ኮሮናቫይረስ፡ የትኞቹ የአፍሪካ አገራት በኮሮናቫይረስ ምርመራ ይመራሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኮሮናቫይረስ ምን ያህል ተዛምቷል አልተዛመተም የሚለውን በትክክል ለመረዳት በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች መመርመር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
በአፍሪካ ያለውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምላሽ በማስተባበር ላይ የሚገኘው የአፍሪካ የበሽታዎች ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል በአህጉሪቷ ያለው የምርመራ ሁኔታ በተለያዩ ሃገራት ዘንድ ልዩነት ያለው መሆኑን ጠቅሶ ፤ ክፍተትንም እንደሚያሳይ ከሰሞኑ አሳውቋል።
በአህጉሪቷ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እየመረመሩ ያሉ ሃገራት የትኞቹ ናቸው ወደኋላስ የቀሩት?
በአህጉሪቷ ውስጥ ያሉ ትንንሽ አገራት ከትልልቆቹ ጎረቤቶቻቸው ጋር በሚወዳደሩበት ወቅት በርካታ ሰዎችን በመመርመር ተሳክቶላቸዋል።
ለምሳሌ ያህል ሞሪሺየሽና ጂቡቲ የመረመሩት ከህዝባቸው ቁጥር ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ደረጃ የሚባል ነው።
ጋናም በበኩሏ ባከናወነቻቸው ምርመራዎች ምስጋናን እየተቸራች ሲሆን፤ መንግሥቷም አስገዳጅ መመሪያዎቹ ሲነሱ ቫይረሱን ለመቆጣጠር እንደሚረዳ ተናግረዋል።
ደቡብ አፍሪካም ቢሆን በከፍተኛ ሁኔታ ምርመራዎችን እያከናወነች ሲሆን እስካሁንም ባለው ከሁለት መቶ ሺ በላይ የላብራቶሪ ምርመራዎችን አድርጋለች። ነገር ግን ይህ አሃዝ እንደ ደቡብ ኮሪያ፣ ጣልያንና ጀርመን ካሉ ሃገራት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው።
በተለይም በአህጉሪቷ በህዝብ ቁጥሯ በአንደኝነት በምትመራው ናይጄሪያ የምርመራ ቁጥር አናሳ ነው ተብሎ ቢተችም መንግሥቷ ግን ቫይረሱ ከተገኘባቸው ግለሰቦች ጋር ንክኪ ወይም ግንኙነት ያላቸው ላይ ነው ትኩረቴ ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በናይጄሪያ የቢቢሲ ዘጋቢ ቺቺ ኢዙንዱ እንደሚናገረው ባለስልጣናቱ የምርመራ ቁጥርን የማሳደግ እቅድ አላቸው ብሏል።
"መንግሥት ያለመው በቀን 5ሺ ሰዎችን መመርመር ቢሆንም አንድ ሺህ ሰዎችን እንኳን እየመረመሩ አይደለም" በማለትም ያለውን ክፍተት ያስረዳል።
በአንዳንድ ሃገራት እንደ ኤርትራና አልጄሪያ ባሉት ደግሞ ምን ያህል ምርመራ እንደተካሄደ መረጃ የለም።
አንዳንዶች በተለያዩ ምክንያቶች የምርመራ ቁጥራቸውን መረጃ መስጠት ቢደብቁም አንዳንድ ሃገራት ደግሞ ለመርመር አቅሙ የላቸውም።
ለምሳሌ የታንዛንያው ፕሬዚዳንት ማጉፉሊ እንዲህ አይነት የምርመራ መረጃዎችን ይፋ ማድረግ በሕዝቡ ዘንድ ፍራቻን ይፈጥራል ብለዋል። ሃገራቸው የተመረጡ መረጃዎችን ሲሆን ለህዝብ ይፋ የምታደርገው አንዳንድ ጊዜም ከቫይረሱ ያገገሙት ላይ ማተኮርን መርጣለች።
የምርመራን አቅም ለማሳደግ ያሉ እክሎች ምንድንናቸው?
የምርመራ ሂደቶችን ለማከናወን የሚያስፈልጉ ኬሚካሎችን በበቂ ሁኔታ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም በርካታ የአፍሪካ ሃገራት ኬሚካሎቹን ስለማያመርቱ ባለው የአለም አቀፉ አቅርቦት ለመግዛት ውድድር ውስጥ መግባታቸው ጥገኛ አድርጓቸዋል።
የአፍሪካ በሽታዎች ቁጥጥርና ክትትል ማእከል ሰራተኛ የሆኑት ጆን ንኬንጋሶንግ " አለምአቀፋዊ ትብብርና መረዳዳት መፈራረሱ አፍሪካን ከምርመራ ገበያ ጨዋታ ውጭ እንድትሆን አድርጓታል" ብለዋል አክለዋል
ምንም እንኳን የአፍሪካ ሃገራት ለዚህ የሚሆን ገንዘብ ቢኖራቸውም " ሰባ የሚሆኑት አገራት ምንም አይነት የህክምና ቁሳቁሶችን ወደ ውጭ መላክ ላይ ጥብቅ የሚባል ገደብ ጥለዋል" ይህም ሁኔታ አስፈላጊ የሚባሉ የህክምና ቁሳቁሶችን ለአህጉሪቷ ማግኘት አዳጋች አድርጎታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከዚህም በተጨማሪ ሃገራቱ የጣሏቸው የእንቅስቃሴ ገደብ መመሪያዎች መመርመሪያ ጣቢያዎች ሄደው እንዳይመረመሩ እክል ሆኗል ተብሏል።
ከዚህ ሁሉ በላይ ግን በለንደን የትሮፒካል ህክምና ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ንጎዚ ኤሮንዱ የህክምና ቁሳቁስ እጥረት ዋነኛውና አፅንኦት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው ይላሉ።
"የመርመሪያ መሳሪያዎችም ሆነ ሂደቱን ለማከናወን የሚረዱ ኬሚካሎችም በበቂ ሁኔታ የሉም" ይላሉ
የናይጄሪያ የበሽታ ቁጥጥር ማዕከል የኮሮናቫይረስን ለመርመር የሚያገለግለሉ አስራ ስምንት ላብራቶሪዎች ቢኖሩትም የመርመሪያ መሳሪያ እጥረት እንዳለበት አሳውቋል።
ኬንያም ከሰሞኑ የመርመሪያ መሳሪያ እጥረት እንደ ምራቅ ናሙና መውሰጃ፣ የኬሚካል እጥረት እንዳጋጠማት አሳውቃለች።
አንድ የኬንያ ባለስልጣን ከሰሞኑ እንደተናገሩት በአገሪቷ ያለው የመርመሪያ መሳሪያ ቁጥር አምስት ሺህ ብቻ ሲሆን 24 ሺህ መመርመሪያ መሳሪያ እንጠብቃለን ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከዚህም በተጨማሪ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶችም የመርመር ሁኔታው ላይ ተፅእኖ ሳያደርሱ አልቀረምም ተብሏል።
"በአንዳንድ ማህበረሰብ ውስጥ ኮሮናቫይረስ ተገኘበት ማለት ለአድልዎና መገለል ሊያጋልጥ ይችላል" የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሯ ንጎዚ ኤሮንዲ " ሊመረጡ የሚፈልጉ የአካባቢውም መሪዎችም ሰዎች እንዲመረመሩ ላያበረታቱ ይችላሉ" ብለዋል።
የአፍሪካ ህብረትና የአፍሪካ በሽታዎች ቁጥጥርና ክትትል ማዕከልም በጋራ በመሆን የምርመራ አቅምን ለመጨመር፣ ከህሙማን ጋር ንክኪ ያላቸው ላይ የሚደረጉ ክትትሎችና ምርመራዎችንም ለማፋጠን አዲስ ጅማሮ አቋቁመዋል።
በዚህም ጅማሮ መሰረት በአህጉሪቷ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ሰዎች የሚመረመሩበትም እቅድ ተይዟል።
የኮሮናቫይረስ በእስያና በአውሮፓ በቅድሚያ በመከሰቱ እንዲሁም ኢቦላን የመሰለ ወረርሽኝን በመቋቋም ልምድ ላካበቱት የአፍሪካ ሃገራት ወረርሽኙን ለመካላከል ጊዜ ሰጥቷቸዋል














