሠራን ነው ይላሉ።

ቃል አቀባዩ እንደሚሉት ሐማስ "ወታደራዊ ንብረቶችን" በሰላማዊ ዜጎች መኖሪያዎች ስለደበቀ "የእነዚህ ሕንጻዎች መውደም የሚፈጸመው ወታደራዊ አስፈላጊነቱ ሲኖር ብቻ ነው" ይላሉ።

የሳተላይት ምሥል
የምስሉ መግለጫ, ይህ ሚያዝያ መጨረሻ አካባቢ የተወሰደ የሳተላይት ምሥል በጋዛ አንድ ክፍል አብዛኞቹ ሕንጻዎች እንደነበሩ ያሳያል
የሳተላይት ምሥል
የምስሉ መግለጫ, ይህ ግንቦት ላይ መጀመሪያ የተወሰደ የሳተላይት ምሥል አብዛኞቹ ሕንጻዎች መውደማቸውን ያሳያል

በቅርቡ በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን በሙሉ አፈናቅሎ በደቡባዊ ክፍል በሚዘጋጅ ካምፕ ለማስገባት ዕቅድ እንዲዘጋጅ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ለጦራቸው ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

በራፋህ ከተማ ፍርስራሽ ላይ "ሰብዓዊ ከተማ" ለማቋቋም እንደሚፈልጉ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ኢዝራኤል ካትዝ ይህም በመጀመሪያ 600 ሺህ ፍልስጤማውያን የሚቆዩበት ካምፕ ይሆናል ብለዋል። ፍልስጤማውያኑ ከካምፑ መውጣት እንደማይፈቀድላቸው ተናግረዋል።

ይህ ዕቅድ በከፍተኛ ሁኔታ የተወገዘ ሲሆን፣ የቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሁድ ኦልመርት "ከማጎሪያ ካምፕ ጋር ተመሳሳይ ነው ተብሎ ይተረጎማል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በራፋህ ከተማ የምትገኘው ቴል አል ሱልጣን በደማቅነቷ ከሚታወቁ ሰፈሮች አንዷ ነበረች። ጥቅጥቅ ያሉ ጎዳናዎቿ የራፋህ ብቸኛ የማዋለጃ ሆስፒታል እንዲሁም ወላጆቻቸውን ያጡ እና የተጣሉ ሕጻናትን የሚንከባከብ ማዕከል መገኛ ነበሩ።

እስራኤል በቦምብ እና በከባድ መሳሪያዎች በፈጸመችው ጥቃት አብዛኛው ሰፈሩ ቢወድምም በርካታ ሕንጻዎች ጥቃቱን ተቋቁመው መጽናት ችለው ነበር።

ሆኖም ከጥቂት ቀናት በፊት፣ ሐምሌ 6/2017 ዓ.ም. ጀምሮ የሕንጻዎቹ ፈረሳ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ጉዳት ደርሶባቸው ቆመው የነበሩ ሕንጻዎችን ጨምሮ ሰፈሩ ላይ ያሉ ሕንጻዎች በሙሉ ተጠራርገው ወደ መሬትነት እንዲቀየሩ ተደርገዋል።

የቀሩት በጣት ከሚቆጠሩ ሕንጻዎች መካከል አንደኛው ሆስፒታል ነው።

በተመሳሳይ ሁኔታ አጎራባቿ ሳዑዲ ሰፈርም በእስራኤል ጦር ወደ ትቢያነት ተቀይራለች። ሰፈሯ በአንድ ወቅት የከተማዋ ትልቁ መስጊድ እንዲሁም በርካታ ትምህርቶች ቤቶች ማዕከል ነበረች።

ቢቢሲ ያረጋገጠው ቪዲዮ አንድ ታንክ በራፋህ ጎዳና ሲንቀሳቀስ እንዲሁም ኤክስካቬተር በመንገድ ዳር ላይ ሆኖ ሲቆፍር ያሳያል።

እስራኤል እየፈጸመቻቸው ያሉ ፈረሳዎች በራፋህ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የጋዛ ሰርጥ ይዞታዎችም ቀጥለዋል። እነዚህ ይዞታዎች የእስራኤልን የቦምብ ጥቃቶች በተወሰነ መልኩ መቋቋም ችለው ነበር።

ከእነዚህም አንዷ ከእስራኤል ድንበር በ1.5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገው የኩዛኣ የእርሻ ከተማ ናት።

ከተማዋ ከጦርነቱ በፊት 11 ሺህ ያህል ፍልስጤማውያን ይኖሩባት ነበር። በለምነቷ የምትታወቀው ይህች ስፍራ ቲማቲም፣ ስንዴ እና ወይራ በአብዛኛው ታበቅላለች።

የጋዛ ካርታ
የምስሉ መግለጫ, ሕንጻዎችን የማፍረስ እና የመጥረግ ተግባር የተከናወነባቸው የጋዛ አካባቢዎች

ከግንቦት ወር በፊት የተወሰዱ የሳተላይት ምሥሎች በከተማዋ ያሉ በርካታ ሕንጻዎች ቆመው እንደነበር ያሳያሉ።

ሆኖም በሰኔ ወር አጋማሽ ላይ የኩዛኣ አብዛኛው ስፍራ በእስራኤል ወታደሮች እንዲደመሰሱ ተደረጉ።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል በኩዛአ 1,200 ሕንጻዎችን አፍርሻለሁ ያለ ሲሆን፣ እነዚህም በሐማስ የሚተዳደሩ "የሽብር መሠረተ ልማቶች" አካል ናቸው ብሏል።

በአቅራቢያው በምትገኘው እና የ27 ሺህ ፍልስጤማውያን መኖሪያ በሆነችው አባሳን አልካቢራ ከተማም ተመሳሳይ ድምሰሳ ነው በእስራኤል ጦር የተፈጸመባት።

ከግንቦት 23 አስከ ሐምሌ 1/2017 ዓ.ም. ባሉ ቀናት የተነሱ ፎቶዎች እንደሚያሳዩት በ38 ቀናት የከተማዋ ሰፊ ክፍል በጦሩ እንድትጠረግ ተደርጓል።

እስራኤል ሰፊ የጋዛ ግዛቶችን "የፀጥታ ቀጠናዎች" እና ኮሪደሮች በሚል ከሌላው ጋዛ ክፍል ለይታ በእነዚህ ይዞታዎች እና አቅራቢያዎቹ ላይ በርካታ ሕንጻዎችን ደርምሳለች።

በጦርነቱ ጅማሮም እስራኤል በድንበር አቅራቢያ ያሉ ሕንጻዎችን በማፍረስ ሰፊ "የመከላከያ ዞኖች" ያለቻቸውን ስፍራዎች ለመፍጠር እየሞከረች እንደሆነ ተንታኞች ይናገራሉ። ነገር ግን አንዳንዶቹ ወደ አፈርነት የተቀየሩት ወደ ጋዛ ጠልቀው በገቡ ስፍራዎች ላይ ነው።

ከእስራኤል ድንበር 7 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ኩዊዛን አቡ ራሽዋን የተሰኘው የእርሻ ሰፈራ ከግንቦት 9/2017 ዓ.ም. ጀምሮ የቆሙ ሕንጻዎች ሙሉ በሙሉ እንዲደመሰሱ ተደርዋል። በርካታ የመኖሪያ እና የንግድ ሕንጻዎች በፍንዳታዎች እንዲወድሙ መደረጋቸውን ቢቢሲ ያረጋገጠው ቪዲዮ ያሳያል።

ቢቢሲ ጦሩ የፈጸማቸውን ፈረሳዎች ዝርዝር አቅርቦ ለእነዚሀ ወታደራዊ ምክንያቶች እንዲሰጥ የእስራኤል መከላከያ ኃይልን ጠይቆ ነበር። ነገር ግን ምክንያት መስጠት አልቻለም።

"ሐማስ እና ሌሎች አሸባሪ ድርጅቶች ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ወታደራዊ ንብረቶችን እንደሚደብቁ በሰፊው ተመዝግቧል" ሲሉ የእስራኤል የመከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

"መከላከያ ኃይሉ በእነዚህ ሕንጻዎች ወይም በሌሎች ስፍራዎች ላይ ያሉ የአሸባሪዎች መሠረተ ልማቶችን በመለየት ያወድማል" ብለዋል።

የሳተላይት ምሥል
የሳተላይት ምሥል

በርካታ የሰብዓዊ መብት ጠበቆች እስራኤል እያካሄደችው ያለው ፈረሳ የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በጦርነት ወቅት ለሰላማዊ ዜጎች ከለላ በሚሰጠው አራተኛው የጄኔቫ ኮንቬንሽን መሠረት ጦሩ እያደረገው ያለው ነገር በቂ ምክንያት የለውም፤ ሲሉ በኢየሩሳሌም የሚገኘው የዲያኮንያ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ ማዕከል ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ ኤይታን ዲያመንድ ያስረዳሉ።

"ዓለም አቀፉ የሰብዓዊነት ሕግ በጦርነት ወቅት ግዴታ በሆነ መልኩ ወታደራዊ ምክንያት ከሌለ እንዲህ ዓይነት ቁጥጥር ባለው መንገድ የሰላማዊ ንብረቶችን ማውደም ይከለክላል" ይላሉ የሕግ ባለሙያው።

"ለወደፊት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል በሚል ስጋት ወይም ግምቶች ከዚህ ከተቀመጠው ልዩ ከሆነው ሁኔታ ውጪ ነው" ይላሉ።

የኦክስፎርድ የሥነ ምግባር፣ የሕግ እና በጦር መሳሪያ የታገዘ ግጭት ተቋም ተባባሪ ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ጃኒና ዲል በበኩላቸው ወራሪ ኃይልም ቢሆን ግዛቶችን ከሕዝቡ ጥቅም ጋር በተጣጠመ መልኩ ማስተዳደር አለባቸው "ግዛቲቱን ለነዋሪዎች መኖር ወደማይቻልባቸው ሁኔታ መቀየር እና ወና ማድረግ ከወታደራዊ አካሄድ ጋር የማይጣጣም ነው" ብለዋል።

ነገር ግን አንዳንድ ተንታኞች በበኩላቸው ጦሩ እያደረገ ያለውን ፈረሳ ለመከላከል ሞክረዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱ ፈረሳ የፈጸመባቸው አብዛኞቹ ሕንጻዎች በከባድ መሳሪያ እና በአየር ጥቃት የፈራረሱ ናቸው የሚሉት በእስራኤል 'ቤሳ' የተሰኘ የስትራቴጂ ጥናት ማዕከል እና የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሚኒስቴር የቀድሞ ባለሥልጣን ፕሮፌሰር ኢታን ሻሚር ናቸው።

እነዚህ ሕንጻዎች ነዋሪዎች ተመልሰው ከገቡባቸው "በክረምት ዝናብ የመደርመስ ዕድላቸው ከፍተኛ ስለሚሆን" የደኅንነት ስጋት እንዳላቸው ይናገራሉ።

ፕሮፌሰሩ ሌላ እንደ ምክንያትነት የሚጠቅሱት የታክቲክ ስጋቶችንም ነው።

"አካባቢው የውጊያ ቀጣና ነው። የእስራኤል መከላከያ ኃይል አንድ ሕንጻ ገብቶ ካጸዳ በኋላ አሸባሪዎቹ አብዛኛውን ጊዜ ተመልሰው ቦምብ ይቀብራሉ ወይም ተደብቀው በእነሱ ላይ ይተኩሳሉ።"

እስራኤል እያካሄደችው ያለውን ፈረሳ የማቀዝቀዝ ምልክት አይታይባትም።

የእስራኤል መከላከያ በርካታ ዲ9 የተሰኙ ቡልዶዘሮችን ከአሜሪካ እንደተቀበለ የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ባለፈው ሳምንት ዘግበዋል። እነዚህ ቡልዶዘሮች የባይደን አሰተዳደር ለእስራኤል ለመስጠት ያቀዳቸው ናቸው።

በጋዛ ለሚካሄደው ማፍረስ ሥራ የወጣ የቅጥር ማስታወቂያ
የምስሉ መግለጫ, በጋዛ ለሚካሄደው ማፍረስ ሥራ የወጣ የቅጥር ማስታወቂያ
በጋዛ ለሚካሄደው ማፍረስ ሥራ የወጣ የቅጥር ማስታወቂያ
የምስሉ መግለጫ, በጋዛ ለሚካሄደው ማፍረስ ሥራ የወጣ የቅጥር ማስታወቂያ

በተጨማሪም በእስራኤል የፌስቡክ ቡድኖች ላይ በጋዛ ፈረሳዎችን ለማካሄድ ተቋራጮችን የሚጠይቁ በርካታ ማስታወቂያዎችን ቢቢሲ አግኝቷል። እነዚህ የፈረሳ ማስተዋወቂያዎች ከግንቦት ጀምሮ በቀጣሪዎች ተጋርተዋል።

አብዛኞቹ ማስታወቂያዎች ፈረሳዎች የሚካሄድባቸውን የጋዛ ይዞታዎች የሚገልጹ ሲሆን፣ ለምሳሌም ያህል "ፊላደልፊ ኮሪደር" እና "ዘ ሞራግ አክሲስ" ተጠቅሰዋል። ሁለቱም ስፍራዎች በእስራኤል መከላከያ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ናቸው።

ቢቢሲ አንደኛውን ተቋራጭ ምላሽ በጠየቀበት ወቅት በዘለፋ የመለሰ ሲሆን፤ ቢቢሲን ብቻ ሳይሆን ጋዛንም በአጸያፊ መልኩ ተሳድቧል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል እየፈጸመ ያለው ፈረሳ "በቋሚነት መቆጣጠር" የሚችለው "የደኅንነት ዞን" ለመመሥረት ሊሆን እንደሚችል የሩትገርስ የሕግ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት አዲል ሃክ ያስረዳሉ።

ሌሎች ተንታኞች በበኩላቸው ፈረሳው እየተፈጸመ ያለው በራፋህ ፍርስራሾች ላይ ሊቋቋም የታሰበውን "የሰብዓዊነት ከተማ" መሬት ጠረጋ ሊሆን ይችላል ይላሉ።

የኢየሩሳሌም የስትራቴጂ እና የፀጥታ ተቋም ፕሬዝዳነት ኤፍሬም ኢንባር በበኩላቸው ፍልስጤማውያን ከጋዛ ሰርጥ በቋሚነት ተፈናቅለው እንዲወጡ ለማድረግ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

ለጋዛውያን የተፈጸመባቸው ጥፋት የከፋ ነው።

የቴል አል ሱልጣን ነዋሪ የነበሩት ሞአታዝ ዩሱፍ አህመድ አል አብሲ ቤታቸው በእስራኤል እንደተጠረገ ይናገራሉ።

"ጦርነቱ ከመጀመሩ ከአንድ ዓመት በፊት ነበር ወደዚህ ቤት የገባሁት። በጣም ደስተኛ ነበርኩ፤ ሕይወቴም በተስፋ የተሞላ ነበር። አሁን ያ ሙሉ በሙሉ ወድሟል" ብለዋል።

እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1948 እንደ አገር ስትመሠረት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ያፈናቀለች ሲሆን፣ ይህንንም "ናቅባ" (ታላቁ እልቂት) ሲሉ ይጠሩታል።

በአሁኑ ወቅትም ፍልስጤማውያኑ ይኸው ይደገማል በሚል ፍራቻ ላይ ናቸው።

ከቀያቸው የተፈናቀሉት ፍልስጤማውያኑ አብዛኞቹ በጋዛ ሰፍረዋል።

በአሁኑ ወቅት ካሉ የጋዛ ነዋሪዎች መካከል ሦስት አራተኛውን የሚይዙት በዚያን ወቅት የተፈናቀሉ የልጅ ልጆች ናቸው።

ሌሎች 900 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ አሁን እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ ይኖራሉ።

በአሁኑ ወቅት 3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በዮርዳኖስ፣ በሶሪያ እና በሊባኖስ እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።