አሜሪካ ፡ የፖሊሶችን ዘረኝነትና መድልዎን ማስቆም ይቻላታል?

አንድ ታዳጊ ከፖሊሶች ፊት ተንበርክኮ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ መገደሉን እንዲሁም በቅርቡ ፖሊስ ጄኮብ ብሌክ የተባለ ጥቁር አሜሪካዊን በበርካታ ጥይቶች ተኩሶ ማቁሰሉን ተከትሎ ተቃውሞዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ዘረኝነትንና መድልዎን በመቃወም ድምጻቸውን አሰምተዋል።

አንዳንዶች ዘረኝነት ከጭፍን ጥላቻ የሚመነጭ ይመስላቸዋል። ነገር ግን ሌሎች ሰዎችን የምናስተናግድበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ በርካታ ነገሮች አሉ።

አንዳንዴ ለራሳችን ሳይታወቀን መድልዎ እንፈጽማለን። ይህም ከእምነታችን እና ከባህሪያችንን ሊጻረር ይችላል።

እነዚህ ድርጊቶች ከግል ተሞክሮ፣ ከአስተዳደግ፣ ከባህል፣ ከምናነበው መጻሕፍት እና ከምንሰማው ዜና ይመነጫል።

አሜሪካ ውስጥ ያሉ የፖሊስ ክፍሎች ለራስ የማይታወቅ መድልዎን ለመቅረፍ የሚረዱ መርሐ ግብሮች አሏቸው። ይህም ፖሊሶች ላይ የሚስተዋለውን ዘረኝነት ለመቅረፍ ሁነኛ መንገድ ነው።

ፖሊሶች ሲያጠፉ የተለያዩ ማኅበራትና ሕግ አስከባሪዎችም ከተጠያቂነት እንዲያመልጡ ያደርጓቸዋል። ከዚህ ቀደም ከሥራ የተባረሩ ፖሊሶች ጥፋታቸውን በማያውቁ ክፍሎች ዳግመኛ ተቀጥረውም ታይቷል።

ይህን ችግር ለመቅረፍ መዋቅራዊ ለውጥ እንደሚሻ፤ በተጨማሪም ሰዎች መድልዎ እንደሚያደርጉ መገንዘብ እንዲንዲችሉ ማድረግ አስፈላጊነት አጽንኦት እተሰጠው ነው።

ለራስ የማይታወቅ መድልዎን በተመለከተ ቢቢሲን ጨምሮ በርካታ ተቋሞች ለሠራተኞቻቸው ስልጠና ይሰጣሉ።

አንድ ሰው መተንፈስ እስኪያቆም ድረስ አንገቱ ላይ መቆም እጅግ የከፋ ድርጊት ቢሆንም፤ ለራስ የማይታወቅ መድልዎ እንዲህ አይነቱና ሌላም የተለያየ ቅርጽ አለው።

ብዙ ጊዜ እኛና ሌሎችም መድልዎውን ልብ ላንለው እንችላለን።

ፖሊሶች አንዲት ጥቁር ሴትን ይዘው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ለመሆኑ ለራስ የማይታወቅ መድልዎን በስልጠና ማስወገድ ይቻላል?

እንዳለብን እንኳን የማናውቀውን መድልዎ መቀነስ ይቻላል? ሙሉ በሙሉ መድልዎን ማስወገድስ?

የመጀመሪያው እርምጃ አድልዎ እንዳለብን ማመን ነው።

ካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በዚህ ጉዳይ ላይ ያተከረ ተቋም አለ። በተቋሙ በሚዘጋጅ ፈተና ቃላት ወይም ምስል በስክሪን ላይ ቀርበው በአንዳች መንገድ እንዲያዋቀሩ ይጠየቃሉ።

ቃላቱ በጎ ወይም መጥፎም ሊሆኑ ይችላሉ። የሚታዩት ምስሎች የጥቁሮችና የነጮች ናቸው። ብዙ ነጮች በጎ ነገርን ከነጭ ጋር፣ መጥፎ ነገርን ከጥቁር ጋር ያዛምዳሉ።

ይህን ፈተና ለብዙዎች አይን ገላጭ ነው። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2007 እስከ 2015 በተሠራ ጥናት መሠረት 73 በመቶ ነጮች፣ 34 በመቶ ጥቁሮች እና 64 በመቶ የሌላ ዝርያ ያላቸው ሰዎች ነጭን የሚደግፍና ጥቁር ላይ መደልዎ የሚያሳድር አመለካከት አላቸው።

የአራት ዓመት ሕጻናት ሳይቀር እንዲህ አይነቱ መድልዎ ተስተውሎባቸዋል።

በዝግመተ ለውጥ ለሰው ወይም ስለእንስሳት ያለን አመለካከት ራሳችንን እንድንከላከል ይረዳ ይሆናል። አሁን ግን ወደ መድልዎ ይወስደናል።

የካሊፎርንያ ዩኒቨርስቲው ጄፍሪ ሸርማን "ከአንድ ቀን በላይ የባህሪ ለውጥ ማምጣት ከባድ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ" ይላሉ።

ነገር ግን አንዳንድ ውጤታማ የለውጥ መንገዶች አሉ።

2012 ላይ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው፤ ከላይ የተጠቀሰውን ፈተና ወስደው ምን ያህል መድልዎ እንደተጫናቸው የተረዱ ሰዎች አሉ።

ሰዎቹ ለሁለት ወር ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ መድልዎን በመቀነስ ረገድ አንጻራዊ ለውጥ አሳይተዋል።

አንደኛው የስልጠና መንገድ ስለሆነ ሰው አስቀድሞ የሚቀመጥ ግምትን ማስወገድ ላይ ያተከረ ነው።

የሥነ ልቦና ተመራማሪዋ ፓትሪሽያ ዴቪን፤ ረዥም ጥቁር ሰው ሲታይ “ቅርጫት ኳስ ይጫወታል” ተብሎ ይገመታል። ይህ ግን ማስረጃ ያለው ሳይሆን ጭፍን መድልዎ ነው።

ይህን ጭፍን መድልዎ መለወጥ ቀላል አይደለም።

ሁሉም ረዥም ጥቁር ሰው ቅርጫት ኳስ እንደማይጫወት ለመረዳት ቢያንስ ሦስት ጥቁር ረዥም ቅርጫት ኳስ የማይጫወቱ ሰዎች ማወቅ እንደሚጠይቅ በማስረጃነት ያቀርባሉ ተመራማሪዋ።

መድልዎን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ስለመቻሉ እርግጠኛ ባይሆኑም በመጠኑ ባህሪን መቀነስ እንደሚቻል ያምናሉ።

"ስር የሰደዱ አስተሳሰቦችን መለወጥ እንችላለን ብዬ ባላስብም አመለካከታችንን በተወሰነ መንገድ አቅጣጫ ማስቀየር እንችላለን። መድልዎ እንዴት ወደተዛባ ወይም ወደማይፈለግ ድምዳሜ እንደሚያደርሰን እንገነዘባለን። ትክክለኛ አመለካከታችንን ለማንጸባረቅ መሞከርም እንጀምራለን" በማለትም ያብራራሉ።

ጾታን መሠረት ያደረገ መደልዎ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምህንድስና፣ በሒሳብ ሴቶች እንዳይቀጠሩ ምክንያት ነው።

በዊስኮንሰን ጾታን መሠረት ስላደረገ መድልዎ ስልጠና ከመሰጠቱ በፊት ሴቶች የሚቀጠሩት 32 በመቶ ነበር። ከስልጠናው በኋላ ግን ወደ 47 በመቶ ከፍ ብሏል።

በስታንፎርድ 61 ፖሊሶች ላይ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው፤ ወንጀል፣ ምርመራ፣ እስር የሚሉትን ቃላት ከጥቁሮች ጋር ያያይዟቸዋል።

በዩኒቨርስቲው የሚሠሩ ጥቁሮችና ነጮችን ፎቶ አሳይተው፤ የትኞቹ ወንጀለኛ ይመስላሉ ተብለው ሲጠየቁ የቆዳ ቀለማቸው ጥቁር ሰዎችን መርጠዋል።

ሌላ የሥነ ልቦና ተመራማሪም ጥቁሮች ወንጀለኛ ብሎ መበየን፣ የሞት ፍርድ ማስተላለፍም እንደሚደጋገም ያስረግጣሉ።

ፖሊሶች በየቀኑ በሚያሰማሩት ኃይል ላይ ለራስ የማይታወቅ መድልዎ ምን ሚና እንዳለው ገና እየተጠና ነው።

ጥናቶች እንደሚየሳዩት ግን፤ መሣሪያ ያልያዙ ጥቁሮች ላይ የመተኮስ እድላቸው ሰፊ ነው።

ፖሊሶች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

"ይህን ሰው የማስቆመው ለምንድን ነው?"

የወንጀል ጥናት ባለሙያዋ ሎሪ ፍሪደል እንደሚሉት፤ ለፖሊሶች የሚሰጡት ስልጠና፤ አንድን ሰው የማስቆመው ለምንድን ነው? ብለው እንዲጠይቁ ያነሳሳል።

"ይህን ሰው የማስቆመው ለምንድን ነው? ብለን ባዶ ቦታ እንተዋለን። ከዚያ የሚቀርቡት ምርጫዎች ሰውየውን የማስቆመው ዘሩን መሰረት በማድረግ ነው? ወይስ ቤት አልባ? እያልን አማራጮች እንሰጣለን።"

ፖሊሶች ከመድልዎ ይልቅ መረጃ ላይ እንዲያተኩሩ እንደሚያበረታቱም ያስረዳሉ።

"አንድ ማኅበረሰብ ውስጥ መድልዎ ባላቸው ሰዎች ምክንያት ለፖሊስ ቢደወልም ፖሊስ መድልዎውን ማስቀጠል የለበትም” ይላሉ።

የፖሊስ ክፍሎች በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እያወጡ ይህን ስልጠና ቢሰጡም፤ ሁሉም ሰው ግን ውጤታማ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም።

ሰዎች መድልዎን መቆጣጠር እንደሚችሉ በሚገልጽ ሁኔታ ስልጠና መሰጠት እንዳለበት የሚናገሩ ባለሙያዎችም አሉ።

በመድልዎ ላይ ጥናት የሠሩት ልዊስ ጄምስ ከስልጠና ጎን ለጎን ሌሎችም እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው ይጠቁማሉ።

ለምሳሌ የፖሊሶችን እንቅስቃሴ የሚከታተልና ቪድዮ የሚቀርጽ መሳሪያ መለያ ልብሳቸው ላይ ማድረግ አንድ አማራጭ ነው።

ባለሙያዎች እንደሚሉት መድልዎን ለማስወገድ፤ ራስን ለተለያዩ ተሞክሮዎች እንዲሁም አካባቢዎች ማጋለጥ አጋዥ ነው።

ለሰባት ዓመታት ከጎዳና ተዳዳሪዎች ጋር የሠሩት ፍሪደል፤ ተሞክሯቸው አመለካከታቸውን እንደቀየረው ያስረዳሉ።

የጎዳና ተዳዳሪዎችን በተመለከተ ለራሳቸው ያልታወቀ መድልዎ እንደነበራቸው፤ በማስታወስ በጊዜ ሂደት ግን ይህን መቅረፍ መቻላቸውን ያክላሉ።

‘ኮፊ ዊዝ ኤ ካፕ’ ወይም ከፖሊስ ጋር ቡና እንጠጣ የተሰኘ ፕሮጀክት ሌላው ምሳሌ ነው። የአንድ ማኅበረሰብ አባላት ከፖሊሶች ጋር እንዲተዋወቁ ይረዳል።

ማኅበረሰብ ተኮር ፕሮጀክቶች ረዘም ላለ ጊዜ ሲቆዩ የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ።