በአቃቂ ቃሊቲ በለይቶ ማቆያ ያሉ የጤና ባለሙያዎች መሠረታዊ ፍላጎታችን እየተሟላ አይደለም አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሳምንታት በፊት በኮቪድ-19 የተያዙ የህክምና ባለሙያዎች ቁጥር መጨመሩን የኢትዮጵያ ጤና ሚንስር ዶ/ር ሊያ ታደሰ መናገራቸው ይታወሳል። በተጨማሪም ቢቢሲ ያነጋገራቸው በተለያዩ የሕክምና ተቋማት የሚሰሩ ባለሙያዎችም የሕክምና መከላከያ ቁሳቁሶች (ፒፒኢ) እጥረት እንዳለባቸው ገልፀዋል።
ከእነዚህም መካከል ቫይረሱ ተገኝቶባቸው በለይቶ ማቆያ የሚገኙት በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ተብሎ በሚጠራው ጤና ጣቢያ ውስጥ ያሉት ይገኙበታል።
ወረዳ 10 ጤና ጣቢያ ተብሎ በሚጠራው ለይቶ ማቆያ ውስጥ እንደሚገኙ ለቢቢሲ የተናገሩ ሁለት የጤና ባለሙያዎች፤ በሚገኙበት ለይቶ ማቆያ መሠረታዊ የሚባሉ ግልጋሎቶችን በአፋጣኝ ማግኘት አልቻሉም።
ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት ስናነጋግራቸው በጣቢያው ውሃ እና መብራት እንዳልነበረ ገልጸውልናል። ሰኞ፣ ሰኔ 9 ቀን 2012 በድጋሚ ስናናግራቸው ግን ለሳምንት ያክል ያልነበረው የመብራት እና ውሃ እገልግሎት እንደመጣ ተናግረው ሌሎች ጥያቄዎቻቸው አሁንም ምላሽ እንዳላገኙ ግን ጨምረው አስረድተዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ የማይፈልጉ አንድ የጤና ባለሙያ እንደሚሉት፤ በሽታው በማኅበረሰቡ ውስጥ እየተሰራጨ ሲመጣ፣ ወደ ህክምና መስጫ ማዕከላት የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር ሲጨምር፤ የጤና ባለሙያዎችም ለበሽታው የበለጠ ተጋላጭ ይሆናሉ።
“ቀድሞውም ለጤና ባለሙያዎች በቂ የመከላከያ ቁሳቁስ [ፒፒኢ] መቅረብ ነበረበት። ይህ ግን አልሆነም። ማስክ በየጊዜው አይገኝም ነበር። ለሁለትና ለሦስት ቀን አንድ ማስክ [ይሰጣል] ጋዋን አይገኝም። የአገሪቱ የአቅርቦት ችግር ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ ግን [ሊታሰብልን ይገባል]” ይላሉ ባለሙያዋ።
በሽታውን በግንባር ቀደምነት ለሚዋጉ የጤና ባለሙያዎች በቂ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም ይናገራሉ። የጤና ባለሙያዎች በበሽታው ሲያዙ ደግሞ በለይቶ ማቆያ ውስጥ መሠረታዊ ፍላጎት መሟላት እንዳለበትም ያክላሉ።
ወደ 15 የሚሆኑ ወንድ እና ሴት የጤና ባለሙያዎች በአንድ መጸዳጃ እየተጠቀሙ እንደነበረ የጤና ባለሙያዋ ተናግረዋል።
አሁን በጣቢያው ውሃ ቢያገኙም ወደ ለይቶ ማቆያ ከአስር ቀን በፊት ሲገቡ ንጹህ መጸዳጃ እንዳልነበረ ይገልጻሉ።
“በአንድ ወለል ላይ ከነበሩ ሁለት መጸዳጃ ቤቶች አንዱ ሙሉ በሙሉ ውሃ አልነበረውም። አንዱ ግን ውሃ ስለነበረው በአንድ ወለል ላይ ያሉ 15 ወንዶችና ሴቶችም አንድ መጸዳጃ ቤት ይጠቀማሉ። ይሄ ለሴቶች አስቸጋሪ ነው። የወር አበባቸው ሲመጣ ሸንት ቤት በደንብ መጠቀም አለባቸው. . .”
ባለሙያዋ እንደሚሉት፤ ያለው ችግር እንዲቀረፍ ለማህበራቸውና ለጤና ሚንስትር በስልክ አሳውቀዋል። “ 'እየሄድንበት ነው' የሚል መልስ ነው የተሰጠን፤ የት እንደደረሰ አናውቅም” ሲሉም ያገኙትን ምላሽ ገልጸዋል።
የጤና ባለሙያዋ አያይዘውም “ሕዝብ እያገለገልን ሳለን መንግሥት ለኛ ዋጋ አለመስጠቱ አሳዝኖኛል። ይህ ነው ብድራችን?” በማለት መሠረታዊ ፍላጎቶች እንዲሟሉላቸው ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል በሌሎች ለይቶ ማቆያዎች ውስጥ ያሉ የጤና ባለሙያዎች መሠረታዊ ፍላጎታቸው ተሟልቶ እንደቆዩ መስማታቸውን የጤና ባለሙያዋ ተናግረዋል።
“በጥሩ ሁኔታ ቆይተው እንደወጡ ሰምቻለሁ። ምንም ቅሬታ የለም። እነሱ የነበሩበት ድሮም አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ተቋም ወስጥ ነው። የኛ ግን አዲስ ጤና ጣቢያ ነው። መሠረተ ልማቱ መሟላቱ ሳይታይ ነው ለይቶ ማቆያ የሆነው። ናሙና ሰጥተን ውጤት የሚመጣውም ዘግይቶ ነው። ሌሎቹ ጋር እንዲህ አይደለም” ይላሉ።
ሌላው ባለፈው ሳምንት (ሰኔ 4 ቀን 2012 ዓ. ም.) ያነጋገርናቸው የጤና ባለሙያ በለይቶ ማቆያ ከገቡ አስረኛ ቀናቸው እንደሆነ ገልጸውልናል። ነርሶችና ዶክተሮች በለይቶ ማቆያው እንደሚገኙ የሚናገሩት ባለሙያው፤ “ምርመራ እንዲደረግልን ስንጠይቅ ፍቃደኛ አይደሉም” ብለዋል።
“በቫይረሱ ተይዞ ወደ ለይቶ ማቆያ የሚገባ ሰው በሰባተኛው ቀን በድጋሚ መመርመር አለበት የሚል መርህ አለ። ይህ መርህ እየተሟላ አይደለም። እስከ 14 ቀን የቆዩ አሉ” ይላሉ።
ለክፍለ ከተማ እንዲሁም ለከተማው ጤና ቢሮ አሳውቀው “ጠብቁን” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ገልጸው፤ “በሽታው የሚያስጠብቅ አይደለም። አገግሞ ለመሄድ የሚመች ሁኔታ አይደለም” ብለዋል።
“የአገሪቱ ኢኮኖሚ ይታወቃል ቢሆንም ግን የጤና ባለሙያዎች እየተጋለጡ ያሉት በቂ ፒፒኢ ስለሌለ ነው። አንዳንዴ ሳኒታይዘር [እጅ ማጽጃ] በራስህ ወጪ ትገዛለህ. . . የታማሚን ስቃይ ለመቀነስ ስትሯሯጥ አንዳንዴ ራስህን የማታስታውስበት ደረጃ ላይ ትደርሳለህ” ሲሉ ከመጀመሪያውም በቂ ለቅድመ ጥንቃቄ የሚሆን የህክምና ቁሳ ቁስ አለመሟላቱን ያስረዳሉ።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ደካማ የጤና መዋቅር ያላቸውን ይቅርና በምጣኔ ሀብት የተሻለ ደረጃ ደርሰዋል የሚባሉትን እንደ አሜሪካ፣ ስፔን እና ጣልያን ያሉ አገራትንም ፈትኗል።
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል፣ ጓንት እና ገዋንን የመሰሉ የሀኪሞች የግል መገልገያዎች (ፒፒኢ) እጥረት ጉዳይም የመላው ዓለም ራስ ምታት ነው።
ሆኖም ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገሮች ያሉ የጤና ባለሙያዎች በሽታውን በግንባር ቀደምነት እንደመከላከላቸው፤ በበሽታው እንዳይያዙ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግላቸው ይጠይቃሉ። በከፍተኛ ሁኔታ ለቫይረሱ ተጋላጭ እንደመሆናቸውም በበሽታው ሲያዙ መሠረታዊ ፍላጎቶች እንዲሟሉላቸውም ያሳስባሉ።
ያነጋገርናቸው የጤና ባለጤና ባለሙያ፤ ከበሽታው አገግመው ወደ ሥራ ሲመለሱ፤ በለይቶ ማቆያ የነበሩበት ሁኔታ በሥራቸው ላይ ጫና ያሳድራል ብለው እንደሚሰጉ ገልጸውልናል።
“ከዚህ የበለጠ ጊዜ ስለሌለ በትክክለኛ መንገድ ቁሳ ቁሶች [ፒፒኢ] መቅረብ አለባቸው። ሥራችን ስለሆነ የትም አንሄድም። የተማርኩት በሙያዬ ኅብረተሰቡን ለማገልገል ነው። መንግሥትም መሟላት ያለበትን ማሟላት አለበት።”
በጉዳዩ ላይ ከጤና ሚንስትር ምላሽ ለማግኘት ሞክረን ወደ አዲስ አበባ ጤና ቢሮ መርተውናል። ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ እንዲሁም ከሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

















