ኦስካር ባሸነፈው የዌስትባንክ ፊልም ተሳታፊ የሆነው ፍልስጤማዊ በእስራኤላዊ ሰፋሪ መገደሉ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, @Kivsa_shchora/Masafering
እስራኤል በወረራ በያዘችው ዌስትባንክ ላይ በወታደሮቿ የሚደርሱ መፈናቀሎችና ጥቃቶችን እንዲሁም የፍልስጤማውያኑን ትግል ላይ ያነጣጠረው 'ኖ አዘር ላንድ' የሚለው ፊልም ላይ ተሳታፊ የሆነው ፍልስጤማዊ በእስራኤላዊ ሰፋሪ መገደሉ ተነገረ።
የኦስካር ሽልማት አሸናፊ በሆነው የዌስት ባንኩ ፊልም ተሳታፊ የነበረው ፍልስጤማዊው መምህር ኦዴህ ሃታሊን በእስራኤላዊ ሰፋሪ በጥይት መገደሉን የፍልስጤም የትምህርት ሚኒስትር እንዲሁም ሲገደል ያየው እስራኤላዊ አሜሪካዊ ተሟጋች አስታውቀዋል።
የ'ኖ አዘር ላንድ' ፊልም አንደኛው ዳይሬክተር ዩቫል አብርሃም እንደተናገረው እስራኤል በወረራ በያዘቻት ዌስት ባንክ ኡም አል ኬይር መንደር አንድ እስራኤላዊ ሰፋሪ ኦዴህን በጥይት ደረቱ ላይ እንደመታው ገልጿል።
የአካባቢው ነዋሪዎችም ገዳዩ በፍልስጤማውያን ላይ በርካታ ጥሰቶችን በመፈጸም በዩናይትድ ኪንግደም ማዕቀብ የተጣለበት እስራኤላዊው ሰፋሪ ይኖን ሌቪ መሆኑን ተናግረዋል።
ግድያውን ፈጽሟል የተባለው እስራኤላዊ ሰፋሪ ጠበቃ አቪቻይ ሐጅቢ ደንበኛቸው "ህይወቱ አደጋ ላይ የወደቀ" ሌላ ነዋሪን ወክሎ እንደሄደ እና ሰፋሪዎቹ "በአረብ ቡድን እና በውጭ አገር ተሟጋቾች በድንጋይ እና ሌሎች ጥቃቶች ተሰንዝሮባቸው"መሳሪያውን ወደ አየር ለመተኮስ ተገዷል" ብለዋል።
በስፍራው የነበረ እስራኤላዊ አሜሪካዊ ተሟጋች ማታን በርነር ካዲሽ ሰኞ ዕለት በአቅራቢያው ከሚገኝ የእስራኤል ሰፈራ የመጣ የእስራኤል ቡልዶዘር በፍልስጤማዊ መሬት ላይ እየነዳ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦን፣ በርካታ የወይራ ዛፎች እና ሁለት አጥር መደረማመሱን ተናግሯል።
በርነር ካዲሽ እና ሌሎች ተሟጋቾች እና የኦዴህ የአጎት ልጅ አህመድ ጋር ሆነው በቡልዶዘሩ ላይ መንገድ ለመዝጋት መሮጣቸውን ገልጿል።
አሽከርካሪው ከቡልዶዘሩ መሰርሰሪያ አውጥቶ አህመድን አንገት እና ትከሻው ላይ ሲመታው መሬት ላይ ሲወድቅ በርነር የቀረጸው ቪዲዮ ያሳያል።
መሬት ላይ የወደቀውን አህመድን እየተንከባከበ የነበረው በርነር ድንገት ዷ የሚል ድምጽ መስማቱን ያስረዳል።
ውሃ ለማምጣት ወደ መንደሩ እየሮጠ ሲሄድ ኦዴህ በጥይት ተመትቶ ደሙ እየፈሰሰ እና እስራኤላዊ ሰፋሪ ሌቪ ጠመንጃ ይዞ መቆሙን ተመልክቷል።
በኦዴህ ዘመድ ተቀርጾ በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ በተለጠፈ ቪዲዮ ላይ ከቡልዶዘሩ ፊት ሌቪ ጠመንጃ ይዞ እና ሰዎች ሲጮሁበት ይታያል። ሌቪ አንድ ሰው ሲገፋ እና እሱም መልሶ ሲገፋው ያሳያል።ሌቪ ጠመንጃውን አንስቶ ወደፊት ለፊቱ ሲተኩስ ያሳያል።
ሴቶች ሲጮሁ ድምጽ መስማቱን ተከትሎ ቪዲዮውን የሚቀርጸው ግለሰብ ወደነሱ የሚሮጥ ሲሆን ከዚያ በኋላ የሆነውን አያሳይም።
የእስራኤል ፖሊስ ማክሰኞ ማለዳ አንድ የእስራኤል ዜጋ ለምርመራ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግሯል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው እስራኤላዊው ሰፋሪ ሌቪ በቤት ውስጥ እስር እንዲቆይ በሚል እንደተለቀቀ ዘግበዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት በክስተቱ እጃቸው አለበት በሚል አምስት ፍልስጤማውያንና ሁለት የውጭ አገር ጎብኝዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ያስታወቀ ሲሆን በርነር በበኩሉ አሁንም እንደታሰሩ ተናግሯል።
ኦዴህ የቅርብ ጓደኛው እንደሆነ የሚናገረው በርነር በመንደሪቷ የእግር ኳስ ሜዳ ለመገንባት ተቃርበው እንደነበር ገልጿል።
የሶስት ትናንሽ ልጆች አባት የሆነው ኦዴህን "አፍቃሪ አባት ሲል" ጓደኛው ገልጾታል።
የፍልስጤም የትምህርት ሚኒስቴር በአካባቢው በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር እንደነበር አስታውቋል።
እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1967 በተደረገው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ነው የፍልስጤማውያኑ ግዛት የሆኑትን ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን የተቆጣጠረችው።
ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ለ700 ሺህ አይሁዳውያን መኖሪያ የሚሆኑ 160 ሰፈራዎችን ገንብታለች። በዌስት ባንክ 3.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ይኖራሉ።
አብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እስራኤል እያደረገችው ያለውን ሰፈራ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገወጥ ነው ሲል ይኮንናል።
እስራኤል ይህንን አትቀበልም።
በእስራኤል በተከታታይ የመጡ አስተዳደሮች ሰፈራዎች እንዲስፋፉ አድርገዋል።
ይሁን እንጂ ሰፈራን የሚደግፈው የቅኝ ክንፍ አክራሪ ጥምረት የሆነውን መንግሥት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድጋሚ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ሰፈራዎች እየተስፋፉ ይገኛሉ።
የጋዛ ጦርነትም እንዲሁ ለእነዚህ ሰፈራዎች መጨመር በር መክፈቱም ተነግሯል። ሰፈራዎች መስፈፋት ብቻ ሳይሆን ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያኑ ላይ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች መባባሱም ተገልጿል።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ የጋዛ ጦርነት ከተነሳ ጀምሮ በዌስት ባንክ ቢያንስ 975 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጸጥታ ኃይሎች እና በእስራኤል ሰፋሪዎች ተገድለዋል።















