ውክልናን በቪድዮ፡ የውክልና ሂደትን በ20 ደቂቃ

ኬብሮን ደጀኔ ከአምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን ጋር

የፎቶው ባለመብት, KEBRON DEJENE

የምስሉ መግለጫ, ኬብሮን ደጀኔ ከአምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን ጋር

ኬብሮን ነዋሪነቱ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት ሲሆን ኢትዮጵያ ለሚገኙ ወዳጅ ዘመዶቹ ውክልና ለመስጠት አስቦ ሂደቱን በአሜሪካን ሃገር ቢጀምርም ነገሮች እንዳሰባቸው ቀላል ሆነው አላገኛቸውም። በዚህ ምክንያት የተነሳም የውክልና አሰጣጥ ሥርዓቱን ለመቀየር ቆርጬ ተነሳሁ ይላል፤ ኬብሮን ።

እንዳለውም አደረገው። የውክልና ሥርዓቱን በማዘመን የሚወስደውን ጊዜ ከወራት ወደ ደቂቃዎች ለማሳጠር ችሏል። እንዴት?

ኬብሮን ደጀኔ 'ሲሊከን ቫሊ' በመባል የሚታወቀው የአሜሪካ ቴክኖሎጂ እምብርት ውስጥ 'ቪዲቸር' የሚባል ድርጅት ካቋቋመ አምስት ዓመት ሊሆነው ነው። አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የውልና ማስረጃን አሠራር ለማፋጠን ትልቅ ሚና ለመጫወት በቅቷል።

በዛሬው ዕለት በ'ቪዲቸር' የተደገፈው የውክልና አሠራር በዋሺንግተን ዲሲ ባለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተመርቋል። ለሕዝብ አገልግሎትም ሥራ ላይ እንዲውል ይፋ ተደርጓል።

የተጓተተ የውክልና ሂደት

ከሁለት ዓመት በፊት ነበር ከውክልና አሠራር ጋር ኬብሮን ግብ ግብ የገጠመው። በኢትዮጵያ ያለን የንግድ ተቋም ዘመድ እንዲያንቀሳቅስለት በማሰብ የውክልና ሂደቱን ቢጀምርም በካሊፎርኒያና በአካባቢው ውክልና የሚጽፍለትም ሆነ የሚያረጋግጥለት ማግኘት ሳይችል ቀረ። ከስድሰት ሰዓታት የአየር ጉዞ በኋላ በዋሽንግተን ዲሲ ሂደቱን አስጀመረ። ውክልና የመስጠት ተግባሩ ግን ቀላል አልነበረም።

11 የተለያዩ ነገሮችን ማሟላት ይጠይቅ እንደነበር እንዲሁም በሕግ ባለሙያ አረጋግጦ ቢያንስ 40 ቀናት መጠበቅ ግድ እንሆነ ይናገራል። ከስንት ወጣ ውረድ በኋላ ኢትዮጵያ የደረሰው የውክልና ወረቀት ስህተት አለበት በመባሉ በድጋሚ ለማሠራት መገደዱንም ኬብሮን ይናገራል።

እንደዚህ ዓይነት ችግሮች መኖራቸውን ከዚህ ቀደም ከብዙ ሰዎች ይሰማ የነበረ ቢሆንም በእርሱ ላይ ከደረሰበት በኋላ አሠራሩን ለመቀየር ቆርጦ እንደተነሳ ይናገራል። በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እና 'ቪዲቸር' መካከል በተደረሰው ስምምነት መሰረት የውልና ማስረጃን አሠራር ለመቀየርና 'ዲጂታላይዝ' ወይም 'አውቶሜት' ለማድረግም 'ቪዲቸር' ለተሰኘው የኬብሮን ተቋም ፈቃድ ተሰጠ።

ለመሆኑ 'ቪዲቸር' ምንድን ነው?

'ቪዲቸር' ማለት የእንግሊዘኛውን 'ቪድዮ' እና 'ሲግኒቸር' (ፊርማ) ቃላት በማጣመር የመጣ ቃል ሲሆን ስሙ እንደሚገልፀውም እራስን ቪድዮ በማንሳት መፈረም ማለት ነው።

"በብዕር ጫር ጫር የሚደረገው ፊርማ" የሰውን ደህንነት ይጠብቃል ብዬ አላምንም የሚለው ኬብሮን፤ አንድ ሰው ውክልና ለሚሰጠው ሰው በሰነዱ መስማማቱን እየገለፀ እራሱን በቪድዮ ይቀርፃል። ቪድዮውም በሰነዱ ይካተታል ስለዚህም ለማረጋገጥ ቀላል ይሆናል ሲል ያስረዳል።

"ጥሩነቱ ማንኛውም ባለ ጉዳይ ካለበት ሆኖ መተግበሪያውን በስልክ በመጫን ቪድዮውን ቀርፆ መላክ መቻሉ ነው። ለጊዜው ግን በአሜሪካ ላሉ ኢትዮጵያውያን ብቻ ነው የጀመርነው" በማለት ሂደቱን ያብራራል።

የቪዲቸርና የኢትዮጵያ መንግሥት ሰምምነት

የፎቶው ባለመብት, KEBRON DEJENE

"በመጀመሪያ ንግግሬን ከአምባሳደር ግርማ ብሩ ጋር ነበር የጀመርኩት ከዚያ በኋላ ከአምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን ጋር ወደ ስምምነት አደረስነው። አምባሳደር ካሳም የቴክኖሎጂውን ሃሳብ ወደ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በመላክ ወደ ውሳኔ አደረሰው በማለት ወደ ሥራ እንዴት እንደገባ ያስረዳል።

ከውጪ ሃገር ወደ ኢትዮጵያ የሚላክ የውክልና ሂደት ምን ይመስል ነበር?

1) ወካይ በአቅራቢያው ባለ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በማምራት የውክልና ሰነዱን ያጽፋል

2) ኤምባሲው ውክልናውን ተረክቦ ከገመገመ በኋላ ፊርማና ማህተም አስፍሮ ለአመልካች ያስረክባል

3) አመልካች ሰነዱን ከኤምባሲ ተረክቦ ወደ ፈጣን የፖስታ አገልግሎት ወይም ወደ ፖስታ ቤት በመሄድ ሰነዱን ለተወካይ ይልካል

4) ተወካይ ከፖስታ ቤት የውክልናውን ሰነድ ይረከባል

5) ተወካይ ሰነዱ በቆንሱላ ጽሕፈት እንዲረጋገጥ ለውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ይወስዳል

6) በቆንሱላ ጽሕፈት ቤት ከተረጋገጠ በኋላ ወደ ውልና ማስረጃ በመውስድ በሰነዶች ማረጋገጫ እንዲረጋገጥ ያደርጋል

ይህ ሁሉ ሂደት በትንሹ ከ20 እስከ 40 የሥራ ቀናት ሊፈጅ ይችል እንደነበርና በ'ቪዲቸር' ግን ሙሉ ሂደቱ ወደ 20 ደቂቃ እንዲያጥር መቻሉ ተነግሯል።

እስራኤል ዮሐንስ በቆንሱል ጽሕፈት ቤት ቢሮ ካሉት 2 ሠራተኞች መካከል አንደኛው ሲሆን "መተግበሪያው ለተጠቃሚም ሆነ ለእኛ በጣም ቀላልና ፈጣን ነው" በማለት የማረጋገጫውን ሂደት እንደሚያቃልል ይናገራል። በኢትዮጵያ የቪዲቸር አማካሪ የሆነችው ጺዮን ትርሲት አክሊሉ ከውጪ የሚመጡ ብዙ የውክልና ሰነዶች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚላኩና ሂደቱን ለማፋጠን መሞከሩ ለሁሉም ጠቃሚ መሆኑን ትናገራለች።

የቆንሱላ ጽሕፈት ቤት 'ቪዲቸር' መሥራያ ቤት

የፎቶው ባለመብት, KEBRON DEJENE

የምስሉ መግለጫ, የቆንሱላ ጽሕፈት ቤት 'ቪዲቸር' መሥራያ ቤት

ውክልናን ከ40 ቀን ወደ 20 ደቂቃ

"አንድ የቅርብ ጓደኛዬ በጋምቤላ የኮንስትራክሽን ሥራ ጀምሮ ነበር። ሥራውን ለማስፈፀም ውክልና መስጠት ፈልጎ ሂደቱን ካገባደደ በኋላ ለሚመለከተው አካል ቢያስረክብም የሰነዱን እውነተኛነት ማመን ባለመቻላቸው ለሦስት ሳምንታት ወደ መቶ ሠራተኛ ደምወዝ እየከፈለ መጠበቅ ግድ ሆኖበት ነበር። ይህ ልክ አይደለም። ብዙ ነገር ያስተጓጉላል። እኛም ይህን የማረጋገጫ ሂደት ቢበዛ ቢበዛ ወደ 20 ደቂቃ መቀነስ ነው የምንፈልገው" ይላል ኬብሮን።

"እያንዳንዱ የውክልና ቪድዮ ለተፈለገው ሰነድ ብቻ የሚሠራ ነው" የሚለው ኬብሮን ይህ አሠራር ወንጀለኞችን ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው ይላል። "ማንም ሰው የውሸት ፊርማ በሰነድ ላይ አስፍሮ ለማጭበርበር ሊሞክር ይችላል። ግን በቪድዮ መልክ እየታየ ማንም ለማጭበርበር አይደፍርም" ይላል።