የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ዌስት ባንክን መጠቅለል 'ቀይ መስመርን' ማለፍ ነው ስትል እስራኤልን አስጠነቀቀች

በዌስት ባንክ በእስራኤል የሰፈራ ፕሮግራም የተሰሩ መኖሪያ መንደሮች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ እስራኤል በወረራ የያዘችውን ዌስት ባንክን ጠቅልሎ መመውሰድ "ቀይ መስመርን" ማለፍ ነው ስትል አስጠነቀቀች።

አክላም የሁለቱን አገራት ግንኙነት መደበኛ እንዲሆን ያደረገውን ''የአብርሀም ስምምነቶች'' መንፈስን እንደሚያደፈርሰው ገልጻለች።

የኤምሬትስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ላና ኑሴቤህ እንዲህ ያለው እርምጃ የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭትን ለመፍታት የሚያስችለው የሁለት አገራት መፍትሄ እንዲያበቃ ያደርጋል ብለዋል።

የፍልስጤም አስተዳደር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስን አቋም እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

የእስራኤል መንግሥት በጉዳዩ ላይ የሰጠው አስተያየት የለም።

የኑሴቤህ አስተያየት የተሰማው የቀኝ አክራሪው የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች አራት አምስተኛውን የዌስት ባንክን ግዛት ለመጠቅለል ሐሳብ ካቀረቡ በኋላ ነው።

እአአ ከ1967 የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ጀምሮ እስራኤል ዌስት ባንክን እና ምሥራቅ እየሩሳሌምን በወረራ በመያዝ ለ700,000 አይሁዶች መኖሪያ የሚሆኑ160 ሰፈሮችን ገንብታለች።

ፍልስጤማውያን ይህንን አካባቢ እና ጋዛን ወደፊት እንመሠርተዋለን ለሚሉት አገር ይፈልጉታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እስራኤል በወረራ በያዘቻቸው አካባቢዎች ከሰፈሩ አይሁዳውያን ጋር 3.3 ሚሊዮን የሚገመቱ ፍልስጤማውያን አብረው ይኖራሉ።

ሰፈራዎቹ በዓለም አቀፍ ሕግ 'ሕገ ወጥ' ናቸው።

እአአ በ2020 የየተፈረመው ''የአብርሃም ስምምነቶች'' የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ባህሬን እና ሞሮኮ ከእስራኤል ጋር ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲመሠርቱ አድርጓል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ስምምነቱን ለመፈረም ከቻለችባቸው ቁልፍ ምክንያቶች አንዱ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የቀድሞ መንግሥት ዌስት ባንክን የመጠቅለል ሐሳብ እንዲሁም በዮርዳኖስ ሸለቆ ጨምሮ የሚደረጉ ሰፈራዎችን ለማቆም በመስማማቱ ነበር።

ኔታንያሁ በወቅቱ እቅዶቹን "ለማቋረጥ" መስማማታቸውን ገልጸው የነበረ ቢሆንም ነገር ግን "ክፍት ሆነው" እንደሚቆዩ ተናግረዋል።

አሁን በሥልጣን ላይ ያሉ በርካታ የእስራኤል ሚኒስትሮች ዌስት ባንክን በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ለመጠቅለል ሲሟገቱ ቆይተዋል።

ነገር ግን በቅርቡ ዩኬ፣ፈረንሳይ እና ሌሎች በርካታ አገራት በዚህ ወር ለፍልስጤም ግዛት እውቅና ለመስጠት ማሰባቸውን ተከትሎ እንደዚህ ዓይነት እቅዶችን ወደፊት መግፋት ተገቢነት ላይ ሲከራከሩ መቆየታቸው ተዘግቧል።

ኔታንያሁ ሐማስ በእስራኤል ላይ በመስከረም 26፣ 2016 ዓ.ም. በጋዛ ጦርነት የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ እውቅና መስጠት "ለሽብርተኝነት ሽልማት" ከመስጠት ጋር ይስተካከላል ብለዋል።

ለፍልስጤም አገርነት እውቅና ከሰጡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 147 አባል አገራት መካከል አንዷ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ነች።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ኑሴቤህ "ከመጀመሪያው ጀምሮ፣ የ[አብርሀምን] ስምምነቶች የምንመለከተው ለፍልስጤም ሕዝቦች ባለን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እና ነፃ አገር የመመሥረት ሕጋዊ ፍላጎታቸውን ለማስቻል እንደ አንድ መንገድ ነበር" ብለዋል።

አክለውም "ዌስት ባንክን ጠቅልሎ መውሰድ ለተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ቀይ መስመርን ማለፍ ይሆናል።''

"የስምምነቱ ራዕይ እና መንፈስን ክፉኛ ይጎዳል፣ ቀጠናዊ ትብብርን ያስተጓጉላል እና ይህ ግጭት ተፈትቶ ሁለቱ አገራት በሰላም አብረው እንዲኖሩ የሚለው እና ሰፊ መግባባት የተደረሰበትን ሐሳብ ይለውጣል ።"

ከሰዓታት በፊት፣ሰፋሪ የሆኑት እና አክራሪ የአይሁድ ብሔርተኛው ስሞትሪች በእየሩሳሌም ለጋዜጠኞች ዌስት ባንክን ጠቅልሎ የመውሰድ "ጊዜው ደርሷል" ሲሉ ተናግረዋል።

"አገርን የመከፋፈልና አሸባሪ መንግሥት በማዕከሉ የመመሥረት ሐሳብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከጠረጴዛው መጥፋት አለበት" ሲሉም አክለዋል።

ከመከላከያ ሚኒስቴር የሰፈራ ቢሮ እንደመጣ በመናገር ባሳዩት ካርታ ላይ "የእስራኤልን ሉዓላዊነት መተግበር" በሚል ወደ 82 በመቶ የሚጠጋው የግዛቱን ክፍል አገራቸው እንድትጠቀልል ምክረ ሐሳብ ያቀርባል።

ይህም "ሰፊ መሬት- ጥቂት አረቦች" ከሚለው መርህ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ተናግረዋል።

የቀረው 18 በመቶ የግዛቱ ክፍል በስድስት የፍልስጤም ከተሞች ዙሪያ ጄኒን፣ቱልካርም፣ናብሉስ፣ራማላ፣ኢያሪኮ እና ሄብሮን ያሉ ገለልተኛ ግዛቶችን ያቀፈ ነበር።

ቤተልሔም ከሌሎቹ የፍልስጤም ከተሞች እና መንደሮች ውስጥ ካልተካተቱት መካከል ስትሆን ምሥራቅ እየሩሳሌም ምንም እንኳ በበርካታ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተቀባይነት ባያገኝም እአአ በ1980 በእስራኤል ስር ተጠቃላለች።

ስሞትሪች ፍልስጤማውያን "በአሁኑ ጊዜ በፍልስጤም አስተዳደር በኩል እንደሚያደርጉት፣ በኋላም በቀጠናው የሲቪል አስተዳደር አማራጮች በኩል የራሳቸውን ሕይወት ማስተዳደርን ይቀጥላሉ" ብለዋል።

የዌስት ባንክን አካባቢዎች የሚያስተዳድረው የፍልስጤም አስተዳደር የስሞትሪች ዕቅድ የፍልስጤም አገርነት ተስፋ "ቀጥተኛ ስጋት" ነው ብሏል።

የእስራኤል ወረራ እንዲቆም የሚሟገተው የኦፌክ ሴንተር ባልደረባ የሆኑት የሁዳ ሻውል የስሞትሪች ካርታ "በ20ኛው ክፍለ ዘመን ሌላ አህጉር ውስጥ ያለ ሌላ ካርታ አስታውሰኝ፣በአፍሪካንስ ቋንቋ ያንን አገዛዝ የሚገልጽ አገላለጽ አለ" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

በርካታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እስራኤል በዌስት ባንክ የአፓርታይድ ሥርዓት ትከተላለች ያሉ ሲሆን እስራኤል ግን ይህንን ውድቅ ታደርጋለች።

ፍልስጤማውያን እስራኤል በወረራ በኃይል የተቆጣጠረቻቸውን የዌስት ባንክ እና የምሥራቅ ኢየሩሳሌም ግዛቶችን ያካተተች አገርን ለመመሥረት እየታገሉ ነው።

በአሁኑ ወቅት ያለው የእስራኤል መንግሥት የፍልስጤምን አገርነት እንዲሁም ሉዓላዊነት ይቃወማል።

እስራኤል በኃይል በያዘችው ዌስት ባንክ ከ3 ሺህ በላይ ቤቶችን ለመገንባት እና ሰፈራን ለማስፋፋት ''ኢ1'' የሚል መጠሪያ የሰጠችውን ፕሮጀክት አጽድቃለች።

''ኢ1'' የሚል ስያሜ የተሰጠው ፕሮጀክት ዌስት ባንክን ለሁለት በመክፈል ከሌላኛው በኃይል ከያዘችው ምሥራቅ ኢየሩሳሌም የሚያቆራርጥ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአውሮፓ ኅብረት እስራኤል በዚህ ዕቅድ እንዳትቀጥል ጠይቀዋል።

እአአ በ 2024 ዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት እስራኤል "በያዘችው የፍልስጤም ግዛት የሚኖራት ቀጣይነት ያለው ቆይታ ሕገ ወጥ ነው" እና አገሪቱ "በተቻለ ፍጥነት . . . ሕገ ወጥ ቆይታዋን የማቆም ግዴታ አለባት" በማለት አስተያየት ሰጥቷል።

ኔታንያሁ በወቅቱ ፍርድ ቤቱ የውሸት ውሳኔ ወስኗል ሲሉ ተናግረው ነበር።