ኔታንያሁ ዌስት ባንክን ከእስራኤል ጋር እንዲቀላቀሉ 'አልፈቅድም'- ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቤንያሚን ኔታንያሁ በእስራኤል ወረራ ስር ያለው ዌስት ባንክን ወደ ግዛታቸው እንዲቀላቀሉ አልፈቅድም አሉ።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አርብ ዕለት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ከማድረጋቸው ቀደም ብለው በኦቫል ኦፊስ ለጋዜጠኞች ሃሳባቸው የሰጡት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት፤ "እስራኤል ዌስት ባንክን እንድትቀላቀል አልፈቅድም…አይሆንም" ብለዋል።
ሰኞ ከኔታንያሁ ጋር የሚገናኙት ትራምፕ የጋዛ ስምምነት "በጣም ተቃርቧል" ሲሉ ገልጸዋል።
እስራኤል በጋዛ ያለውን ጦርነት እና የዌስት ባንክን ወረራ እንድታቆም ዓለም አቀፍ ጫና እየደረሰባት ነው። የምዕራባውያን መንግሥታት ለፍልስጤም ነጻ አገርነት በይፋ ዕውቅና እየሰጡ ነው።
ቀኝ ዘመም እስራኤላውያን አካባቢውን መጠቅለል ይህንን ግፊት ለማስቆም አማራጭ መንገድ እንደሆነ ይመለከቱታል።
በኔታንያሁ የአስተዳደር ጥምረት ውስጥ ያሉ አክራሪ እስራኤላዊያን የፍልስጤም ግዛት አካል የሆነው ዌስት ባንክን እንዲቀላቀል ተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም እና ጀርመን እስራኤል አካባቢውን ከግዛቷ ጋር እንዳትቀላቅል አስጠንቅቀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሰኞ ዕለት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደተናገሩት ይህ "ሞራላዊ፣ ሕጋዊ እና ፖለቲካዊ ትዕግስት የሌለው ነው" ብለዋል።
ትራምፕ ሐሙስ ዕለት በኦቫል ኦፊስ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ከኔታንያሁ እና ከሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ መሪዎች ጋር ተነጋግረዋል።
ትራምፕ "በጋዛ ላይ ስምምነት ለማድረግ፤ ምናልባትም ሠላም ለመፍጠር ጭምር በጣም እየተቃረብን ነው" ብለዋል።
የፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ባለፈው ሐሙስ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ በቪዲዮ ባደረጉት ንግግር በፈረንሳይ ይፋ የተደረገውን የእስራኤል እና የፍልስጤምን የሠላም ዕቅድን ተግባራዊ ለማድረግ ከዓለም መሪዎች ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የ89 ዓመቱ አባስ በአካል ወደ ኒውዮርክ ተጉዘው ንግግር እንዳያደርጉ በአሜሪካ ተከልክለዋል።
ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ እንግሊዝ፣ ፖርቱጋል፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጂየም፣ ሉክሰምበርግ፣ ማልታ፣ ሞናኮ፣ ሳን ማሪኖ፣ አንዶራ እና ዴንማርክ ለፍልስጤም መንግሥት ዕውቅና በመስጠታቸው አመስግነዋል።
አሜሪካ ለፍልስጤም ዕውቅና ለመስጠት ጊዜው አሁን አይደለም በማለት ተቃውማለች። ይህ እርምጃ ለሐማስ ሽልማት ነው ስትል አክላለች።
አባስ በንግግራቸው "ሐማስ በአስተዳደሩ ውስጥ ሚና አይኖረውም" ብለዋል። የእስራኤልን መውጣት ተከትሎ የፍልስጤም መንግሥት ለጋዛ ሰርጥ ሙሉ ኃላፊነት እንዲወስድ እና በእስራኤል ከተያዘው ዌስት ባንክ ጋር እንዲያገናኝም ጠይቀዋል።
ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት ቁልፍ ከሆኑ የአረብ እና የሙስሊም አገራት መሪዎች ጋር በተገናኙበት ወቅት እስራኤል አከባቢውን መቀላቀል ከጀመረች መዘዙ አለው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፋርሃን ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት በዌስት ባንክ ውስጥ ያለውን የመቀላቀል አደጋ እና ስጋት በሚገባ የተረዱ ይመስለኛል።"
እስራኤል ረቡዕ ጠዋት ዌስት ባንክ እና በአጎራባች ዮርዳኖስ መካከል ያለውን ብቸኛ መሻገሪያ ዘግታለች። በዚህም ከሁለት ሚሊዮን በላይ ፍልስጤማውያን ከውጭው ዓለም ጋር እንዳይገናኙ አድርጋለች።
መሻገሪያው የተዘጋው ሁለት የእስራኤል ወታደሮች በአካባቢው በዮርዳኖሳዊ ታጣቂ በጥይት ከተገደሉ ከቀናት በኋላ ነው። ግለሰቡም በስፍራው ተገድሏል።
ረቡዕ ዕለት ጋዛ ውስጥ ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ ከ80 የሚበልጡ ፍልስጤማውያን በእስራኤል መገደላቸውን የአካባቢው ሆስፒታሎች ተናግረዋል።
መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በሐማስ መሪነት በደቡብ እስራኤል ላይ በደረሰው ጥቃት አንድ ሺህ 200 ሰዎች ሲገደሉ 251 ሌሎች ታግተዋል። ይህንን ተከትሎ የእስራኤል ጦር ምላሽ ለመስጠት በጋዛ ዘመቻ ከፍቷል።
ከዚያን ጊዜ ወዲህ እስራኤል በጋዛ ባደረሰችው ጥቃት ከ18 ሺህ በላይ ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 65,419 ሰዎች ተገድለዋል ሲል በሐማስ የሚመራው የግዛቲቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል።
በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው የተቀናጀ የምግብ ዋስትና ደረጃ ምደባ (አይፒሲ) በነሐሴ ወር እንዳስታወቀው፤ በመላው ጋዛ ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች "ለረሃብ፣ ለችጋር እና ለሞት" የሚያጋልጡ "አሰቃቂ" ሁኔታዎች እያጋጠማቸው መሆኑን ገልጿል። ኔታንያሁ በጋዛ ረሃብ እየተከሰተ መባሉን ደጋግመው አስተባብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጣሪ ኮሚሽን እስራኤል በጋዛ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች ቢልም የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "የተዛባ እና ሀሰት" በማለት ውድቅ አድርጎታል።
እስራኤል ጦርነቱን እና ወረራውን እንድታቆም ከፍተኛ ግፊት እየተደረገባት ነው።















