ጭምብል አለማድረግ "የማኅበረሰብ ጠንቅ" መሆን ነው ተባለ

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ሁሉም ሰው ከቤቱ ሲወጣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድግ እንዳለበት የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት መከሩ።
የሮያል ሶሳይቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት ሰር ቬንኪ ራማክሪሽናን (ፕሮፌሰር) ጭንብል ማድረግ የሚያደርገውን ሰውና በዙሪያው ያሉትን ሰዎች ከበሽታው እንደሚከላከል ማስረጃዎች አሉ ብለዋል።
የጭንብል አጠቃቀምን በተመለከተ በመንግሥት የሳይንስ አማካሪዎች ዘንድ የተቀላቀሉ አስተያየቶች በተለያዩ ጊዜያት ሲሰነዘሩ ቆይተዋል።
አንዳንዶች በአንዳንድ የእስያ አገራት ውስጥ የጉንፋን መስፋፋትን ለመከላከል ጥቅም ላይ ቢውሉም ብዙም ያሳዩት ለውጥ የለም። ስለዚህም ጭምብል በመጠቀም ተገቢ ያልሆነ የደኅንነት ስሜት ሊፈጠር ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ነገር ግን ሁሉንም የሚያስማማው እውነታ ጭንብሎች ቫይረሱ ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው የመታላለፍ እድሉን እንዲቀንስ ሊያደርገው ይችላል።
ፕሮፌሰር ራማክሪሽናን የሮያል ሶሳይቲ በጭምብል ላይ ባቀረባቸው ሁለት ሪፖርቶች ዙሪያ እንደተናገሩት "የተላለፉት መልዕክቶች ግልጽና ወጥ ስላልነበሩ" ሕብረተሰቡ ውስጥ "ጥርጣሬ" ተፈጥሯል።
በሚያዝያ ወር ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ጭምብል ያደርጉ የነበሩ ሰዎች 25 በመቶ ያህል ሲሆኑ በተመሳሳይ ወቅት ጣሊያን ውስጥ 83.4 በመቶ፣ በአሜሪካ 65.8 በመቶ እና በስፔን ደግሞ 63.8 በመቶ ሰዎች ጭምብል ይጠቀሙ ነበር።
ከቤት ውጪ የአፍን የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አለመጠቀም ጠጥቶ እንደማሽከርከርና የመቀመጫ ቀበቶን እንዳለመጠቀም ሁሉ "ለኅብረተሰብ ጠንቅ" ድርጊት ተደርጎ መወሰድ አለበት ብለዋል ፕሮፌሰሩ።
"ጭምብል አለማድረግ በእድሜ የገፉ ወላጆችንና የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ሁሉንም ሰው ለበሽታው ያጋልጣል" ብለዋል።
የጭንብሎችን ሌሎች መሸፈኛዎች በሽታውን በመከላከል በኩል ስላላቸው ውጤታማነት በተመለከተ ፍተሻ ያደረገ ጽሁፍ ያቀረቡት የፔንሲልቫኒያ ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር ፖል ኤደል ስታይን፤ ሌሎችን በበሽታው ከማስያዝ እንደሚከላከል "እንደሁል ጊዜው ግልጽ " መሆኑን ጠቅሰው በተጨማሪም ተጠቃሚውንም ከበሽታው እንደሚከላከል " አንዳንድ መረጃዎች" አሉ ብለዋል።
የበሽታው ምልክት የማይታይባቸው በርካታ ሰዎች የዕለት ከዕለት ሥራቸውን ለማከናወን በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ሳያውቁ ቫይረሱን የያዙ ጥቃቅን ፋሳሾችን ከትንፋሻቸው ጋር ስለሚያስወጡ በዙሪያቸው የሚገኙ ሰዎችን ለበሽታው ሊያጋልጡ ይችላሉ ይላሉ ፕሮፌሰር ፖል።
"እነዚህ ሰዎች አፍና አፍንጫቸውን ከሸፈኑ ጥቃቅኖቹ ጠብታዎች ወደ ሌሎች ሰዎች እንዳይሸጋገሩ ማድረግ ይችላሉ። ለዚህም ጭምብል ማድረግ ወረርሽኙን እንዳይተላለፍ በማድረግ የሰዎችን ህይወት መታደግ ይቻላል" ብለዋል።














