ኮሮናቫይረስ፡ አሜሪካ የጀርመንን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ‘በመውሰድ’ ተከሰሰች

የጀርመን ወታደር ጭምብሎቹን የያዘውን እሽግ ሲከፍት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካ ለጀርመን የተዘጋጀ 200 ሺህ የፊት ጭምብል (ማስክ) ወደ ራሷ በማዞር ተከሰሰች፤ ድርጊቱ "ዘመናዊ ወንበዴነት" በሚልም ተወግዟል።

በአሜሪካ የተሰሩት የፊት ጭምብሎች በታይላንድ ባንኮግ መያዛቸውን የበርሊን መንግሥት አስታውቋል።

ኤፍኤፍፒ2 የተሰኙት ጭምብሎች የተዘጋጁት በበርሊን የፖሊስ ኃይል ትዕዛዝ የነበረ ቢሆንም በእጃቸው ሳይገባ ቀርቷል።

የጀርመን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪያስ ጌሴል፤ ጭምብሎቹ ወደ አሜሪካ ሳይመለሱ እንዳልቀሩ ተናግረዋል።

ጭምበሎቹን ያመረተው የአሜሪካው ኩባንያ በበኩሉ፤ በፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በተጣለው ሕግ 3 ሚሊየን የሚሆኑት ጭምበሎቹ ወደ ሌሎች አገራት እንዳይላኩ ተከልክለዋል ብሏል።

ፕሬዚደንቱ የአሜሪካ ድርጅቶች በአገሪቷ ውስጥ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት በርካታ የህክምና ቁሳቁሶች ማምረት እንዳለባቸው ትናንት ተናግረዋል።

"እነዚህን ቁሳቁሶች በአስቸኳይ ለአገር ውስጥ ፍጆታ እንፈልጋቸዋልን፤ ሊኖሩን ይገባል" ሲሉ በዋይት ሐውስ በየቀኑ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ለተቋቋመው ግብረ ኃይል በሚሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

ፕሬዚደንቱ አክለውም የአሜሪካ መንግሥት 200 ሺህ የሚሆኑ ኤን95 ጭምብሎች፣ 130 ሺህ የቀዶ ህክምና ጭምብሎች እንዲሁም 600 ሺህ ጓንቶች መያዙን ተናግረዋል።

ይሁን እንጅ እነዚህ የህክምና ቁሳቁሶች ከየት እንደገቡ ያሉት ነገር የለም።

የጀርመን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስተሩ ጌሴል በበኩላቸው የጀርመን የሆነውን የፊት ጭምብል ወደ አሜሪካ አስቀይሶ መውሰድ "ወንበዴነት ነው" ሲሉ የትራምፕ አስተዳደር ዓለም አቀፉን የንግድ ሕግ እንዲያከብር አሳስበዋል።

ኮሮና
Banner