ፍልስጤም እንደ እስራኤል በአገርነት ለምን አልተመሠረተችም? የሁለት አገራት መፍትሄስ ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/BBC
በቅርቡ ሳዑዲ አረቢያ እና ፈረንሳይ ለአስርት ዓመታት የዘለቀውን ለፍልስጤም-እስራኤል ግጭት እልባት ለማበጀት በሚል የሁለት አገራት ምሥረታን አጀንዳ ያደረገ ከፍተኛ ጉባኤ በተባበሩት መንግሥታት መርተው ነበር። ጉባኤው በዋነኝነት ያለመው የፍልስጤምን አገርነት መሠረት መጣል ላይ ነበር።
ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የሁለት አገራት ምሥረታ ሂደት የራቀ ሃሳብ መስሎ ታይቷል።
እስራኤል በምላሹ ጋዛ ላይ የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት እየፈጸመች ሲሆን፣ ሁለት ታዋቂ የእስራኤል ሰብዓዊ መብት ድርጅቶችን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማት እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው ብለዋል።
በጋዛ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ አስከፊ በሆነበት በዚህ ወቅት የአረብ እና የአውሮፓ አገራት የሁለት አገራት ምሥረታ ሃሳብ እንዲታደስ እየሞከሩ ይገኛሉ።
ካናዳ፣ ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደም ለፍልስጤም አገርነት እውቅና እንሰጣለን ያሉ ምዕራባውያን አገራት ሆነዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የፍልስጤም አገርነት እውቅና እስራኤል ማሟላት ባለባት የተኩስ አቁም እና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ ነው።
እስራኤልም ሆነች የቅርብ አጋሯ አሜሪካ ለሁለት ቀናት የቆየውን ጉባኤ ካለመሳተፋቸው በተጨማሪ፤ አሜሪካ ጦርነቱን ለማስቆም በሚደረገው ጥረት ላይ "የማይጠቅም" ነው ስትል ተችታዋለች።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ጉባኤው "እንደ ወሳኝ የለውጥ መነሻ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። ወራራውን በማስቆም እንዲሁም በጋራ የምንመኘውን የሁለት አገራት ምሥረታ መፍትሄን በማይቀለበስ መልኩ ለማራመድ የሚያነሳሳ ሊሆን ይችላል" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሁለት አገራት መፍትሄ ምንድን ነው?
የሁለት አገራት መፍትሄ የሚባለው ከእስራኤል በተጨማሪ ድንበሩ የታወቀ እንዲሁም ደኅንነቷ የተጠበቀ የፍልስጤም አገር ምሥረታን የያዘ ነው።
ፍልስጤማውያን እስራኤል በወረራ በኃይል የተቆጣጠረቻቸውን የዌስት ባንክ እና የምሥራቅ ኢየሩሳሌም ግዛቶችን ያካተተች አገርን ለመመሥረት እየታገሉ ነው።
በአሁኑ ወቅት ያለው የእስራኤል መንግሥት የፍልስጤምን አገርነት እንዲሁም ሉዓላዊነት ይቃወማል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእስራኤል አቋም
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የፍልስጤምን የነጻ አገርነት ምሥረታን አጥብቀው የሚቃወሙ ሲሆን፣ የሁለት አገራት መፍትሄንም በፖለቲካ ሕይወታቸው በሙሉ ሲጻረሩት የኖረ ነው።
ኔታንያሁ ሐማስ ከፈጸመው ጥቃት ሁለት ሳምንታት በፊት በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለእስራኤል እና ለአረብ ጎረቤቶቿ "የሰላም ዘመን አዲስ መባቻ" በሚል ንግግር አድርገው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሩብ ምዕተ ዓመታት "ባለሙያ ነን ባሉ እስራኤል እንዲሁም የወደፊቷ ፍልስጤም በዮርዳኖስ ወንዝ እና በሜዲትራንያን የሚገኘውን መሬት ተጋርተው የሁለት አገራት መፍትሄ የሚሉ ሃሳብ አንድ የሰላም ስምምነት ማምጣት አልቻሉም" ብለዋል።
"በ2020 እኔ በተሟገትኩለት ዕቅድ በአጭር ጊዜ ውስጥ አስደናቂ እመርታ አገኘን። በአራት ወራት ውስጥ አራት የሰላም ስምምነቶችን ከአራት የአረብ አገራት ጋር መድረስ ችለናል" ብለዋል።
ኔታንያሁ የጠቀሱት በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን በአሜሪካ አሸማጋይነት የተደረሱትን "የአብርሃም ስምምነቶች" የተሰኙትን ነው።
ስምምነቱ ፍልስጤማውያን "እስራኤልን የማፍረስ ህልማቸውን ትተው እውነተኛ የሰላም መንገድ እንዲቀበሉ የሚያደርግ ነው" ብለዋል ኔታንያሁ።
ኔታንያሁ በመቀጠልም አዲሱን የመካከለኛው ምሥራቅ ካርታ ከፍ አድርገው ያሳዩ ሲሆን፣ በዚህም የሁለት አገራት መፍትሄ ማብቃቱን የሚጠቁም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሁለት አገራት መፍትሄ አመጣጥ እና የነበሩ ተስፋዎች
የሁለት አገራት ምሥረታ መፍትሄ አመጣጡ የተባበሩት መንግሥታት በአውሮፓውያኑ 1947 ፍልስጤምን ለሁለት የመክፈል ዕቅድ በወጠነበት ጊዜ ነው።
ብሪታኒያ በቅኝ ግዛት በኋላም በበላይነነት ታያት የነበረችውን ፍልስጤምን ለሁለት በመክፈል ሁለት አገራት መመሥረት የሚል ዕቅድ ነበር።
እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1948 በአገርነት ስትመሠረት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ያፈናቀለች ሲሆን፣ ይህንንም ፍልስጤማውያኑ "ናቅባ" (ታላቁ እልቂት) ሲሉ ይጠሩታል።
ከቀያቸው የተፈናቀሉት ፍልስጤማውያኑ አብዛኞቹ በጋዛ ሰፍረዋል።
በአሁኑ ወቅት ካሉ የጋዛ ነዋሪዎች መካከል ሦስት አራተኛውን የሚይዙት በዚያን ወቅት የተፈናቀሉ የልጅ ልጆች ናቸው።
ሌሎች 900 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ አሁን እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ ይኖራሉ።
በተጨማሪም 3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በዮርዳኖስ፣ በሶሪያ እና በሊባኖስ እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።
እስራኤል ከዚያም በኋላ በአውሮፓውያኑ 1967 በተደረገው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የፍልስጤማውያን ግዛት ተብለው የተከፈሉትን ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን ተቆጣጥራለች።
ሆኖም የሁለት አገራት ስምምነት ረቂቅ የመጣው ከዓመታት በኋላ በአውሮፓውያኑ 1993 ነበር።
እስራኤል እና ያሲር አረፋት የሚመሩት የፋታህ ክፋይ፣ የፍልስጤም ነጻ አውጭ ድርጅት (ፒኤልኦ) ኖርዌይ ከኋላ ሆና ባደረደረችው ስምምነት የጋራ ዕውቅና በመስጠት ነበር ስምምነቱ የተረቀቀው።
ሆኖም ይህ የኦስሎ ስምምነት ተግባራዊ መሆን አልቻለም።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በዚህ መሬት ለሰላም በተሰኘው ስምምነት መሠረት እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1967 በነበረው ጦርነት በወረራ የያዘቻቸው ግዛቶች ላይ የፍልስጤም ባለሥልጣን (ፖለስታይን ኦቶሪቲ) ራሱን በራሱ እንዲያስተዳደር እና አስተዳደር እንዲመሠርት ይላል።
ነገር ግን እስራኤል በወረራ የያዘቻቸውን ግዛቶች ላለመልቀቅ እንዲሁም የአይሁድ ሰፈራዎችን ማስፋት በመጀመሯ ሊሳካ አልቻለም።
በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት ፍልስጤም ለሁለት እንድትከፈል እና እስራኤል ተብላ በአገርነት ስትመሠረት በመቶ ሺዎች ያፈነቀለቻቸው ፍልስጤማውያን ወደቀያቸው በቋሚነት ያለመመለስ ጉዳይ እልባት ያገኘ ጉዳይ አይደለም።
እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1967 የጠቀለለቻት እና በሁለቱም ማኅበረሰቦች እንደ ቅዱስ ስፍራ የምትታየው ምሥራቅ የኢየሩሳሌም ጉዳይ አከራካሪነቱ ቀጥሏል።
ከዓመታት በኋላ በአውሮፓያኑ 2000 በዚያን ጊዜው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን አሰናጅነት በካምፕ ዴቪድ በነበረ የዝግ ስብሰባ ላይ የወቅቱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሁድ ባራክ እና የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዝዳንት አረፋት ቢገናኙም መፍትሄ ላይ ሳይደረስ ቀረ።
ሁለቱም ወገኖች ስምምነት ላይ ላለመደረሱ እርስ በርስ ተወቃቅሰዋል።
የእስራኤል እና አጋሯ አሜሪካ ባለሥልጣናት ያሲን አረፋት "ብዙ የሰጣቸውን" ስምምነት ውድቅ አድርገዋል ሲሉ ወቅሰዋቸዋል።
ፍልስጤማውያን በበኩላቸው ካነሷቸው በርካታ መስፈርቶች ለምሳሌ ምሥራቅ እየሩሳሌም የፍልስጤም መዲና መሆንን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮችን ስምምነቱ አለማሟላቱ "ማጭበርበሪያ" ሲሉ ጠርተውታል።
በአውሮፓውያኑ 1987 በጋዛ የተመሠረተው ሐማስ ይህንን የኦስሎን ስምምነት ፍልስጤማውያንን ያሳጣ ነው በሚል አልተቀበለውም።

የፎቶው ባለመብት, Uriel Sinai / Getty Images
ከኦስሎ በኋላ ምን ተፈጠረ?
ከኦስሎ ስምምነት በኋላ ፍልስጤማውያን የተነሱበት ሁለተኛው ኢንቲፋዳ (አመጽ) በአውሮፓውያኑ 2000 ተነሳ።
ለዚህም መነሻው የነበረው በወቅቱ የእስራኤል የተቃዋሚ መሪ የነበሩት ጄነራል አሪየል ሻሮን በወረራ በተያዘችው ምሥራቅ ኢየሩሳሌም በሚገኘው አል አቅሳ መስጊድ ግቢ ውስጥ አንድ ሺህ የሚሆኑ የታጠቁ ፖሊሶች እና ወታደሮች ውስጥ በድንገት ሰብረው መግባታቸው ነው።
ያንን የፍልስጤማውያኑን ተቃውሞ ተከትሎ የእስራኤል ፖለቲካ ወደ ቀኝ ክንፉ ማምራት ጀመረ።
ከኦስሎ ስምምነት ጀርባ የነበረው የእስራኤል ሌበር ፓርቲ የነበረው ተሰሚነት እየቀነሰ ሰፈራን የሚደግፈው ቀኝ አክራሪ ታዋቂ እየሆነ መጣ።
ተቃውሞ ያነሱት ፍልስጤማውያን በእስራኤል ወታደሮች በኃይለኛው ተመቱ።
በአውሮፓውያኑ 2001 ወደ ሥልጣን የመጡት አሪያል ሻሮን ካቢኔያቸው ፍልስጤማውያንን ከእስራኤላውያን የሚለይ ትልቅ አጥር እንዲገነባ አጸደቀ።
አረፋት እስካረፉበት የአውሮፓውያኑ 2004 ድረስ በራማላህ እንዲወሰኑ ተደረጉ።
የሰብዓዊ መብት ተቋማት ይህንን አጥር ሕገወጥ ሲሉ የሚፈርጁት ሲሆን፣ ሻሮን ይህንን የገነቡት እስራኤላውያንን ከፍልስጤም ጥቃት ለመከላከል ነው ብለዋል።
ሆኖም በሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት መሠረት ይህ በወረራ በተያዘችው ዌስት ባንክ ባሉ የእስራኤል ሰፈራዎችን አካባቢ ግንብ መገንባቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ከቀረው ዌስት ባንክ ለማቆራረጥ ነው ብሏል።
ሻሮን ከአውሮፓውያኖቹ 1970ዎቹ ጀምሮ ፍልስጤማውያንን በማፈናቀል በርካታ መንደሮችን ወደ እስራኤል ሰፈራ በመቀየር "የሰፈራ አባት" የሚል ስያሜ ማግኘታቸውን ሂውማን ራይትስ ዋች ከዓመታት በፊት ካወጣው ጽሁፍ መረዳት ይቻላል።
ከዚያ በኋላም ፖለቲካዊ ድርድሮች አልቀጠሉም።
በተጨማሪም እስራኤል በግብፅ ትብብር ጋዛን ሙሉ በሙሉ ዘጋቻት።
በጋዛ ታጣቂዎች ሮኬት የሚያስወነጭፉ ሲሆን፣ እስራኤል በበኩሏ የቦምብ ጥቃቶችን እንዲሁም የእግርኛ ሠራዊት ጥቃቶቿን ቀጠለች።
በአውሮፓውያኑ 2006 በፍልስጤም አስተዳደር በተካሄደ የምክር ቤት ምርጫ ሐማስ አብላጫ ድምጽ መያዝ ቻለ። በርካቶች ፋታህ የፍልስጤም ነጻነትን ማምጣት ባለመቻሉ ተሰላችተው ስለነበረ ነው ሐማስን የመረጡት።
ሆኖም ሐማስ የፍልስጤምን አስተዳደር ከጋዛ በኃይል ማስወጣቱን ተከትሎ ጋዛን የትጥቅ ትግል ማዕከል በማድረግ ዌስት ባንክን ከሚመራው እና በኦስሎ ሰላም ስምምነቶች እመራለሁ ከሚለው ፋታህ ተነጠለች።
ሐማስ በተጨማሪም በጋዛ ወታደራዊ አቅሙን ጨምሮ ከሊባኖሱ ሔዝቦላህ ጋር በመተባበር 'አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ' በሚል ጥምረት ከእስራኤል ጋር ሲፈላሙ ቆይተዋል።
ነገር ግን ሐማስ ከረጅም ጊዜ በኋላ የትጥቅ ትግልን በማቆም እስራኤል በወረረቻቸው ግዛቶች የፍልስጤምን አገር የመመሥረት እንዲሁም የፖለቲካ ውይይቶች ሊኖር እንደሚችል የሚጠቁሙ አቋሞችን አንጸባርቋል።
ሆኖም ሐማስ እስራኤል እንድትጠፋ የሚጠይቀውን አንቀጽ ከቻርተሩ ያላወጣ ሲሆን፣ በርካታ አመራሮቹን የገደለችው እስራኤል መቼም ቢሆን ሐማስን ሳላጠፋው አልቀርም ስትል ይሰማል።
እስራኤል በጋዛ ከምትፈጽማቸው ጥቃቶች በተጨማሪ በወረራ በያዘቻቸው ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌም ሰፈራዎችን እያስፋፋች ትገኛለች።
ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ለ700 ሺህ አይሁዳውያን መኖሪያ የሚሆኑ 160 ሰፈራዎችን ገንብታለች። በዌስት ባንክ 3.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ይኖራሉ።
አብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እስራኤል እያደረገችው ያለውን ሰፈራ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገወጥ ነው ሲል ይኮንናል።
እስራኤል ግን ይህንን አትቀበልም።

የፎቶው ባለመብት, Jaafar Ashtiyeh / AFP via Getty Image
በእስራኤል በተከታታይ የመጡ አስተዳደሮች ሰፈራዎች እንዲስፋፉ አድርገዋል።
ይሁን እንጂ ሰፈራን የሚደግፈው የቅኝ ክንፍ አክራሪዎች ጥምረት የሆነውን መንግሥት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድጋሚ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ሰፈራዎች እየተስፋፉ ይገኛሉ።
የጋዛ ጦርነትም እንዲሁ ለእነዚህ ሰፈራዎች መበራከት በር መክፈቱም ተነግሯል። ሰፈራዎች መስፈፋት ብቻ ሳይሆን ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያኑ ላይ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች መባባሱም ተገልጿል።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ የጋዛ ጦርነት ከተነሳ ጀምሮ በዌስት ባንክ ቢያንስ 975 ፍልስጤማውያን በእስራኤል የፀጥታ ኃይሎች እና በእስራኤል ሰፋሪዎች ተገድለዋል።
የመስከረም 2015 ዓ.ም. ጥቃት ተከትሎ ኔታንያሁ በፍልስጤም አገርነት ምሥረታ ላይ የሚያነሱትን ተቃውሞ በጽኑ የቀጠሉ ሲሆን "የእስራኤልን ኅልውና አደጋ ውስጥ የሚከት ነው" ሲሉም ተሰምተዋል።
ኔታንያሁ የጋዛ ሰርጥ እና ዌስት ባንክን ጨምሮ "ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ በሚገኙ ሁሉም ግዛቶች ላይ በበላይነት ጥበቃውን እንደሚይዙ" ተናግረዋል።
የእስራኤል ፓርላማ በቅርቡ የፍልስጤም አገርነት መመሥረትን ውድቅ የሚያደርግ የውሳኔ ሃሳብ አጽድቋል።
የቀኝ ክንፍ አክራሪ የኔታንያሁ ደጋፊዎቹ እስራኤል ጋዛን ጨምሮ የፍልስጤማውያንን መሬት በሙሉ እንድትጠቀልል ሲናገሩ ይደመጣሉ።
አንዳንዶቹ ደግሞ ፍልስጤማውያን በሙሉ ከጋዛ ለዘለቄታው በግዳጅ እንዲፈናቀሉ የሚሉ ሃሳቦችን ይወረውራሉ።
የእስራኤል ጦር በቅርቡ በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያንን በሙሉ አፈናቅሎ በደቡባዊ ክፍል በሚዘጋጅ ካምፕ ለማስገባት ዕቅድ እንዲያዘጋጅ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ትዕዛዝ መስጠታቸው ተዘግቧል።
በራፋህ ከተማ ፍርስራሽ ላይ "ሰብዓዊ ከተማ" በማቋቋም በመጀመሪያ 600 ሺህ ፍልስጤማውያን የሚቆዩበት ካምፕ ከዚያም አጠቃላይ 2.1 ሚሊዮን የጋዛን ሕዝብ የሚያኖር ነው ተብሏል። ፍልስጤማውያኑ ከካምፑ መውጣት እንደማይፈቀድላቸው ተገልጿል።
የሐማስ ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎችን እንዲሁም የኢራንን ወታደራዊ መሪዎችን የገደለችው እና ሔዝቦላህን ያዳከመችው እስራኤል በጋዛ ከ60 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን መገደላቸውን ተከትሎ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ወደ ሰላም እንድትገባ እያደረገው ያለው ጫና ጨምሯል።
በአረብ አገራት እና በአውሮፓውያኑ የተደገፈው የተባባሩት መንግሥታት ጉባኤ እንዲሁም በቅርቡ እንደ ፈረንሳይ እና ካናዳ ያሉ አገራት ለፍልስጤም አገርነት እውቅና እንሰጣለን ማለታቸውን ተከትሎ እስራኤል ወደ ሁለት አገር መፍትሄ እንድትመጣ ያደርጋታል የሚል እሳቤ አለ።
በታሪክ የሁለት አገራት መፍትሄን ስትሻ የነበረችው አሜሪካ ከዚህ ሃሳብ ርቃለች።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህንን የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤን ቢቃወሙም የሁለት አገራት መፍትሄ ላይ ያላቸውን አቋም ግልጽ አላደረጉም።
በቅርቡ የረጅም ጊዜ መፍትሄ ላይ እንዲደረስ እስራኤል ላይ ጫና ሊደረግባት ይገባ ይሆን ሲሉ የተጠየቁት ትራምፕ፣ ሐማስን እንደመሸለም ሊቆጠር ይችላል ብለዋል።
የሁለት አገር መፍትሄ ውይይቶችን ለማደስ በሚደረገው ጥረት የአሜሪካ ድጋፍ ከሌለ ወደፊት ሊራመድ ይችል ይሆን በሚለው ላይ ጥያቄ ያጭራል።















