የአውሮፓ አገራት ለፍልስጤም የሰጡት የአገርነት እውቅና ያለ አሜሪካ ድጋፍ ተጨባጭ ይሆናል?

የፎቶው ባለመብት, EPA
ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ ለፍልስጤም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ላይ የአገርነት እውቅና መስጠታቸው አንድ ክፍለ ዘመን ለተጠጋው የእስራኤልና የፍልስጤም ግጭት ታሪካዊ ክስተት ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ታላላቅ የአውሮፓ ኃያላን አገራት ግጭቱ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ እርምጃ እንዲወስዱ የሚያስገድድበት ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያሳዩበት ዲፕሎማሲያዊ ቁማር ነው።
አሁን ላይ በጋዛ ያለውን አስከፊ ቀውስ የተጋፈጡት እና እስራኤል እና ሐማስን ያወገዙት የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን " ከኃይል ይልቅ መብት መከበር አለበት" ብለዋል።
ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር በመተባበር እንዲሁም በሳዑዲ ድጋፍ የወሰዱት እርምጃም 'የሁለት አገራት'ን መፍትሄ ለመተግበር ያለመ ነው።
አገራቱ፣ ይህ ለረጅም ጊዜ የቆየ ዓለም አቀፍ የሰላም ቀመር [ የሁለት አገራት መፍትሔ] ሁለቱ ሕዝቦች ወደፊት ለሚጋሩት ፍትሃዊ የሆነ ሕይወት ብቸኛው መንገድ እንደሆነ ያምናሉ።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም ከዚህ ውጭ ያለው አማራጭ "የአንድ አገር መፍትሔ" እንደሆነና ይህ ግን የእስራኤልን የበላይነት የሚያረጋግጥ እና ፍልስጤማውያን እንዲገዙ የሚያደርግ መሆኑን በኒዮርክ በተካሄደው የተመድ ጉባኤ ላይ ተናግረዋል።
"ፍልስጤማውያን በጅምላ የሚደርስባቸውን ቅጣት ፣ ረሃብ ወይም የዘር ማጥፋት በምክንያትነት የሚቀርብ ምንም ነገር የለም" ብለዋል ዋና ጸሐፊው።
እስራኤል በዚህ የተበሳጨች ሲሆን ምላሽ እንደምትሰጥ እየዛተች ነው።
ዩኬ፣ ፈረንሳይ፣ ካናዳ እና አውስትራሊያ እንዲሁም ሌሎች አገራት ለፍልስጤም እውቅና መስጠታቸውን ጨምሮ የተመድን ስብሰባ የተመለከተችውም አገሪቷ ላይ ጥቃት የመፈፀመውን እና በርካቶችን አግቶ የወሰደውን ሐማስ እንደመሸለም ነው።
አንዳንድ የእስራኤል ሚኒስትሮችም ለዚህ ምላሹ መሆን ያለበት የፍልስጤም ግዛት እስከወዲያኛው እንዳይኖር ማድረግ እና በእስራኤል ሥር የምትገኘው ዌስት ባንክ ከእስራኤል ጋር መጠቅለሏን ማወጅ እንዲሆን ይፈልጋሉ።
ፍልስጤማውያንን በማፈናቀል አይሁዶች እንዲሰፍሩ ፖሊሲ የቀረጹ ቀኝ አክራሪ ባለሥልጣናትን ጨምሮ የጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ የአስተዳደር ጥምረት የሁለት አገር መፍትሔን አይቀበልም።
የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደርም የአውሮፓውያኑን እርምጃ ውድቅ ያደረገ ሲሆን የፍልስጤምን ባለሥልጣን ፕሬዚደንት መሐመድ አባስን በመቅጣት አጋሩን እስራኤል መደገፉን ቀጥሏል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የተመድ ጉባኤ የተመራው በሳዑዲ አረቢያ ሲሆን በአረብ ሊግ ተደግፏል።
ፈረንሳውያኑ እንደሚሉትም በጉባኤው ላይ ቁልፍ የሆኑ የአረብ ሊግ አገራት ሃማስ ትጥቅ እንዲፈታ እና መሣሪያውን እንዲያስረክብ በመጠየቃቸው ይህ ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ ሃማስን በተመለከተም ሊጠቅም ይችላል። በዚህም ምክንያት ሐማስ ወደፊት ለፍልስጤማውያን የመሪነት ሚና ሊኖረው እንደማይችልም ያስረዳሉ።
ማክሮንም ይህ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለእስራኤልም እንደሚጠቅም እና ትራምፕ እና ኔታንያሁ ለረጅም ጊዜ ሲፈልጉት ለነበረው ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ለሚኖራት መደበኛ ግንኙነት በር ይከፍታል ብለው ያምናሉ።
ሆኖም ፈረንሳይ የዋሽንግተንን ፍላጎት በሚቃረን መልኩ ለፍልስጤም የአገርነት እውቅና መስጠቷ ወሳኝ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ፍትጊያን ይፈጥራል።
የትራምፕ አስተዳደር ፕሬዚደንት መሐመድ አባስ በኒው ዮርኩ ጉባኤ ላይ በአካል እንዳይገኙ በመከልከል በምትኩ በቪዲዮ ሃሳባቸውን እንዲናገሩ አድርጓል።
ፍልስጤምን የተመለከተው ስብሰባ እና የትራምፕ አስተዳደር የወሰደው እርምጃም በዋሽንግተን እና በአውሮፓ አጋሮቿ መካከል የመካከለኛው ምሥራቅን ግጭት መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሰፊ ክፍተት ፈጥሯል።
ሆኖም አውሮፓውያኑ መሬት ላይ ካለው ሁኔታ አንጻር ጥቂት ምርጫ ብቻ እንዳላቸው ነው የሚያምኑት።
እስራኤል አሁን ላይ በርካታ ፍልስጤማውያን በየቀኑ በሚገደሉበት ጋዛ ከተማ ተጨማሪ ጦሯን አሰማርታለች። ሃማስም ወደ 50 የሚጠጉ ታጋቾችን እንደያዘ ሲሆን አብዛኞቹ ሞተዋል።
በዌስት ባንክም እስራኤል ሰፈራን እያስፋፋች ሲሆን የሰፋሪዎች ጥቃት ቀውስ ተባብሷል።
ይህ ሁሉ ከአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7 ጀምሮ ለሁለት ዓመት በሚጠጋ ጊዜ የሆነ ሲሆን እስራኤል የምታካሂደው ወታዳራዊ ጥቃት ሃማስ እጅ እንዲሰጥ ሊያስገድድ እንደሚችል የሚያሳዩ ምልክቶች ጥቂት ናቸው።
በመሆኑም ማክሮን ያደረጉት ዲፕሎማሲ ወሳኝ አማራጭ ሊሆን እንደሚችል የሚያሳይ ሙከራ ነው።
መጀመሪያ በጋዛ ያለውን ጦርነት የሚያስቆም አማራጭ መፈለግ ከዚያም በመቀጠል እስራኤል እና ፍልስጤምን "የሁለት አገር" የረዥም ጊዜ መፍትሔ መፈለግ።
የአውሮፓ አገራት የእስራኤል ስልት የሰላማዊ ሰዎችን ስቃይ ከማብዛት እና በእገታ ውስጥ ያሉትን እስራኤላውያን አደጋ ላይ ከመጣል በስተቀር ያመጣው ውጤት የለም ሲሉም ይከራከራሉ።

የፎቶው ባለመብት, EPA
በተመድ አዳራሽ መድረክ ላይ ማክሮንን ማየት ፕሬዚደንቱ በጋዛ ያለው "አስፈሪ ቅዠት" እንዲያበቃ ዓለም አቀፍ የመሪነት ሚናቸውን ለመወጣት እየሞከሩ እንደሆነ ያሳያል።
ነገር ግን ይህ ድርጊታቸው በኃይል አሰላለፍ መልኩ ከታየ ማክሮን ስህተት ናቸው።
ምክንያቱም በሁሉም ወገኖች ጫና መፍጠር የምትችለው ዋሽንግተን በመሆኗ ጥረቱን አሜሪካ ካልመራችው ትርጉም ያለው ውጤት አያመጣም።
የትራምፕ አስተዳደር ደግሞ አውሮፓውያኑን እየተከተሉት ያለውን መንገድ አልተቀበለውም።
በቁልፍ አገራት መካከል ቅንጅት አለመኖር የፍልስጤምን የአገርነት እውቅና እና ለጦርነቱ ፍፃሜ የማበጀቱ ነገር አይሳካም የሚለውን ስሜት ጨምሮታል።
ከዚህ ቀደም እስራኤል እና ሃማስን ስታሸማግል የነበረችው ኳታር፣ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ እስራኤል በገዛ መሬቷ ውስጥ የሃማስ መሪዎች ላይ ጥቃት ከፈፀመች በኋላ በሁለቱ ወገኖች መካከል ጣልቃ አልገባም ብላለች።
ማክሮን እና ስታርመርም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ያመጡት የአገራቸውን የቅኝ ግዛት አሻራ ነው።
በዚህ እርምጃቸው እንደ አውሮፓውያኑ 1948 ብሪታኒያ ከታሪካዊቷ ፍልስጤም ከወጣች በኋላ የዓለም ማኅበረሰብ ለእስራኤል እውቅና የሰጠበትን ሁኔታ አስታውሰዋል።
አሁን ላይ ግን ፍልስጤማውያን በአገራቸው እኩል መብት እንዳላቸው ተረድተዋል።
ፍልስጤማውያንም ከአውሮፓ አገራት የተሰጣቸውን እውቅና የተቀበሉት ሲሆን እውቅናውን የሰጧቸው አገራት የቀደሙት ልዕለ ኃያላን እንደነበሩ ያውቃሉ።
የፍልስጤም የአገርነት እውቅና ተጨባጭ የሚሆነው ግን ዛሬ ልዕለ ኃያል በሆነችው አሜሪካ ከተደገፈ ብቻ ነው።
ፕሬዚደንት ትራምፕ ደግሞ በዚህ ላይ እስካሁን ድረስ ያላቸው ሃሳብ ሌላ ነው።















