እስራኤል "የፍልስጤምን የአገርነት ጥያቄ ለመቅበር" በኃይል በያዘችው ግዛት ሰፈራ መስፋፋትን አጸደቀች

የአገሪቱ የቀኝ አክራሪ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

እስራኤል በኃይል በያዘችው ዌስት ባንክ ከ3 ሺህ በላይ ቤቶችን ለመገንባት መወጠኗ ሰፈራን በማስፋፋት "የፍልስጤምን የአገርነት ጥያቄ የሚቀብር ነው" በማለት የአገሪቱ የቀኝ አክራሪ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች አወደሱ።

ኢ1 የሚል ስያሜ የተሰጠው ፕሮጀክት ዌስት ባንክን ለሁለት በመክፈል ከሌላኛው በኃይል ከያዘችው ምስራቅ ኢየሩሳሌም የሚያቆራርጥ ነው።

ስፍራው በምስራቅ ኢየሩሳሌም እና በዌስት ባንክ እስራኤል በመሰረተችው ማሌ አዱሚም በተሰኘው ሰፈራ መካከል የሚገኝ ሲሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ገጥሞት ለአስርት ዓመታት ቆሞ ነበር።

በዚህ ስፍራ ግንባታዎችን ማካሄድ ማለት ዌስት ባንክን ከሌላኛው በኃይል ከያዘችው ምስራቅ ኢየሩሳሌም የሚያቆራርጥ ነው።

ይህ ዕቅድ የፍልስጤምን አገርነት ጥያቄ የሚያከሽፍ እንደሆነ የገለጹት ስሞትሪች "ምንም እውቅና የሚሰጠው ወይም ማንም ዕውቅና የሚሰጠው አካል የለም ብለዋል።

ሰፈራዎች በአለም አቀፉ ህግ መሰረት ህገወጥ ናቸው።

እስራኤል በኃይል በያዘቻቸው ዌስት ባንክ እና ምስራቅ ኢየሩሳሌም ባቋቋመቻቸው 160 ሰፈራዎች 700 ሺህ ያህል እስራኤላውያን ሰፋሪዎች እንደሚኖሩ ሰፈራን የሚቃወመው 'እስራኤል አንታይ ሴትልመንት ግሩፕ ፒስ ናው' አስታውቋል።

"ከአስርት ዓመታት አለም አቀፍ ጫና እና መቆም በኋላ ስምምነቶችን በማፍረስ ማሌ አዱሚምን ከእየሩሳሌም ጋር ልናገናኘው ነው" ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ጽዮናዊነት ማለት ይህ ነው፤ መገንባት፣ ማስፈር እንዲሁም በእስራኤል ምድር ሉዓላዊነታችንን ማጠናከር" ብለዋል።

ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በርካታ አገራት ለፍልስጤም ዕውቅና ለመስጠት ማወጃቸውን ተከትሎ ነው።

ዕቅዱን ከሰፈራ ድርጅቶች የሻ ካውንስል ሊቀ መንበር እስራኤል ጋንዝ እና የማሌ አዱሚም ከንቲባ ጋይ ይርፋች ጋር በጋራ በመሆን ይፋ ያደረጉት ስሞትሪች "ይህ መሬት ለአይሁዳውያን ከአምላክ የተሰጠ ነው" ብለዋል።

በመጪው መስከረም ለፍልስጤም ዕውቅና ለመስጠት ላቀዱት ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይ መልዕክት ይኖራቸው እንደሆነ በቢቢሲ የተጠየቁት ሚኒስትሩ "ይህ አይፈጸምም፤ ዕውቅና የሚሰጡት አገር አይኖርም" ብለዋል።

ይህንን እርምጃ አስመልክቶ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "የተረጋጋች ዌስት ባንክ የእስራኤልን ደህንነት ያስጠብቃል እናም ይህምበቀጣናው ሰላም ለማስፈን አስተዳደሩ ከወጠነው ግብ ጋር የሚጣጣም ነው" ብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረት እስራኤል በዚህ ዕቅድ እንዳትቀጥል ጠይቀዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ "ዩናይትድ ኪንግደም የእስራኤል መንግሥት የያዘውን ኢ-ዋን የተሰኘውን የሰፈራ ዕቅድ አጥብቃ ትቃወማለች። ይህ የወደፊት የፍልስጤምን አገርነት ለሁለት የሚከፍል እና የዓለም አቀፍ ህግን በግልጽ የሚጥስ ነው" ብለዋል።

የፍልስጤም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ አዲሱ የሰፈራ ዕቅድ "የዘር ማጥፋት ወንጀል ፣ ማፈናቀል እና የመጠቅለል አካላ ነው" ሲል አውግዞታል።

እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል አልፈጸምኩም ብትልም የእስራኤል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን ጨምሮ እስራኤል በጋዛ ጦርነት እየፈጸመችው ያለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው ይላሉ።

እስራኤል በአገርነት፣ በአውሮፖውያኑ 1948 ስትመሠረት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ያፈናቀለች ሲሆን፣ ይህንንም "ናቅባ" (ታላቁ እልቂት) ሲሉ ይጠሩታል።

በአሁኑ ወቅትም ፍልስጤማውያኑ ይኸው ይደገማል በሚል ፍራቻ ላይ ናቸው።

ከቀያቸው የተፈናቀሉት ፍልስጤማውያኑ አብዛኞቹ በጋዛ ሰፍረዋል።

በአሁኑ ወቅት ካሉ የጋዛ ነዋሪዎች መካከል ሦስት አራተኛውን የሚይዙት በዚያን ወቅት የተፈናቀሉ የልጅ ልጆች ናቸው።

ሌሎች 900 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ አሁን እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ ይኖራሉ።

በተጨማሪም 3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በዮርዳኖስ፣ በሶሪያ እና በሊባኖስ እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።

እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1967 በተደረገው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ነው የፍልስጤማውያኑ ግዛት የሆኑትን ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን የተቆጣጠረችው።

ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ለ700 ሺህ አይሁዳውያን መኖሪያ የሚሆኑ 160 ሰፈራዎችን ገንብታለች። በዌስት ባንክ 3.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ይኖራሉ።

አብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እስራኤል እያደረገችው ያለውን ሰፈራ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገወጥ ነው ሲል ይኮንናል።

እስራኤል ይህንን አትቀበልም።

በእስራኤል በተከታታይ የመጡ አስተዳደሮች ሰፈራዎች እንዲስፋፉ አድርገዋል።

ይሁን እንጂ ሰፈራን የሚደግፈው የቅኝ ክንፍ አክራሪ ጥምረት የሆነውን መንግሥት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድጋሚ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ሰፈራዎች እየተስፋፉ ይገኛሉ።

የጋዛ ጦርነትም እንዲሁ ለእነዚህ ሰፈራዎች መጨመር በር መክፈቱም ተነግሯል። ሰፈራዎች መስፈፋት ብቻ ሳይሆን ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያኑ ላይ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች መባባሱም ተገልጿል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ የጋዛ ጦርነት ከተነሳ ጀምሮ በዌስት ባንክ ቢያንስ 975 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጸጥታ ኃይሎች እና በእስራኤል ሰፋሪዎች ተገድለዋል።