እስራኤል "የፍልስጤምን የአገርነት ጥያቄ ለመቅበር" የወጠነችበት አወዛጋቢው ሰፈራ ምንድን ነው?

እስራኤል በኃይል በያዘችው ዌስት ባንክ ያቋቋመችው ሰፈራ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, እስራኤል በኃይል በያዘችው ዌስት ባንክ ያቋቋመችው ሰፈራ

እስራኤል በኃይል ይዛው በምትገኘው ዌስት ባንክ የወጠነችው ሰፈራ የመስፋፋት ዕቅድ "የፍልስጤምን የአገርነት ጥያቄ የሚቀብር ነው" በማለት የቀኝ አክራሪው የእስራኤል የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች መናገራቸውን ተከትሎ ከባድ ውግዘት ገጥሟቸዋል።

ይህ የአይሁዳውያንን ሰፈራዎች ማስፋፋት እስራኤል በኃይል በያዘችው ዌስት ባንክ ከሦስት ሺህ በላይ ቤቶችን ለመገንባት የወጠነ ነው።

ኢ1 የሚል ስያሜ የተሰጠው ፕሮጀክት ዌስት ባንክን ለሁለት በመክፈል ከሌላኛው እስራኤል በኃይል ከያዘችው ምሥራቅ ኢየሩሳሌም የሚያቆራርጥ ነው።

ስፍራው በምሥራቅ ኢየሩሳሌም እና በዌስት ባንክ እስራኤል በመሠረተችው ማሌ አዱሚም በተሰኘው ሰፈራ መካከል የሚገኝ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ለአስርት ዓመታት ተቋርጦ ነበር።

እስራኤል በኃይል በያዘቻቸው መሬቶች የምታካሂደው ሰፈራዎች በዓለም አቀፉ ሕግ መሠረት ሕገወጥ ናቸው ቢባሉም እስራኤል ግን ይህንን አትቀበለውም።

ረቡዕ ዕለት ቀኝ አክራሪው ሚኒስትር ስሞትሪች ይህንን የሰፈራ ዕቅድ መጽደቁን በመደገፍ "ታሪካዊ ስኬት" ሲሉ አሞካሽተውታል።

የፍልስጤም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ አዲሱ የሰፈራ ዕቅድ "የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ ማፈናቀል እና የመጠቅለል አካል ነው" ሲል አውግዞታል።

እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል አልፈጸምኩም ብትልም፤ የእስራኤል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን ጨምሮ እስራኤል በጋዛ ጦርነት እየፈጸመችው ያለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው ይላሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ቱርክ እና የአውሮፓ ኅብረት የተለያዩ አገራት ኢ-ዋን የተሰኘውን ይህንን የእስራኤል የሰፈራ ዕቅድ በመቃወም እንዲቆም ጠይቀዋል።

 የቀኝ አክራሪው የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የቀኝ አክራሪው እስራኤል የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች

የኢ-ዋን የሰፈራ ዕቅድ ምንድን ነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እስራኤል በኃይል በያዘቻቸው ግዛቶች ዜጎቿን ማስፈሯን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሕገወጥነት ይፈርጀዋል።

ኢ-ዋን የተሰኘው የሰፈራ ፕሮጀክት መጀመሪያ የቀረበው በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ በጠቅላይ ሚኒስትር ይስሐቅ ራቢን ነበር።

ይህም እስራኤል በኃይል በያዘችው መሬት ለዜጎቿ 2500 ቤቶችን ለመገንባት ወጥኖ የተጀመረ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2004 ዕቅዱ ተስፋፍቶ የንግድ እና የቱሪዝም ተቋማትን በማካተት 4 ሺህ ሕንጻዎችን በዚህ በኃይል በተያዘው መሬት ላይ ይገነባል ተባለ።

በቀጣይም በአውሮፓውያኑ 2009 እና 2020 አዳዲስ የሰፈራ ዕቅዶች ታወጁ።

ይህም ዕቅድ በፍልስጤማውያኑ የተያዙ መሬቶችን ወረራን ጨምሮ፣ አዳዲስ ዲዛይን እና የመንገድ ግንባታን ያካተተ ነው።

ሆኖም ዕቅዱ በዓለም አቀፉ ጫና ምክንያት እንዲቆም ሆነ።

ይህ በኃይል በተያዘው መሬት እስራኤላውያኑን ኢ-ዋን ተብለው በተለዩት አካባቢዎች የማስፈር ዕቅድ ፍልስጤማውያኑ አገር ለመመሥረት የሚያደርጉትን ትግል ዋነኛ ማደናቀፊያ ተደርጎ ይታያል።

ለዚህም ምክንያቱ ስፍራዎቹ ያላቸው ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ነው።

ዕቅዱ የኢየሩሳሌም የተለያዩ ክፍሎችን ከማቆራረጡ በተጨማሪ የፍልስጤማውያኑን ራማላህ፣ ምሥራቅ ኢየሩሳሌም እና ቤተልሄም ከተሞችን የሚለያይ ነው።

በአሁኑ ወቅት ሊደረጉ የታቀዱ ግንባታዎች 38 ሺህ እስራኤላውያን ሰፋሪዎችን የያዘውን ማሌ አዱሚም ሰፈራ 33 በመቶ እንደሚያሰፋው በዌስት ባንክ ሰፈራን የሚቃወመው የእስራኤሉ ተቋም 'ፒስ ናው' አሰታውቋል።

ይህ ፕሮጀክት እስራኤል በዌስት ባንክ ያላትን ይዞታ የሚያስፋፋ እንደሆነ ተቋሙ አክሏል።

የኢ-ዋን የሰፈራ ዕቅድ በሚቀጥለው ሳምንት ለቴክኒክ ኮሚቴ ቀርቦ የሚጸድቅ ሲሆን፤ ይህ ኮሚቴ ከዚህ ቀደም በዕቅዱ ላይ የቀረቡ ተቃውሞዎችን ውድቅ ማድረጉን ይኸው ተቋም ገልጿል።

የእስራኤል ሰፋሪዎች በዌስት ባንክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሰፈራ በኃይል በተያዘው ዌስት ባንክ

እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1967 በተደረገው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ነው የፍልስጤማውያኑ ግዛት የሆኑትን ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን የተቆጣጠረችው።

ዌስት ባንክ በእስራኤል እና በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል የምትገኝ ሲሆን፣ ሦስት ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን የሚኖሩበት አካባቢ ነው።

ዌስት ባንክ፣ እየሩሳሌም እና ጋዛ በአንድ ላይ በኃይል የተያዙ የፍልስጤም ግዛቶች ተብለው ይታወቃሉ።

እስራኤል በኃይል በያዘቻቸው ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌም ውስጥ ባቋቋመቻቸው 160 ሰፈራዎች 700 ሺህ ያህል እስራኤላውያን ሰፋሪዎች ይኖራሉ።

ፍልስጤማውያን፤ እስራኤል እነዚህን ግዛቶች በኃይል መያዟን በጽኑ የሚቃወሙት ነው።

እስራኤል አሁንም ቢሆን በአጠቃላይ ዌስት ባንክን በበላይነት የምትቆጣጠር ቢሆንም፣ ከአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ጀምሮ የፍልስጤም አስተዳደር በርካታ ከተሞችን ያስተዳድራል።

ሐማስ በ2016 ዓ.ም. መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በዌስት ባንክ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን ላይ የምታደርሰው ጫና በከፍተኛ መጠን ጨምሯል።

እስራኤል ይህንን የሰፈራ ማስፋፋት ከፀጥታ እርምጃዎች መካከል አንዱ ነው የሚል ምክንያት ትሰጣለች።

ሰኔ ወር ላይ 100 የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ሰፋሪዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው የተባበሩት መንግሥታት ዘግቧል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ የጋዛ ጦርነት ከተነሳ ጀምሮ በዌስት ባንክ ቢያንስ 975 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ፀጥታ ኃይሎች እና በሰፋሪዎች ተገድለዋል።

የእስራኤል ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያኑ ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ግዛቷን የሚቆጣጠረው የእስራኤል ፀጥታ ኃይሎች በዝምታ ያልፉታል ሲሉ ፍልስጤማውያን እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይተቻሉ።

ዝም ብሎ ከማለፍ በተጨማሪ እነዚህ የእስራኤል የፀጥታ ኃይሎች በጥቃቶቹ ተሳታፊ እንደሆኑ ባለፈው ዓመት የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪው ሂውማን ራይትስ ዋች ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።

እስራኤል በኃይል በያዘቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች ላይ ሰፈራን የሚከለክለው የጄኔቫ ኮንቬንሽን ተፈጻሚነት የለውም ትላለች፤ ይህ ዕይታ ግን አጋሮቿን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያዎች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም።

ፍልስጤማውያኑ በእስራኤል የተያዙባቸውን ግዛቶችን ጨምረው የወደፊቷን አገር የመመሥረት ዕቅድ ስላላቸው በእነዚህ ግዛቶች ውስጥ የሚደረጉ ሰፈራዎችን ይቃወማሉ።

የእስራኤል መንግሥት ፍልስጤማውያን የራሳቸውን አገር የመመሥረት መብት አላቸው የሚለውን አጥብቆ ይቃወማል።

በዚህም በኃይል የያዛቸውን ዌስት ባንክ የእስራኤል አካል ነው ሲል ይከራከራል።

የተባበሩት መንግሥታት፣ ዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት እስራኤል በኃይል የያዘቻቸውን የፍልስጤም ግዛቶች ተቆጣጥራ መቆየቷ ሕገወጥ ነው፤ እንዲሁም ሰፋሪዎቿን ማስወጣት አለባት የሚል ውሳኔ ላይ ባለፈው ዓመት ደርሷል።

ፍርድ ቤቱ በተጨማሪም እስራኤል በወረራ በተቆጣጠረቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች በፍልስጤማውያኑ ላይ የጣለቻቸው ገደቦች "በዘር፣ በሃይማኖት ወይም በጎሳ ላይ የተመሠረተ ስልታዊ መድልዎ" ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ "ሐሰተኛ" ሲሉ ተችተዋል።

"የአይሁድ ሕዝብ በገዛ ምድሩ ወራሪዎች አይደሉም፤ በዘላለማዊቷ ዋና ከተማችን በእየሩሳሌም፣ በወረስናት የይሁዳ እና ሰማርያ (ዌስት ባንክ) ምድር" ሲሉ ባወጡት መግለጫ አትተዋል።

በእስራኤል በተከታታይ የመጡ አስተዳደሮች ሰፈራዎች እንዲስፋፉ አድርገዋል።

ይሁን እንጂ ሰፈራን የሚደግፈው የቀኝ አክራሪ ጥምረት የሆነውን መንግሥት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድጋሚ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ሰፈራዎች እየተስፋፉ ይገኛሉ።

የጋዛ ጦርነትም እንዲሁ ለእነዚህ ሰፈራዎች መጨመር በር መክፈቱም ተነግሯል። ሰፈራዎች መስፈፋት ብቻ ሳይሆን ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያኑ ላይ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች መባባሱም ተገልጿል።

የእስራኤል የጸጥታ ኃይሎች ከሰፋሪዎች ጋር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ዓለም ለኢ-ዋን የሰፈራ ዕቅድ ምላሹ ምንድን ነው?

ሚኒስትሩ ዕቅዱን ይፋ ካደረጉ በኋላ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሃካቤ ላደረጉላቸው ድጋፍ አመስግነው፤ ዌስት ባንክ "ለእስራኤል በአምላክ ቃል የተገባላት የማይነጣጠል መሬት ነው" ብለዋል።

አንድ ሚሊዮን አዳዲስ ሰፋሪዎችን በዌስት ባንክ ለማስፈር ሚኒስትሩ ማቀዳቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድጋፍ እንዳለውም አክለው ገልጸዋል።

የፍልስጤም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ይህንን ፕሮጀክት አውግዞ፤ በፍልስጤም የግዛት አንድነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንዲሁም የፍልስጤም አገርነት ምሥረታን የሚጎዳ ነው ብሏል።

ዕቅዱ የፍልስጤምን የመልከዓ ምድር እና የሥነ ሕዝብ ትስስርን በማዳከም፤ ዌስት ባንክን ከፋፍሎ በቅኝ ግዛት ወደተከለሉ ስፍራዎች በማስገባት ለመጠቅለል የሚወሰድ እርምጃ ነው ብሏል።

ይህንን እርምጃ አስመልክቶ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "የተረጋጋ ዌስት ባንክ የእስራኤልን ደኅንነት ያስጠብቃል፤ ይህም በቀጣናው ሰላም ለማስፈን አስተዳደሩ ከወጠነው ግብ ጋር የሚጣጣም ነው" ብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአውሮፓ ኅብረት እስራኤል በዚህ ዕቅድ እንዳትቀጥል ጠይቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይህ ኢ-ዋን ሰፈራ ሰሜን እና ደቡብ ዌስት ባንክን በማቆራረጥ "የፍልስጤምን ግዛት በመከፋፈል አገር ለመመሥረት የሚደረገውን ተስፋ በእጅጉ የሚጎዳ ነው" ብሏል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ "ዩናይትድ ኪንግደም የእስራኤል መንግሥት የያዘውን ኢ-ዋን የተሰኘውን የሰፈራ ዕቅድ አጥብቆ ይቃወማል። ይህ የወደፊት የፍልስጤምን አገርነት ለሁለት የሚከፍል እና የዓለም አቀፍ ሕግን በግልጽ የሚጥስ ነው" ብለዋል።

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውሳኔውን "ዓለም አቀፍ ሕግን የሚቃረን" እንዲሁም "የፍልስጤም ግዛት አንድነት ላይ ያነጣጠረ" በማለት አውግዟል።

ግብፅም ይህንን እርምጃ ያወገዘች ሲሆን፣ የዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ "የፍልስጤም ሕዝብ ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን ዋና ከተማቸው አድርገው በአውሮፓውያኑ 1967 በተከለለከው ድንበር መሠረት ነጻ ሉዓላዊ አገር የመመሥረት የማይገረሰስ መብታቸው ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው" ሲል ተቃውሟል።

ይህ ዕቅድ የፍልስጤምን አገርነት ጥያቄ የሚያከሽፍ እንደሆነ የገለጹት የእስራኤሉ ሚኒስትር ስሞትሪች "ምንም እውቅና የሚሰጠው ወይም ማንም ዕውቅና የሚሰጠው አካል የለም" ብለዋል።

ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ፈረንሳይ እና ካናዳን ጨምሮ በርካታ አገራት ለፍልስጤም የአገርነት ዕውቅና ለመስጠት መወሰናቸውን ተከትሎ ነው።

በአሁኑ ወቅት ከ193 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት መካከል 140ዎቹ ፍልስጤምን በአገርነት ዕውቅና ሰጥተዋታል።

እስራኤል በአገርነት፣ በአውሮፓውያኑ 1948 ስትመሠረት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ያፈናቀለች ሲሆን፣ ይህንንም "ናቅባ" (ታልቁ እልቂት) ሲሉ ይጠሩታል።

በአሁኑ ወቅትም ፍልስጤማውያኑ ይኸው ይደገማል በሚል ፍራቻ ላይ ናቸው።

ከቀያቸው የተፈናቀሉት ፍልስጤማውያኑ አብዛኛዎቹ ጋዛ ውስጥ የሰፈሩ ሲሆን ከጋዛ ነዋሪዎች መካከል ሦስት አራተኛውን የሚይዙት በዚያን ወቅት የተፈናቀሉ የልጅ ልጆች ናቸው።

ሌሎች 900 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ አሁን እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ ውስጥ ይኖራሉ።

በተጨማሪም 3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በዮርዳኖስ፣ በሶሪያ እና በሊባኖስ እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።