ኮሮናቫይረስ፡ በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችና በተለያዩ መስኮች ላይ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች ለኮሮናቫይረስ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል።
ይህንን በተመለከተም ባለፈው ሐምሌ ወር ላይ የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው በዓለም ዙሪያ በኮቪድ-19 ከተያዙት ሰዎች መካከል 10 በመቶዎቹ የጤና ሠራተኞች ሲሆኑ በአፍሪካም ከ10 ሺህ በላይ የህክምና ባለሙያዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ወረርሽኙ መኖሩ ከታወቀ ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ሠራተኞች ላይ ቫይረሱ እንደተገኘ ተነግሯል።
ይህንን በተመለከተ ቢቢሲ በአገሪቱ ውስጥ አንዳንድ አካባቢዎች ያሉ የጤና ባለሙያዎች ስላሉበት ሁኔታ ለማወቅ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በሲዳማ ክልሎችና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የዳሰሳ ቅኝት አድርጓል። በዚህም በሁሉም ክልሎች የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች ለኮቪድ-19 ያላቸው ተጋላጭነት አሳሳቢ መሆኑን ተገንዝቧል።
በተጨማሪም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች ዘንድ እየተስፋፋ መሆኑን ያነጋገርናቸው ክልሎች የጤና ቢሮ ኃላፊዎች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
የጤና ቢሮ ኃላፊዎቹ ለቢቢሲ እንዳሉት ባለሙያዎቹ በተለያየ ምክንያት ለቫይረሱ የተጋለጡ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ከጥንቃቄ ጉድለት፣ ለመከላከያነት የሚያገለግሉ የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦት እጥረት መኖር እና በሌሎች ስፍራዎች በሚኖር የቫይረሱ ተጋላጭነት ምክንያት መያዛቸውን ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል እስካሁን ድረስ ከ30 በላይ በኮቪድ-19 የተያዙ የህክምና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች መኖራቸውን የክልሉ የኮሮናቫይረስ ሎጀስቲክስ አስተባባሪ አቶ ጣዕመ አረዶ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ባለሙያዎቹ ከሥራ ቦታ ውጪ በነበራቸው ተጋላጭነት፣ ከቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር በነበራቸው ንክኪ፣ በጤና ተቋማት ውስጥ የኮሮናቫይረስ መከላከያ በቂ አቅርቦት ባለመኖሩ ምክንያት መያዛቸውን ጨምረው ተናግረዋል።
በማይጨው ለምለም ካርል ሆስፒታል ለይቶ ማቆያ የሚሰሩት ዶ/ር ሳምሶን ነጋሲ የቫይረሱ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
"በአላማጣ በላብራቶሪ ቴክኒሺያንነት የሚሰሩ ሰባት ባለሙያዎች በቫይረሱ ተይዘዋል" ያሉት ዶ/ር ሳምሶን፣ በአይደር ሆስፒታል ሦስት ከፍተኛ የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ በርካታ የህክምና ባለሙያዎች በኮቪድ-19 ተይዘዋል ሲሉ ይናገራሉ።
በዚህም የተነሳ ሆስፒታሉ ከድንገተኛ፣ ማዋለጃ እና አንዳንድ ህክምናዎች ውጪ ሌላው ክፍል ህክምና እየሰጠ አለመሆኑን ገልፀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዶ/ር ሳምሶን በህክምና ማዕከላቱ የሕክምና እቃዎች አቅርቦት ችግር መኖሩንም ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። ለክልሉም ሆነ ለፌደራል አካላት ያለባቸውን ችግር ቢያቀርቡም እስካሁን መፍትሄ አለማግኘታቸውን ጨምረው አስረድተዋል።
በአማራ ክልል በአሁኑ ሰዓት በስፋት በኮሮናቫይረስ ከተያዙት የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል የህክምና ባለሙያዎች እንደሚገኙበት የገለፁት ደግሞ የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና ኢመርጀንሲ ማኔጅመንት ተወካይ ዳይሬክተር አቶ አሌ አያል ናቸው።
ጨምረውም ለወረርሽኙ ተጋላጭ ናቸው የሚባሉት የህክምና ባለሙያዎች በክልሉ በተለየ ሁኔታ ተጠቅተዋል ባይባልም፤ አሁን ግን ቁጥሩ እየጨመረ በመምጣት 23 ባለሙያዎች በቫይረሱ መያዛቸውን መረጋገጡን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በድሬዳዋ አስተዳደር 21 የሕክምና ባለሙያዎችና በጤና ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች በኮቪድ-19 መያዛቸውን የከተማዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ለቢቢሲ ማረጋገጡ ይታወሳል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪ ስንታየሁ ደበሳ እንደተናገሩት በሕክምና ዘርፍ ላይ ያሉ ባለሙያዎች በቫይረሱ መያዛቸው እተደረገ ያለውን ወረርሽኙን የመከላከል ሥራን ያዳክመዋል የሚል ስጋት አለ ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪዋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የጤና ባለሙያዎቹና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞቹ ለኮሮናቫይረስ የተጋለጡት በሥራ ቦታቸው ላይ እያሉ ነው።
"የጤና ባለሙያዎቻችን በቫይረሱ እየተያዙ መምጣት ወረርሽኙን ለመከላከል የምናደርገውን ጥረት ያዳክማል" ሲሉም በአስተዳደሩ በኩል ያለውን ስጋት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪዋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የጤና ባለሙያዎቹና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞቹ ለኮሮናቫይረስ የተጋለጡት በሥራ ቦታቸው ላይ እያሉ ነው።
በሽታውን ለመከላከል አስፈጊ የሆኑ አቅርቦቶችን አስተዳደሩ በበቂ ሁኔታ ማቅቡንና ገልጸው "እስካሁን ድረስ እጥረት የለብንም" ብለዋል።
ነገር ግን በሕክምና ተቋማቱ የሚኖሩ ንክኪዎች ባለሙያዎቹን ለቫይረሱ ማጋለጡን የሚናገሩት አስተባባሪዋ፤ ከባለሙያዎቹ ጋር በተደረገ ውይይት ለቫይረሱ የተጋለጡት በየትኛው ጊዜ እንደሆነ ለማለየት እንደሚቸገሩ ገልፀዋል።
በህክምና ተቋማቱ ያሉ ሁኔታዎች እንደሚያሳዩት ግን ይላሉ ባለሙያዋ "በሕክምና ሥራ ላይ እያሉ ተጋላጭ መሆናቸውን ነው" በማለት ባለሙያዎቹ እየወሰዱ ያሉትን የጥንቃቄ እርምጃዎችን መፈተሽ እንደሚያስፈልግም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን በሁሉም የክልሉ ዞኖችና ከተሞች ቫይረሱ መከሰቱን የክልሉ ጤና ቢሮ ገልጿል።
በክልሉ እስካሁን ድረስ 1827 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል 34 የሚሆኑት የጤና ባለሙያዎች መሆናቸውን የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኃላፊ አቶ ደረጃ አብደና ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የጤና ባለሙያዎች በብዛት የተገኙት መደበኛ ህክምና በሚሰጡ ሆስፒታሎችና ጤና ጣብያዎች ውስጥ መሆናቸውን አቶ ደረጀ ጨምረው ተናግረዋል።
የሲዳማ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ማቴ መንገሻ በበኩላቸውእስከ ዛሬ ድረስ በሲዳማ ክልል 13 የሕክምና ባለሙያዎች እና ሁለት ድጋፍ ሰጭ ሠራተኞች በኮቪድ-19 መያዛቸውን ተናግረዋል።
በኮቪድ-19 ከተያዙት የህክምና ባለሙያዎች መካከል ወደተለያየ ስፍራ ሄደው ራሳቸውን ለቫይረሱ ያጋለጡ፣ በሚሰሩባቸው ተቋማት አካባቢ ባለ የጥንቃቄ ጉድለት እንዲሁም የህክምና ቁሳቁስ እጥረት በመኖሩ የተነሳ የተጋለጡ እንደሚገኙበት አብራርተዋል።
















