ለፍልስጤም አገርነት እውቅና መስጠት የከፈታቸው ሌሎች ጥያቄዎች፡ ማን ይመራታል?

በዚህ ወር መጀመርያ ላይ የፍልስጤም ዲፕሎማት የሆኑት ሁደሳም ዞምሎት ለንደን በሚገኘው ቲንክ ታንክ ቻተም ሀውስ ለውይይት ግብዣ ቀርቦላቸው ተግኝተዋል።
ቤልጂየም በመንግሥታቱ ድርጅት ስብሰባ ወቅት ለፍልስጤም የአገርነት እውቅና ለመስጠት ቃል የገቡትን ዩኬ ፈረንሳይ እና ሌሎች አገራትን ተቀላቅላለች።
የፍልስጤም ሚሽን በዩኬ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ዞምሎት ይህ ወሳኝ ጊዜ መሆኑ ገብቷቸዋል።
"በኒውዮርክ የምታዩት የሁለት አገርነት መፍትሄ ትግበራ የመጨረሻ ሙከራን ይሆናል" ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
"ይህ ሊያመልጠን አይገባም።"
ጊዜው ደርሶ የእስራኤል ጠንካራ አጋር የሆኑት ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ እና አውስትራሊያ ለፍልስጤም የአገርነት እውቅና በመስጠት እርምጃ ወስደዋል።
ሰር ኪር ስታርመር በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋሩት የቪዲዮ መልዕክት ላይ የዩኬን ውሳኔ ይፋ አድርገዋል።
በመልዕክታቸው ላይ "በመካከለኛው ምሥራቅ እያደገ በመጣው ጭካኔ ፊት፣ ለሰላም ያሉ ዕድሎችን እና የሁለት አገርነት መፍትሄ በሕይወት ለማቆየት እርምጃ እየወሰድን ነው" ብለዋል።
"ያ ማለት ከእስራኤል ጎን ደህንነቷ የተጠበቀ እና ሰላም የሆነች ፍልስጤም ነው፤ አሁን ግን ሁለቱም የሉንም።"
ከዚህ በፊት ከ150 በላይ አገራት ለፍልስጤም የአገርነት እውቅና የሰጡ ቢሆንም የዩኬ እና የሌሎች አገራት መጨመር ግን በበርካቶች እንደ ተጨባጭ እርምጃ ታይቷል።
"ዓለም ከፍልስጤም ጎን ቆሟል።"
ነገር ግን ሌላ መመለስ ያለባቸው ውስብሰብ ጥያቄዎች አሉ፤ እነዚያም ፍልስጤም ምንድን ነች እና እውቅና ልንሰጠው የምንችለው አገር አለ? የሚሉት ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Shutterstock
እአአ በ1933 በሞንቴቪዲዮ ኮንቬንሽን ላይ አራት መስፈርቶች ተዘርዝረዋል።
ፍልስጤም ሁለቱ ይመለከተኛል ስትል ትጠቅሳለች።
ቋሚ የሆነ ሕዝብ (በጋዛ ያለው ጦርነት ይህንን በከፍተኛ ሁኔታ አደጋ ላይ ቢጥለውም) እና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ውስጥ ለመግባት ያለ አቅም መሆናቸውን ዶ/ር ዞምሎት ይጠቅሳሉ።
ነገር ግን "ግልጽ የሆነ ግዛት" የሚለውን አታሟላም።
የፍልስጤም ድንበር ላይ ግልጽ የሆነ ስምምነት ባለመኖሩ (የሰላም ሂደትም አለመኖሩ ተጨምሮ) ፍልስጤም ማለት ምን ማለት መሆኑን በግልጽ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው።
ፍልስጤማውያን ራሳቸው ለረዥም ጊዜ ሲጠይቁት የቆዩት አገርነት ሦሰት ክፍሎችን ያዘ ነው።
ምሥራቅ እየሩሳሌም፣ ዌስት ባንክ እና የጋዛ ሰርጥ።
ሁሉም እአአ በ1967 በተካሄደው የስድስት ቀኑ ጦርነት በእስራኤል በወረራ ተይዟል።
የፍልስጤምን ካርታ የሚመለከት ማንኛውም ሰው ችግሩ የት ላይ እንደሚጀምር በቀላሉ ይታየዋል።
ዌስት ባንክ እና የጋዛ ሰርጥ ከእስራኤል ነጻነት እአአ 1948 ጀምሮ ላለፉት ሰባት አስርት ዓመታት ተለያየተው ነው ያሉት።
እአአ በ1990 ከኦስሎ የሰላም ስምምነት በኋላ የተመሰረተው የፍልስጤም አስተዳደር በዌስት ባንክ የእስራኤል ጦር እና የአይሁድ ሰፋሪዎች በመኖራቸው የተነሳ የሚያስተዳድረው የግዛቱን 40 በመቶ ብቻ ነው።
እአአ ከ1967 ጀምሮ የሰፋሪዎች መስፋፋት ዌስት ባንክን ዕለት በዕለት እየቀነሳት፣ ወደ ተበታተነ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ቡድን ቀይሯታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፍልስጤማውያን እንደ ዋና ከተማቸው የሚቆጥሯት የምሥራቅ እየሩሳሌም በአይሁድ ሰፋሪዎች የተከበበች ሲሆን ቀስ በቀስ ከዌስት ባንክ እየቆረጣት ይገኛል።
የጋዛ እጣ ፈንታ ደግሞ እንዲሁ ከሁሉ የባሰ ነው።
መስከረም 26/2016 ዓ.ም. ሐማስ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የተቀሰቀሰው እና ላለፉት ሁለት ዓመት የተካሄደው ጦርነት አብዛኛውን የግዛቱን አካል አውድሞታል።
ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ነገሮችን ለማስተካከል በቂ ያልሆኑ ያህል በሞንቴቪዲዮ ኮንቬንሽን ላይ አንድን አገር እውቅና ለመስጠት በሚል የተቀመጠ አራተኛ መስፈርት አለ፤ የሚሰራ መንግሥት።
ይህ ደግሞ ለፍልስጤማውያን ግዙፍ ተግዳሮት ሆኖ የተቀመጠ ነው።
"አዲስ አመራር እንፈልጋለን"
እአአ በ1994 በእስራኤል እና በፍልስጤም ነፃ አውጭ ድርጅት (PLO) መካከል የተደረገ ስምምነት የፍልስጤም ብሄራዊ ባለስልጣን (የፍልስጤም አስተዳደር) እንዲመሰረት አድርጓል።
አስተዳደሩ በጋዛ እና በዌስት ባንክ በፍልስጤማውያን ላይ በከፊል የሲቪል ቁጥጥር ያደርጋል።
ነገር ግን እአአ በ2007 በሐማስ እና በዋናው የፍልስጤም አስተዳደር አንጃ ፋታህ መካከል ደም አፋሳሽ ጦርነት ከተካሄደ በኋላ በጋዛ እና ዌስት ባንክ የሚኖሩ ፍልጤማውያን በሁለት ተቀናቃኝ መንግሥቶች ነው የሚተዳደሩት።
በጋዛ ሐማስ፣ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የፍልስጤም አስተዳደር ደግሞ ፕሬዚዳንቱን ማሃሙድ አባስ በማድረግ ዌስት ባንክን ያስተዳድራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዌስት ባንክን እና የጋዛ ሰርጥ ላለፉት 77 ዓመታት በመልክዓ ምድር ለ18 ዓመታት ደግሞ በፖለቲካ በመከፋፈላቸው ለረዥም ጊዜ ተለያይተው ኖረዋል።
በዚህ መካከል ደግሞ የፍልስጤም ፖለቲካ ውዥንብር ውስጥ ገብቷል።
አብዛኞቹ ፍልስጤማውያን በአመራራቸው ላይ ጥርጣሬ ያላቸው ሲሆን አንድ አገር የመሆን ተስፋቸው ሰልሏል።
ያ ብቻ ሳይሆን በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ማንኛውም ዓይነት የእርቅ ዕድል ይኖራል የሚለው ፍላጎትም ተመናምኗል።
በፍልስጤም የመጨረሻው የፕሬዚዳንታዊ እና የፓርላማ ምርጫ የተካሄደው እአአ በ2006 ነበር።
ይህ ማለት ከ36 ዓመት በታች የሆነ ፍልስጤማዊ በዌስት ባንክ ወይም በጋዛ ድምጽ አልሰጠም።
ፍልስጤማዊ ጠበቃ ዲያና ቡቱ "በዚህ ሁሉ ጊዜ ምርጫ አላደረግንም መባሉ የሚከነክን ነው" ብለዋል።
አክለውም "አዲስ አመራር እንፈልጋለን"።
መስከረም 2016 ዓ.ም. በጋዛ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ጉዳዩ ይበልጥ አሳሳቢ ሆኗል።
የአባስ የፍልስጤም አስተዳደር በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቹን ሞት በዌስት ባንክ ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤቱ ሆኖ በመመልከት በአመዛኙ ረዳት አልባ ሆኖ እንዲታይ ተደርጓል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለዓመታት የዘለቀው ውስጣዊ አለመግባባት
በፍልስጤም አመራር መካከል ያለው ውጥረት ለዓመታት የዘለቀ ነው።
የፍልስጤም ነጻ አውጪ ድርጅት ሊቀመንበር የነበሩት ያሲር አራፋት ከዓመታት ስደት በኋላ ተመልሰው የፍልስጤም አስተዳደርን ለመምራት ሲመጡ፣ በአገር ውስጥ የነበሩ የፍልስጤም ፖለቲከኞች በአብዛኛው ወደ ጎን ገለል ተደርገዋል።
በአረፋት ዙሪያ የተሰባሰቡ "የቅርብ ሰዎች" ሌሎቹን በጥርጣሬ የሚመለከቱ ሆኑ።
በአራፋት ዙሪያ የተሰባሰቡት ፖለቲከኞች በሙስና መዘፈቃቸው እየተወራ ሲመጣ ደግሞ የፍልስጤም አስተዳደርን ስም ለመታደግ አዳጋች እየሆነ መጣ።
አዲስ የተቋቋመው የፍልስጤም አስተዳደር፣ እአአ በመስከረም 1993 በዋይት ሐውስ ከቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ይስሃቅ ራቢን ጋር ከተጨባበጠ በኋላ ለነጻነት እና ሉዓላዊነት የገባው ቃል አብቅቶ እስራኤል ቀስ በቀስ በዌስት ባንክ የምታደርገውን ወረራ እና ቅኝ ግዛት ማስቆም ሳይችል ቀረ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቀጣዮቹ ዓመታት ለሰላማዊ ፖለቲካ ለውጥ ምቹ አልነበሩም።
ውጤታማ መሆን ያልቻሉ የሰላም ጥረቶች፣ የአይሁድ ሰፈራ መስፋፋት፣ የሁለቱም ዋልታ ረገጥ ኃይሎች ጥቃት፣ የእስራኤል የፖለቲካ ወደ ቀኝ መንሸራተት እና እአአ በ2007 በሐማስ እና በፋታህ መካከል የተፈጠረው በጦር መሣሪያ የታገዘ ግጭት ነገሮችን አከፋቸው።
ፍልስጤማዊው የታሪክ ምሁር ዬዚድ ሳይይ "በተለመደው ሁነት ቢሆን አዳዲስ አመራሮች፣ አዳዲስ ትውልዶች ብቅ ይሉ ነበር" ይላሉ።
"ነገር ግን ያ የማይቻል ነበር… በወረራ የተያዙት ግዛቶች ውስጥ ያሉ ፍልስጤማውያን በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ተለያዩ ትናንሽ ቦታዎች ተከፋፍለዋል፤ እና ይህም አዳዲስ አመራሮች እንዳይወጡ እና ሕዝቡን እንዳያሰባስቡ አድርጓል።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዚህ ወቅት አንድ መሪ ብቅ አለ፤ ማርዋን ባርጋውቲ።
በዌስት ባንክ ተወልዶ ያደገው ባርጋውቲ፣ በ15 ዓመቱ በአራፋት የሚመራው የፍልስጤም ነጻ አውጪ ድርጅት፣ ፋታህ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ጀመረ።
ባርጋውቲ አምስት እስራኤላውያን የተገደሉበትን ጥቃት በማቀድ ከመታሰሩ በፊት በሁለተኛው የፍልስጤም አመፅ ወቅት ታዋቂ መሪ ሆኖ ብቅ አለ።
በርግጥ ክሱን ቢክድም እአአ ከ2002 ጀምሮ በእስራኤል እስር ቤት ውስጥ ይገኛል።
አሁንም ፍልስጤማውያን ወደፊት መሪዎች ሊሆኑ ስለሚችሉ ግለሰቦች ሲናገሩ፣ ወደ ሩብ ምዕተ ዓመት ገደማ ታስሮ ስላለው ባርጋውቲ ይናገራሉ።
በቅርቡ በዌስት ባንክ የፍልስጤም የፖሊሲ እና የዳሰሳ ጥናት ማዕከል በሰበሰበው የሕዝብ አስተያየት ላይ 50 በመቶ ፍልስጤማውያን ባርጋውቲን በፕሬዚዳንትነት የሚመርጡ መሆናቸው ተመልክቷል፤ ይህም እአአ ከ2005 ጀምሮ በሥልጣን ላይ ካሉት አባስ በጣም የበለጠ ቁጥር ነው።
ከሐማስ ጋር ለረዥም ጊዜ ሲጋጭ የቆየው የፋታህ ከፍተኛ አባል ቢሆኑም፣ ሐማስ በጋዛ ያገታቸውን እንዲለቅ በምላሹ እስራኤል ፍልስጤማውያን እስረኞችን እንድትለቅ ሲደራደር ስማቸውን ከሰጣቸው የፖለቲካ እስረኞች መካከል ባርጋውቲ ከፊት ይገኛሉ።
ነገር ግን እስራኤል ባርጋውቲን ለመልቀቅ ፈቃደኛ መሆንዋን የሚያሳይ ምንም ዓይነት ፍንጭ አላሳየችም።
በነሐሴ አጋማሽ ላይ የ66 ዓመት አዛውንት ባርጋውቲ ከስተው እና ደካማ ሆነው የእስራኤል የደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ጊቪር ሲሳለቁባቸው የሚያሳይ ቪዲዮ ወጣ።
ባርጋውቲ ከዓመታት በኋላ በአደባባይ ሲታዩ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር።
ኔታንያሁ እና የፍልስጤም አገርነት
ቤንያሚን ኔታንያሁ ከጋዛ ጦርነት በፊትም የፍልስጤም አገርነት እንደሚቃወሙ አሻሚ አልነበረም።
እአአ በ2024 "ፍልስጤም አገር መሆኗ የእኛ ኅልውና ላይ አደጋ ላይ ስለሚጥል ለአስርታት ዓመታት ስከላከል የኖርኩ መሆኔን ሁሉም ያውቃል" ብለው ነበር።
የፍልስጤም አስተዳደር ጋዛን እንዲቆጣጠር ዓለም አቀፍ ጥሪ ቢቀርብም ኔታንያሁ ግን አባስ የመስከረም 26ቱን የሐማስ ጥቃት አላወገዙም በማለት በጋዛ የወደፊት አስተዳደር ላይ ምንም ዓይነት ሚና እንደማይኖረው ተናግረዋል።
በነሐሴ ወር እስራኤል ምሥራቅ እየሩሳሌምን ከዌስት ባንክ ለሚለያይ የሰፈራ ፕሮጀክት ይሁንታን ሰጥታለች።
በዚህ ዕቅድ ላይም 3,400 ቤቶች እንደሚገነቡ የተገለፀ ሲሆን የእስራኤል የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች ዕቅዱ የፍልስጤም የአገርነት ሀሳብ የሚቀብር ነው ብለዋል።
"ምክንያቱም ዕውቅና የሚሰጠው እና ማንም ዕውቅና የሚሰጥ የለም" ብለዋል።
ሳይይ ይህ ምንም አዲስ ነገር አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ።
"አማልክትን የፍልስጤም አስተዳደር እንዲመሩት ማድረግ ትችላላችሁ። ነገር ግን ምንም ለውጥ አያመጣም። ምክንያቱም የትኛውንም ዓይነት ስኬት ፈጽሞ የማይቻል በሚያደርጉ ሁኔታዎች ውስጥ መሥራት አለባቸው። እና ይህ ለረጅም ጊዜ የነበረ ነው።"
አንድ የተረጋገጠው ነገር ፍልስጤም እንደ አገር ከተመሰረተች ሐማስ አይመራትም።
በፈረንሣይ እና ሳዑዲ አረቢያ ድጋፍ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ኮንፈረንስ በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ያወጣው መግለጫ "ሐማስ በጋዛ ያለውን አገዛዝ በማቆም የጦር መሳሪያዎቹን ለፍልስጤም አስተዳደር ማስረከብ አለበት" ይላል።
ይህ "የኒውዮርክ ስምምነት" በሁሉም የአረብ አገራት የፀደቀ ሲሆን በመቀጠልም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 142 የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ተቀባይነት አግኝቷል።
ሐማስ በበኩሉ የጋዛን ሥልጣን ለቴክኖክራቶች ገለልተኛ አስተዳደር ለማስረከብ ዝግጁ ነኝ ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እውቅናን መስጠት ብቻ በቂ ነው?
ባርጋውቲ በእስር ላይ እያሉ አባስ 90 ዓመት ሊሞላቸው ነው።
ሐማስ እየተዳከመ፣ ዌስት ባንክ ተሸንሽና ፍልስጤም አመራር እና ቅንጅት እንደሌላት ግልጽ እየሆነ ነው።
ይህ ማለት ግን ዓለም አቀፍ እውቅና ትርጉም የለውም ማለት አይደለም።
ዲያና ቡቱ "ይህ በእውነቱ በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል" በማለት "እነዚህ አገሮች ለምን እንደሚያደርጉት እና ፍላጎታቸው ምን ድን ነው በሚለው ላይ ይወሰናል" ብላለች።
አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የብሪታኒያ መንግሥት ባለስልጣን ደግሞ እውቅና ለይስሙላ ብቻ መሆን እንደሌለበት ይናገራሉ።
"ጥያቄው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ እውቅና የሚሰጥ ፓርቲ ብቻ እንዳይሆን ወደ አንድ ነገር ማምጣት እንችላለን ወይ ነው።"
በኒውዮርክ ስምምነት ላይ የፈረሙት አገራት ብሪታንያንን ጨምሮ "የፍልስጤም ጥያቄን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተጨባጭ፣ በጊዜ የተገደበ እና የማይቀለበስ እርምጃ እንደሚወስዱ ቃል ገብተዋል።"
የዩኬው ባለሥልጣን የጋዛን እና የዌስት ባንክን ውህደት፣ ለፍልስጤም አስተዳደር ድጋፍ እና የፍልስጤም ምርጫን (እንዲሁም በጋዛ የአረብ አገራት የመልሶ ግንባታ ዕቅድ) እውቅናን መከተል ያለባቸው እርምጃዎች መሆናቸውን ይጠቁማሉ ።
ነገር ግን እንቅፋቶቹ ከባድ መሆናቸውን ያውቃሉ።
እስራኤል ግልጽ በሆነ መልኩ ተቃውሞዋን በመቀጠል በከፊል ወይም ሁሉንም የዌስት ባንክን ክፍል በመገንጠል አጸፋ እንደምትሰጥ ዝታለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በተገናኙ ወቅት በጉዳዩ ላይ ቅሬታቸውን ገልፀው "በዚህ ነጥብ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር አልስማማም" ብለዋል።
በነሐሴ ወር አሜሪካ ለበርካታ የፍልስጤም ባለሥልጣናትን ቪዛ የመሰረዝ ወይም የመከልከል ያልተለመደ እርምጃ ወስዳለች።
አሜሪካ በተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም መንግሥት እውቅና ላይ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማለች።
ዶናልድ ትራምፕ ጋዛን የመጠቅለል ሃሰብ አላቸው። "ጋዛን እንወስዳታለን፣ እንቆጣጠራታለን፣ ውብ እናደርጋታለን" ብለዋል።
በርካታ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ሆቴሎችን፣ መኖርያ ቤቶችና ቢሮዎችን በጋዛ እንደሚገነቡም ፍንጭ ሰጥተዋል።
በዚህም ለዮርዳኖስ ዜጎችና ለሌሎች ብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጠራል ብለዋል።
ሁሉም ዕቅዶች፣ በየራሳቸው እጅጉን በተለያየ መንገድ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በጋዛ ከደረሰው አደጋ አንድ ነገር ለማግኘት ተስፋ ያደርጋሉ።
እና ምንም ዓይነት መፍትሄ ቢመጣ ፍልስጤም እና አመራሯ ምን ይመስላሉ የሚለውን ጥያቄ መመለስ አይችሉም።
እንደ ዳያና ቡቱ ላሉ ፍልስጤማውያን ግን የበለጠ አሳሳቢ ጉዳይ አለ። እሷ በእርግጥ የምትመርጠው እነዚህ አገራት ተጨማሪ ግድያን እንዲያስቀሩ ነው።
"እና በመንግሥት ጉዳይ ላይ ከማተኮር ይልቅ ግድያን የሚያስቆም አንድ ነገር ያድርጉ።"















