600 ዓመታትን ያስቆጠረው የሣር ድልድይ

የፎቶው ባለመብት, Jordi Busque
በፔሩ አፐሪማክ ግዛት አንድን ትልቅ ወንዝ ለመሻገር በሣር የተሠራን ድልድይ መሻገር ግድ ይላል። የሣር ድልድዩ ለአንድ ዓመት የሚያገለግል ሲሆን በየዓመቱ በአዲስ ገመድ ይተካና አሮጌው በታች ይደረደራል።
የ'ኬስዋቻካ' ድልድይ በእጅ በተፈተለ የሣር ገመድ የሚሠራና በየዓመቱ እየተተካ ከ600 ዓመታት በላይ የኖረ ነው።
ከኢንካ ሥልጣኔ መገለጫ ከሆኑት ከተሞች መካከል ከአንዷ ጋር የሚያገናኝ እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ድልድይ በ2013 በዪኔስኮ በቅርስነት ተመዝግቧል።

የፎቶው ባለመብት, JORDI BUSQUE
ድልድይ የመገንባት ባህሉ ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ ወጣቶች አሮጌውን ገመድ በአዲስ እየተኩ በየዓመቱ ለድልድዩ አዲስ መንፈስና ጥንካሬ ያላብሱታል።
ድልድዩን የሚሠሩት ወንዶች ብቻ እንዲሆኑ የነዋሪዎቹ ባህል ያስገድዳል። ሴቶች ገመዶችን እየፈተሉ ከወንዙ አፋፍ ላይ ከሚገኝ ሸለቋማ ስፍራ እንዲቀመጡ ይደረጋል።
በመጀመሪያው መልሶ የመገንባት ቀን ወንዶች ተሰባስበው ትልልቅ ገመዶችን ወጥረው በትንንሾቹ ያጠላልፋሉ። አጠቃላይ የድልድዩ ስፋት የሰው እግር ውፍረት ያክል ባላቸው ስድስት ገመዶች ላይ ያርፋል። ስድስቶቹ ወፋፍራም ገመዶች እያንዳንዳቸው ከ120 ቀጫጭን የሣር ግማዶችን ይሠራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Jordi Busque
እያንዳንዱ ቤተሰብ ባለሁለት ፈትል፣ ከጠንካራ ሣር የተገመደ በአካባቢው አጠራር 'ኮያ ኢቹ' የሚባል ገመድ ማበርከት ይኖርበታል። ድልድይን በሚያዘጋጁበት ወቅት ገመዱ የመተጣጠፍ ባህርይ እንዲኖረው ሣሩ ወደገመድነት ከመፈተሉ በፊት በድንጋይ ይቀጠቀጥና ውሃ ውስጥ ይዘፈዘፋል።
በድልድይ ሥራው ወቅት ከፊሉ ሰው፣ የድልድይ ሥራውን የሚያሳልጡ ሠራተኞች እንዳይራቡ ከወንዙ የሚጠመዱ ዓሣዎችን፣ አሳማና ዶሮዎችን በድንች ከሽኖ ለምግብነት ያሰናዳል።
አዲሱ ድልድይ እንደተጠናቀቀም አሮጌው ይቆረጥና ወንዙ ላይ እንዲንሳፈፍ ይደረጋል።
ከስድስቱ ትልልቅ ገመዶች አራቱ መረማመጃ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ ለእጅ መደገፊያና ሚዛን መጠበቂያ ሆነው በጎን በኩል በአጥር መልኩ ቋሚ ሆነው ይሠራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Jordi Busque
ስድስቱንም ገመዶች ሚዛናቸውን በጠበቀ መልኩ ተወጥረው ከወንዙ ጫፍና ጫፍ በትልልቅ ድንጋይ እንዳይበጠሱ ተደረጎ ይታሰራሉ። በዚህም ማንም ያለፍርሃት ወንዙን በገመድ ድልድዩ አማካኝነት ይሻገራል።
ድልድዩን ለመሥራት ምንም ዓይነት ዘመናዊ መሣሪያ አያስፈልግም፤ አይጠቀሙምም። የሚያስፈልገው ሁለተ ነገር ብቻ ነው። ሰውና ሣር።
በየዓመቱ ሰኔ በገባ በሁለተኛው እሁድ የሚደረገው የ'ኬስዋቻካ' ድልድይ ግንባታ አራት ቀናትን የሚወስድ ሲሆን በመጠናቀቂያው ዕለት የሙዚቃና የምግብ ድግስ ማሰናዳት የፍፃሜው ማብሰሪያና ማድመቂያ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Jordi Busque












