ካናዳ ለፍልስጤም አገርነት እውቅና ልትሰጥ ነው

የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ በመጪው መስከረም ፍልስጤምን በአገርነት እውቅና እንደሚሰጡ ገለጹ።

ካናዳ ይህንን ማስታወቋን ተከትሎ ፍልስጤምን በአገርነት ዕውቅና እንሰጣለን ያለች ሶስተኛዋ የቡድን ሰባት (ጂ7) አባል አገር ሆናለች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ዕውቅና በዲሞክራሲያዊ ማሻሻያዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸው ፤ የፍልስጤም አስተዳደር በሚቀጥለው ዓመት ያለ ሐማስ ምርጫ ማድረግን ያካትታል ብለዋል።

ወደ 200 የሚጠጉ የቀድሞ የካናዳ አምባሳደሮች እንዲሁም ዲፕሎማቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፍልስጤም አገርነት እውቅና እንዲሰጡ ፊርማቸውን ባኖሩበት ደብዳቤ ጠይቀዋል።

"ፍልስጤማውያን በየቀኑ በከፍተኛ ሁኔታ መጠነ ሰፊ መፈናቀል፣ ማንንም የማይለይ የቦምብ ድብደባ እንዲሁም በጋዛ ሰላማዊ ዜጎች እየተራቡ እና በዌስት ባንክ ጽንፈኛ ሰፋሪዎች በሚያደርጓቸው ከፍተኛ ጥቃቶች የካናዳን መርሆች ተዘንግተዋል" ብለዋል።

የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር አስተያየት የተሰማው ዩናይትድ ኪንግደም እስራኤል ለተኩስ አቁም እንዲሁም ሌሎች ሁኔታዎች የማትስማማ ከሆነ ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና እንሰጣለን ካሉ በኋላ ነው።

የዩናይትድ ኪንግደም የፍልስጤም አገርነት እውቅና እስራኤል ማሟላት ባለባት ቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተመሰረተ ሲሆን ፤ከዚያ ቀደም ብሎ ግን ፈረንሳይ በመጪው መስከረም ለፍልስጤም አገርነት እውቅና እሰጣለሁ ብላለች።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የካናዳና ፍልስጤምን በአገርነት እውቅና እሰጣለሁ ማለቷን "ለሐማስ ሽልማት ነው" ሲል ተችቶታታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአሁኑ ወቅት ከ193 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት መካከል 140ዎቹ ፍልስጤምን በአገርነት ዕውቅና ሰጥተዋታል።

ከነዚህም መካከል ስፔንና አየርላንድን ጨምሮ ጥቂት የአውሮፓ ህብረት አባላት አገራት ይገኙበታል።

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ከፈረንሳዩ መሪ ጋር በተመሳሳይ መልኩ ፍልስጤምን በአገርነት በይፋ እውቅና የመስጠት እወጃው የሚደረገው በኒውዮርክ በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ እንደሆነ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ እስራኤል በወረራ በያዘቻት ዌስት ባንክ የምታደርገው መስፋፋት መጠናከሩን፣ የጋዛ ሰብዓዊ ቀውስ መክፋት እንዲሁም ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመው ጥቃት ለአገራቸው የውጭ ፖሊሲ ለውጥ ምክንያቶች እንደሆነ ጠቅሰዋል።

"በጋዛ ያለው የሰዎች ሰቆቃ ደረጃ ልንታገሰው በማንችለው እና በፍጥነት እየከፋ ነው" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ረቡዕ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና መስጠት የፍልስጤም አስተዳደር፣ ግዛቱን ከወታደራዊ ትጥቅ ውጭ በማድረግ አስተዳደሩን በመሰረታዊ መልኩ ከማሻሻል ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል።

ካናዳ በድርድር የሁለት አገራት መመስረት እንደ መፍትሄ ስታየው ቆይታለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኖም "ይህ አካሄድ ከአሁን በኋላ ሊተገበር የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል" ብለዋል።

"የፍልስጤም አገር ምስረታ ተስፋ አይናችን እያየ እየተሸረሸረ ነው" ሲሉ አክለዋል።

ካርኒ ፍልስጤምን በአገርነት እውቅና እንደሚሰጡ ለፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ እንደነገሯቸው በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

የፍልስጤም አስተደር የተወሰነውን የዌስት ባንክ ግዛቶችን የሚያስተዳድር ሲሆን ሐማስ ደግሞ ጋዛን ይመራል።

እስራኤል በአገርነት፣ በአውሮፖውያኑ 1948 ስትመሰረት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ያፈናቀለች ሲሆን ይህንንም "ናቅባ" (ትልቁ እልቂት) ሲሉ ይጠሩታል።

በአሁኑ ወቅትም ፍልስጤማውያኑ ይኸው ይደገማል በሚል ፍራቻ ላይ ናቸው።

ከቀያቸው የተፈናቀሉት ፍልስጤማውያኑ አብዛኛዎቹ በጋዛ ሰፍረዋል።

በአሁኑ ወቅት ካሉ የጋዛ ነዋሪዎች መካከል ሶስት አራተኛውን የሚይዙት በዚያን ወቅት የተፈናቀሉ የልጅ ልጆች ናቸው።

ሌሎች 900 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ አሁን እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ ይኖራሉ።

3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በዮርዳኖስ፣ ሶሪያ እና ሊባኖስ እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።

እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1967 በተደረገው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ነው የፍልስጤማውያኑ ግዛት የሆኑትን ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን የተቆጣጠረችው።

ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ለ700 ሺህ አይሁዳውያን መኖሪያ የሚሆኑ 160 ሰፈራዎችን ገንብታለች። በዌስት ባንክ 3.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ይኖራሉ።

አብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እስራኤል እያደረገችው ያለውን ሰፈራ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገወጥ ነው ሲል ይኮንናል።

እስራኤል ይህንን አትቀበልም።

በእስራኤል በተከታታይ የመጡ አስተዳደሮች ሰፈራዎች እንዲስፋፉ አድርገዋል።

ይሁን እንጂ ሰፈራን የሚደግፈው የቅኝ ክንፍ አክራሪ ጥምረት የሆነውን መንግሥት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድጋሚ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ሰፈራዎች እየተስፋፉ ይገኛሉ።

የጋዛ ጦርነትም እንዲሁ ለእነዚህ ሰፈራዎች መጨመር በር መክፈቱም ተነግሯል። ሰፈራዎች መስፈፋት ብቻ ሳይሆን ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያኑ ላይ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች መባባሱም ተገልጿል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ የጋዛ ጦርነት ከተነሳ ጀምሮ በዌስት ባንክ ቢያንስ 975 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጸጥታ ኃይሎች እና በእስራኤል ሰፋሪዎች ተገድለዋል።