እስራኤል በጋዛ እርዳታ በአውሮፕላን መጣል መጀመሯን አስታወቀች

የእርዳታ ምግብ ለመቀበል እየተጠባበቁ የሚገኙ ፍልስጤማውያን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የእስራኤል ጦር ለሳምንታት የዘለቀውን ዓለም አቀፍ ጫና እና በፍልስጤም ግዛት እየጨመረ ያለውን የረሃብ ቀውስ ተከትሎ "በቅርቡ" በጋዛ ሰርጥ የሰብዓዊ እርዳታ በአውሮፕላን መጣል መጀመሩን ይፋ አድርጓል።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት (አይዲኤፍ) እሁድ ዕለት በሰጠው መግለጫ ከአየር ላይ የተጣሉት "ሰባት ጥቅሎች ዱቄት፣ ስኳር እና የታሸገ ምግብ የያዙ ናቸው" ብሏል።

እስራኤል የተባበሩት መንግሥታት እርዳታ የጫኑ መኪኖች ወደ ጋዛ ለመግባት እንዲችሉ የሰብዓዊነት ኮሪደሮችን ለመክፈት መዘጋጀቷን ቀደም ሲል ተናግራለች።

ይህ የሆነው እስራኤል ተጨማሪ እርዳታ ወደ ጋዛ እንድታስገባ በተጠየቀችበት ወቅት እና በግዛቱ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች ለወራት በቆየው የተገደበ የእርዳታ አቅርቦት የተነሳ የጅምላ ረሃብ እንደተከሰተ ማስጠንቀቂያ በተሰጠበት ወቅት ነው። እስራኤል በጋዛ ውስጥ "ሆን ተብለው እንዲራቡ ተደርገዋል የሚለው ውንጀላ ሐሰት ነው" በማለት አስተባብላለች።

የእስራኤል ጦር በመግለጫው ከአየር የሚጣለው እርዳታ "ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሚካሄድ እና በኮጋት የሚመራ ነው" ሲል የእስራኤል ወታደራዊ አካልን የሆነው ተቋም ወደ ጋዛ የሚገባውን እርዳታ እንደሚቆጣጠር አስታውቋል።

ወታደራዊ አውሮፕላን እርዳታዎችን ሲጥል የሚያሳይ ቪዲዮም ለቅቋል። ይህ ምስል በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም።

የፍልስጤም ባለስልጣናት በጋዛ እርዳታ ከአውሮፕላን እየተጣለ ነው ስለሚለው የእስራኤል መከላከያ ኃይል መረጃ እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።

ቅዳሜ አመሻሹ ላይ የእስራኤል መከላከያ "በጋዛ ሰርጥ ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ለማሻሻል የታቀዱ ተከታታይ እርምጃዎችን መውሰድ መጀመሩን" እና "ብዙ ሰዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ ፋታዎችን ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቱን" ተናግሯል ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተጨማሪም በጋዛ ለተከሰተው ከፍተኛ የውሃ እጥረት የሚሆን ለውሃ ማጣርያ ጣቢያው ኃይል ማቅረብ እንደጀመረ ገልጿል። ይህም "ወደ 900,000 የሚጠጉ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል" ብሏል።

እስራኤል ከመጋቢት ወር መጀመሪያ ጀምሮ ወደ ጋዛ የሚገቡ ማንኛቸውንም የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች አቋርጣ በግንቦት ወር አዲስ ገደብ በመጣል ዳግም እንዲጀመር አድርጋለች።

ከአሜሪካ ጋር በመሆን የጋዛ ሂውማኒተሪያን ፋውንዴሽን (GHF) የተሰኘውን ተቋም በመደገፍ በግዛቱ ውስጥ እንዲሰራ ፈቅዳለች።

ፋውንዴሽኑ በግንቦት መጨረሻ ስራውን ከጀመረ ወዲህ እርዳታ ለመቀበል ወደ ጣብያው የሚመጡ ፍልስጤማውያን እየተገደሉ መሆኑን የሚገልጹ ሪፖርቶች በየቀኑ ማለት በሚያስደፍርል መልኩ ይሰማል።

አብዛኞቹ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ወታደሮች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እስራኤል ወታደሮቿ የማስጠንቀቂያ ጥይት መተኮሳቸውን በመግለጽ የሟቾቹ ቁጥር ላይ ያላትን ተቃውሞ ገልጻለች።

ሐማስን በእርዳታ ማዕከላት አካባቢ ሁከት እንዲፈጠር አድርጓል ስትል ትከስሳለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የእርዳታ ቡድኖች እና አንዳንድ የእስራኤል አጋሮች በጋዛ የምግብ እጥረት እና ቀውስ እየተባባሰ መምጣቱን ሲገልጹ፣ በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ደግሞ በርካታ ሰዎች በተመጣጠነ ምግብ እጦት ምክንያት እየሞቱ እንደሆነ በመግለጽ እስራኤል እርዳታ ያለገደብ እንዲገባ እና እንዲዳረስ እንድትፈቅድ ጠይቀዋል።

ቅዳሜ ዕለት 85 ሕጻናትን ጨምሮ 125 ሰዎች በምግብ እጥረት ምክንያት መሞታቸው ይፋ ተደርጓል።

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ቴድሮስ አድሃኖም ገብረእየሱስ ቀውሱን "ሰው ሠራሽ የጅምላ ረሃብ" ሲሉ ገልጸውታል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል በበኩሉ በጋዛ ውስጥ ለሚኖረው ሕዝብ የምግብ ማከፋፈል ኃላፊነት "የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ነው" ካለ በኋላ አክሎም "እርዳታው ሐማስ ጋር አለመድረሱን ማረጋገጥ አለባቸው" ብሏል።

እስራኤል ቅዳሜ ዕለት የዮርዳኖስ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ መንግሥታት በዩኬ መንግሥት ድጋፍ ያገኘውን በአውሮፕላን እርዳታ መጣል የሚለውን ዕቅድ መቀበሏን አስታውቃለች። የእርዳታ ኤጀንሲዎች ግን እንዲህ ዓይነት እርምጃዎች በጋዛ የተከሰተውን ረሃብ ለመቅረፍ እምብዛም አይረዱም ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም የስደተኞች ኤጀንሲ ኃላፊ ፊሊፕ ላዛሪኒ ከአየር የሚጣሉ እርዳታዎች በእቅዱ መሰረት ካልሄዱ "ውድ፣ ብኩን እና የተራቡ ሰላማዊ ዜጎችን ሊገድሉ ይችላል" ብለዋል።

ላዛሪኒ ድርጅታቸው በዮርዳኖስና በግብፅ ወደ ጋዛ ለመግባት የሚጠባበቁ 6,000 የጭነት መኪኖች እንዳሉት ገልፀው እስራኤል "እገዳውን እንድታነሳ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እንቅስቃሴ እንዲኖር መተላለፊያዎችን እንድትከፍት እና ለተቸገሩ ሰዎች ተገቢውን ክብር በጠበቀ መልኩ ተደራሽነትን እንድታረጋግጥ" አሳስቧል።

ቢቢሲ ቅዳሜ ዕለት ያነጋገራቸው በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን ከአየር የሚጣሉ እርዳታዎች "ከባድ ጉዳት" ሊያስከትሉ ይችላሉ ብለው እንደሚሰጉ ተናግረዋል።

በጋዛ ሰርጥ ሰሜናዊ ክፍል የሚኖር አንድ ሰው ለቢቢሲ አረቢክ ሚድል ኢስት ዴይሊ ባለፈው ዓመት በነበረው ተመሳሳይ ጥረት ሂደቱ "አስተማማኝ ያልሆነ" እና "ብዙ አሳዛኝ ሁኔታዎችን የተፈጠሩበት" እንደነበር ተናግሯል።

"እርዳታ ከአየር ላይ በሚወርድበት ጊዜ በቀጥታ በድንኳኖች ላይ የማረፍ አደጋ አለው፤ ይህም ጉዳት ከማድረስ አልፎ ተርፎ ሞትን ሊያስከትል ይችላል" ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፍልስጤማውያን ከረሃብ ባሻገር በከፍተኛ የውሃ እጥረት እየተሰቃዩ ነው። አንዲት እናት ለቢቢሲ "የምኖረው የሚበላ እና የሚጠጣ በሌለበት ነው፤ ምግብ የለም፣ ዳቦ የለም፤ ውሃ እንኳን የለም" ብላለች።

ሐማስ በደቡብ እስራኤል መስከረም 26 2016 ዓ.ም. ድንገተኛ ጥቃት አድርሶ 1200 እስራኤላውያንን ከገደለ እና 251 ካገተ በኋላ የእስራኤል ጦር በጋዛ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍቷል።

በዚህም በሐማስ የሚመራው የጡና ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ እስካሁን ድረስ ከ59,000 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።